“…ስለተበደልን ከመንበረ ተክለሃይማኖት ተነጥለን መንበረ ሰላማ የሚባል የፕትርክና መንበር አቁመናል…” ያሉ አባቶች ከሰሞኑ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በሰላም ጉዳይ ዙሪያ ለመወያየት የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ መግለጻቸውን ተከትሎ የወልቃይት ጠገዴ የሃይማኖት አባቶች አወገዙት። “በሃይማኖት ስም የትህነግን ዓላማ ማራመድ አይቻልም። ብዙ ቁስል አለብን” ብለዋል።
ወደ አዲስ አበባ እንዲያቀና ከተዋቀረው ልዑካን መካከል አንዱ የሆኑት አባ አረጋዊ ፣ ልዑኩ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በወቅታዊው ጉዳዮች ዙሪያ ይወያያል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ዋዜማ ላይ ቃለ በቃል ከተጻፈው ለመረዳት ተችሏል።
በቅርቡ ፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በክልሉ ድጋሚ ጦርነት እንዳይካሄድ ለማስቀረት የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የክልሉ ተወላጆች የጦርነት ነጋሪት ሰባኪ የሆኑ አካላትን በመምከር የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።
ይህንኑ ተከትሎ፣ በክልሉ የሚገኙት የቤተክርስቲያኒቱ አባቶችና የ”መንበረ ሠላማው” አባላት በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ መቀሌ ውስጥ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውንና በጽሁፍ መግለጫ አሰራጭተዋል። ይህንኑ መግለጫ በማህበራዊ ሚዲያና የተለያዩ የዜና አውታሮች ተቀባብለውታል። መረጃውን ሲያሰራጩ የግል አስተያየታቸውን በመጨመር ትችትና ማበረታቻም የሰጡ ጥቂት አይደሉም።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ እንዳሰጋቸው የገለጹት የመንበረ ሰላማ አባቶች የሃይማኖት አባቶቹ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተያየት በትግራይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንደማያንጸባርቅ በመግለጫቸው አስፈረዋል። ትህነግ ከሻዕቢያ ጋር ህብረት መፈጠሩን በገሃድ እያስታወቀና የጦርነት ዝግጅት እየደረገ መሆኑን ይፋ እያስታወቀ ባለበት ሁኔታ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ማሳሳቢያ ከትግራይ ክልል ነባራዊ ሁኔታ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ማስታወቃቸው ግርምት መፈጠሩን በረካቶች ታዝበዋል።
“የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና አጋሮቹ [ሻዕቢያና ፋኖ ለማለት ነው] ባለፉት አምስት ዓመታት በትግራይ ህዝብ ላይ ባደረሱት ወታደራዊ ጥቃትና ኢኮኖሚያዊ በደል ሳቢያ ሕዝቡ በከፍተኛ ስቃይ እና መከራ ውስጥ እንደሚገኝ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው” ያለው የሃይማኖት አባቶቹ መግለጫ፣ “የፕሪቶሪያ የተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት ምንም እንኳ በትግራይ የተኩስ ድምጽን ቢያስቀረም፣ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ባለመተግበሩ በተለይ ከቀያቸው የተፈናቀሉ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ወደ መኖሪያቸው ባለመመለሳቸው በሞትና በስቃይ መካከል ይገኛሉ” ሲል ትህነግ እንደሚለው በተመሳሳይ ኮንኗል። ይሁን እንጂ መንግስት የተፈናቀሉ ይመለሱ ማለቱን በመግለጫቸው አላካተቱም። የወላቃይት ጠገዴ የሃይማኖት አባቶችም ከዚህ ተነስተው ነው “በእምነት ስም የትህነግን ዓላማን ማሳካት አይቻልም” ሲሉ ተቃውሞ ያሰሙት።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የትግራይን እውነተኛ ምስል እና የትግራይ ህዝብ ምኞት ዘላቂ ሰላም መሆኑን ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሚያስረዳ ልዐካን ቡድን ለመላክ መወሰናቸው ተገልጧል።
የመንበረ ሰላማ አባቶች ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ወክለው የሚላኩትን ሽማግሌዎች በክብር ተቀብለው እንደሚያነጋግሩ እምነታቸው የጸና መሆኑንም ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ፣ በክልሉ ለሰላም የሁለት ቀናት ጾምና ጸሎት እንዲደረግም ጥሪ አድርገዋል። በትግራይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶችና ጳጳሳት አቡነ ማትያስ ከሚመሩት ዋናው ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጥለው “መንበረ ሠላማ” የተባለውን ሲኖዶስ በተናጥል ያቋቋሙት፣ በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ሕዝብ ላይ መዓት ሲወርድና በቤተክርስቲያናት ላይ ጉዳት ሲደርስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አጋርነቱን ማሳየት አልቻለም በማለት ነበር። እነሱ ይህን ቢሉም “ትህነግ አማራና አፋር ክልልን ወሮ በጅምላ ሲጨፈጭፍና ሲዘርፍ፣ ወታደሮቹ ሲያወድሙና በጅምላ ሲደፍሩ እነዚሁ አባቶች መቀለ ቁጭ ብለው እያዩና እየሰሙ ያሉት ነገር የለም” ሲሉ ለህልውና የተደረገውን ውጊያና ሰሜን ዕዝ በመመታቱ ሳቢያ የተጀመረውን ውጊያ አለማውገዛቸውን በማንሳት ከሃይማኖት ይልቅ የፖለቲካ ተቋም እንደሆኑ አድርገው ይገልጹዋቸዋል።
ትግራይ የሚገኙ አባቶች የቤተክርስቲያኗን ቀኖናዎችና ሕግጋት በጣሰ መልኩ በተናጥል ሲኖዶስ ማቋቋማቸውን ያወገዘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በክልሉ የሚገኙት አባቶች ወደ እናት ቤተክርስቲያናቸውና ወደ ሲኖዶሱ እንዱመለሱ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱን ይታወሳል።
የወልቃይት ጠገዴ አባቶች ” አዲስ አበባ መሄድ ችግር የለውም፣ ችግሩ የሚመጣው ተከዜን ለመሻገር ከታሰበ ነው” በማለት የአዲስ አበባውን ጉዞ አውግዘው አስተያየት ሰጥተዋል። እነዚሁ አባቶች ጣና ቲቪ በተሰኘ የዩቲብ ቻናል እንዳሉት ” ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ብዙ መከራ አሳልፈናል። ወደዛ ተመልሰን መግባት አንፈልግም” ብለዋል።
“ሃይማኖታዊ ስብከትና ትምህርት በአማርኛ በማስጠታቸው ቃፍታ ላይ ለሊት ወደ አገልግሎት ሲሄዱ ተያዘው ምላሳቸውን ተቆርጠው ተሰቃይተው የሞቱት ቄስ ይርጋ አለሜን አንረሳም” ሲሉ የነበረባቸውን አስከፊ ጭቆና ያስታወሱት አባቶች፣ ዛሬ ላይ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይለይ ትህነግን ዳግም ማየት እንደማይፈልጉ ይፋ አድርገዋል። ይህንኑም ዕለት ዕለት እንደሚያስተምሩ አመልክተዋል።
“ዓላማቸው ትህነግ ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ በመያዝ ተፈናቃቶችን ከነ አስተዳደሩ ይመለስ የሚል አጀንዳ ለማራመድ ነው። አቡነ ሰላማ የትህነግ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ክንፍ ነው” ያሉት እነዚህ የኃይማኖት አባቶች፣ ህዝብ ያነቃል፣ ያስተምራል የሚሉትን ጠባብ፣ ትምክህተኛ እያሉ ሲያሳድዱ እነዚህ የኃይማኖት አባቶች በዝምታ የሚመለከቱ ነበሩ ሲሉ ከሰዋቸዋል።
“30 ኣመት ወልቃይት ጠገዴ ተሰቃይቷል ይህ እንዲደገም አንፈቅድም” ሲሉ የአዲስ አበባውን ጉዞ አንስተው ተቃውሞ ያሰሙት የወልቃይት ጠገዴ አባቶች፣ አቡነ ሰላማ በሃይማኖት ስም የተደራጀ የትህነግ አንድ አደረጃጀት በመሆኑ ወደ አራት ኪሎ መሄዱ ባያሰጋቸውም ወደ ተከዜ ሊያመራ ማቀዱ ስጋት እንደሚሆንባቸው አልሸሸጉም።



