የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ይፋ እንዳደረገው በቁጥጥር ስር ከዋሉት 3800 በላይ አጭበረባሪዎች መካከል 2077 የሚሆኑት ሃሰተኛ ሰነድ ያቀረቡ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 275 ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሳይኖራቸው ፓስፖርት ለማውጣት ሲሞክሩ፣ እንዲሁም የተቀሩት በተለያየ መንገድ በተጭበረበረ ሰነድ ፓስፖርት ለማውጣት ሲሞክሩ የተያዙ ህግ ተላላፊዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ስታስጀምር አብዝተው የተቃወሙት በዋናነት ማንነታቸውን በመደበቅ በሃሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ስም የተመዘገቡ ስለመሆናቸው አገራቸውን የሚወዱ ሲገልጹ ነበር። ከዚህም በላይ በውጭ አገር የሚገኙ በተቃዋሚነት የሚታወቁ ጉዳዩን የኢትዮጵያን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ከተለያዩ ኃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር በማያያዝ ለማደነቃቀፍ ሲሞክሩ ታይተዋል። ኢትዮሪቪው ባላት መረጃ በመጪው ዓመት ይህንኑ የዲጂታላይዜሽን እንቅስቃሴ በእምነት “መምህሮች” በዘመቻ ለማቀጣጠል ዕቅድ ተያዟል።

ተቋሙ አሰራሩን ካሻሻለ በሁዋላ ከ3 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በተጭበረበረ ሰነድ ፓስፖርት ለማውጣት ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት አስታውቀዋል። የታያዙትን አጭበርባሪዎች በአገር ለይተው ባይገልጹም ስለምርመራው የሚያውቁ የኤርትራ ተወላጆች እንዳሉበት ለኢትዮሪቪው ነገረዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገለግሎት ከ2016 ዓ.ም ጀመሮ ተግባራዊ የሆነውን የሪፎርም አጀንዳዎች ግምገማ ውጤትን ሲያቀርቡ ነው ይህን ያሉት።
ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገለግሎት ባለፉት ሁለት ዓመታት አዲስ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ ከቀድሞው የተሻለ ውጤት ማስመዘገቡን አመልክተዋል። በዚሁ የተሻሻለውና ቁጥጥርን በሲሰተም በመጠቀም 3 ሺህ 868 ሰዎች የተጭበረበረ ሰነድ በመጠቀም ፓስፖርት ለማውጣት የሞከሩ አጭበርባሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት አጭበርባሪዎች ብዛት የሚያሳየው የተጀመረው ሪፎርሙ የአገልግሎት ጥራቱና ቁጥጥሩ ጠንካራ እየሆነ መሄዱን ነው። ከሁሉም በላይ ግን አሰራሩ ተቋማዊ ደህንነትን ማረጋገጥ መቻሉን ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሯ ይፋ ባያደርጉትም የኢትዮጵያዊነት ዜግነት ሳይኖራቸው ፓስፖርት እንዲሰጣቸው ካመለከቱት አጭበረባሪዎች መካከል አብዛኞቹ የኤርትራ ተወላጆች መሆናቸውን ለምርመራ ስራው ቅርብ የሆኑ ለኢትዮሪቪው ገልጸዋል። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ቀደም ሲል በዚሁ የማጭበርበር መንገድ ከተቋሙ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር የኢትዮጵያ ፓስፖርት የያዙ በረካቶች መለየታቸውን ጠቁመዋል። ማጥራቱ በዘመቻ ሊካሄድ እንደሚችልም ገልጸዋል። የዲጂታል ሲሰተም አሰራርንና የፋይዳ መታወቂያን ወይም ብሄራዊ መታወቂያን የሚቃወሙ ወገኖች ለምን ሲቃወሙ እንደነበር ይህ አንዱ ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል።
ጋዜጣ ፕላስ ተቋሙን ገልጾ እንደዘገበው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት 1 ሚሊዮን 465 ሺህ 989 ፓስፖርት ተሰጥቷል ብለዋል። የ2017 ዓ.ም አፈጻጸም አስመልክቶ ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት መግለጫ ሲሰጡ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ከተሰጠው የፓስፖርት ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው አንስተው፤ ይህም የሆነው በተቋሙ ተግባራዊ በተደረገው ሪፎርም ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
ለፓስፖርት በኢሚግሬሽን ቢሮዎች ተራ የሚጠብቁ ግለሰቦች ቁጥር መቀነስ ተችሏል ብለው፤ በቀጣይም ከዚህ በበለጠ እየቀነሰ እንደሚሄድ ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ወደ ስራ የገባው ኢ-ፓስፖርት አገልግሎት በጎተራ ቅርንጫፍ መሰጠት የተጀመረ መሆኑንም አስታውሰዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሌብነትና በተጭበረበረ አሰራር ከፍተኛ ኃላፊዎች ሳይቀር ከደላላ ጋር በትስስር ዝርፊያ የሚፈጽሙበት ተቋም ነው። ይህ “ሽንፍላ” በሚል ስያሜ የሚታወቀው ተቋም በተደጋጋሚ ኃላፊዎቹ ቢታሰሩም ምዝበራ ሊቆም ያልቻለበት ተቋም ነው። ይህ ከአገር ደህንነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ተቋም በዚህ ደረጃ በሌብነት የተተበተበ በመሆኑ የተነሳ ራሱን በዲጂታል ሲስተም ሊያደራጅና አሰራሩን ሊያነጻ እንደሚገባ በተደጋጋሚ አሳብ ሲቀርብ እንደነበር አይዘነጋም።
ዛሬ ላይ ለውጥ ያሳየው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊ አሰራር መገንባቱን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት አፋቸውን ሞልተው ተናግረዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከክልል መዝጋቢ እና ባለድርሻ አካላት ጋር የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያተኮረ ጉባኤ እያካሄደ ባለበት ወቅት የመንግስት ሚዲያዎች እንዳሉት በመድረኩ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፣ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራር እና አባላት እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በመክፈቻ ንግግራቸው፥ አገልግሎቱ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት አስታውሰዋል። ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ከማሟላት አንጻርም ጉድለቶች እንደነበሩ በመጥቀስ፥ አገልግሎቶቹ ከማህበረሰቡ ፍላጎት ጋር ያልተጣጣሙ ሆነው መቆየታቸውን አንስተዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ፈጣንና ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማድረግ የብልጽግና ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው አገልግሎቱም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሪፎርም ማካሄዱን ገልጸዋል።
ለዚህም 11 የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርጸው ወደ ስራ መገባቱን በማውሳት፥ ኋላቀር የነበረውን የባዮሜትሪክ መረጃ መቀበያ ስርዓት ወደ ዘመናዊ አሰራር መቀየር መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት በማተም ችግሩን በጉልህ መቅረፍ መቻሉን ተናግረው ከአስር በላይ የጉዞ ሰነዶች እንዲዘምኑ መደረጋቸውን አስረድተዋል።
የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመን ወደ ዲጂታላይዜሽን ስኬታማ ሽግግር መደረጉን ገልጸው፥ በተቋሙ የሪፎርም ሥራዎች ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊ አሰራር ገንብተናል ነው ያሉት።
ከዜጎች ፍላጎት አንጻር በ2018 በጀት ዓመት አገልግሎቱን ይበልጥ በማዘመንና በማቀላጠፍ የህዝብ እርካታን ለማሳደግ ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል። ባለድርሻ አካላትም ለአገልግሎቱ ግብ መሳካት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።



