ሰውን በባርነት ወይም ባርነት መሰል ተግባር፣ በአገልጋይነት ወይም በእዳ መያዣነት መያዝ፣ አካሉን ማውጣት፣ ዝሙት አዳሪነት ወይም መሰል የወሲብ ብዝበዛ፣ ለግዳጅ ሥራ፣ ለልመና፣ ለወንጀል ተግባር፣ ለግዳጅ ጋብቻ፣ ማህፀን ኪራይ፣ ህፃናትን በጉልበት ሥራ መበዝበዝ እና መሰል ተግባራትን መፈፀም እንዲሁም ህፃናትን ለመበዝበዝ አላማ መመልመልን፣ ማጓጓዝን፣ ወደሌላ ሰው ማስተላለፍን፣ ማስጠለልን፣ መደበቅን ወይም መቀበልን የሚያካትት የወንጀል ድርጊት ነው፡፡
መግቢያ
በሰዎች መነገድ እና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድምበር የማሻገር ወንጀል በአለማቀፍ ደረጃ ስጋት ከሆኑ ወንጀሎች መካከል አንዱ በመሆኑ ወንጀሉን በተደራጀ መልኩ ለመከላከል በአለማቀፍም ሆነ በሀገራት ደረጃ ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡ አገራችንም የዚህ ወንጀል ተጠቂ እንደመሆኗ ወንጀሉን ለመከላከል እየሰራች ትገኛለች፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ በሰዎች መነገድ እና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድምበር የማሻገርን ወንጀል ምንነት እንዲሁም በሰዎች መነገድ እና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድምበር የማሻገርን ወንጀል እና ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ተቀፅላ ወንጀሎች የሚያስከትሉትን ቅጣት እንመለከታለን፡፡
በሰዎች መነገድ እና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድምበር የማሻገር ወንጀል ምንነት
በሰው መነገድ እና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድምበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 3 መሰረት በሰው የመነገድ ወንጀል ሰውን በባርነት ወይም ባርነት መሰል ተግባር፣ በአገልጋይነት ወይም በእዳ መያዣነት መያዝ፣ አካሉን ማውጣት፣ ዝሙት አዳሪነት ወይም መሰል የወሲብ ብዝበዛ፣ ለግዳጅ ሥራ፣ ለልመና፣ ለወንጀል ተግባር፣ ለግዳጅ ጋብቻ፣ ማህፀን ኪራይ፣ ህፃናትን በጉልበት ሥራ መበዝበዝ እና መሰል ተግባራትን መፈፀም እንዲሁም ህፃናትን ለመበዝበዝ አላማ መመልመልን፣ ማጓጓዝን፣ ወደሌላ ሰው ማስተላለፍን፣ ማስጠለልን፣ መደበቅን ወይም መቀበልን የሚያካትት የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ 8
በሌላ በኩል ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ታስቦ ሰውን በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር እንዲገባ፣ እንዲወጣ፣ በኢትዮጵያ ግዛት እንዲተላለፍ ማድረግ ወይም ከሀገር ለማስወጣት ዝግጅት ማድረግ፣ ማጓጓዝ ወይም የመቀበል ድርጊት መሆኑን ከአዋጁ አንቀፅ 8 መረዳት ይቻላል፡፡
በሰዎች መነገድ ወንጀል የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት
ማንኛውም ሰው ሌላውን ሰው በባርነት ወይም በባርነት መሰል ተግባር፣ በአገልጋይነት ወይም ዕዳ መያዣነት የያዘ፣ አካሉን በማውጣት ወይም በዝሙት አዳሪነት ወይም መሰል የወሲብ ብዝበዛ የመፈፀ፣ በግዳጅ ሥራ ወይም አገልግሎት፣ በልመና፣ በወንጀል ተግባር፣ በግዳጅ ጋብቻ ወይም በማህፀን ኪራይ ያሰማራ ወይም ህፃናትን በጉልበት ሥራ የበዘበዘ ወይም መሰል ብዝበዛዎችን የፈፀመ እንደሆነ ከ7 እስከ 15 አመት ፅኑ እስራት እና ከብር 20 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ በአዋጁ አንፅ 3 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት ባለፈ ሰው ላይ ብዝበዛ የተፈፀመ ወይም መፈፀሙ ተጀምሮ እንደሆነ ብዝበዛውን የፈፀመውም ሆነ በሂደቱ የተሳተፈ ሰው ከ7 እስከ 12 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 40 ሺ እስከ 100 ሺ በሚደርስ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም በሰዎች መነገድ ወንጀሉ የተፈፀመው በህጻናት፣ በአካል ጉዳተኞች ወይም አእምሮ ህመምተኞች ላይ ከሆነ፣ አደንዛዝ እፅ፣ መድኀኒት ወይም የጦር መሳሪያ በመጠቀም ከሆነ፣ ወንጀሉ በመንግስት ሰራተኛ ወይም ባለስልጣን የተሰጠውን ሀላፊነት መከታ በማድረግ የፈፀመው ከሆነ እና የአገር ውስጥ እና የውጪ አገር የሥራ ስምሪት ፈቃድ ኖሮት እሱኑ ተገን አድርጎ የፈፀመው ከሆነ ቅጣቱ ከ10 እስከ 20 አመት ፅኑ እስራት እና ከብር 30 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ወንጀሉ በተደራጁ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን/በመምራት/በማስተባበር ከተፈፀመ፣ በተጎጂው ላይ የማይድን በሽታ ካስከተለ፣ በተጎጂው ህይወትና ደህንነት ላይ አደጋ ከጣለ ወይም ከባድ የአካል ጉዳት ካስከተለ ወይም ለኢሰብአዊ አያያዝ የዳረገ ከሆነ ቅጣቱ ከ15 -25 አመት ፅኑ እስራት እና ከብር 50 ሺህ እስከ ብር 150 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይሆናል፡፡ ይህ ወንጀል በተጎጂው ላይ ሞትን አስከትሎ ከሆነ እንደየ ሁኔታው ከ15 እስከ 25 አመት ወይም እድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት እና አስከ ብር 200 ሺ የገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡
በሰዎች መነገድ ወንጀልን መደገፍ እና በሌሎች ዝሙት አዳሪነት መጠቀም ወንጀል
በሰዎች የመነገድ ወንጀል ውስጥ ቀጥተኛ ተካፋይ ባይሆንም ወንጀሉን መደገፍ በራሱ ወንጀል ሲሆን በሌሎች ዝሙት አዳሪነት መነገድም እንዲሁም እራሱን ችሎ ወንጀል ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 5 ላይ እንደተደነገገው ለዚህ ወንጀል መፈፀም ምቹ ሁኔታን መፍጠረ ንብረቱን ለዚህ ወንጀል መፈፀሚያነት እንዲውል መፍቀደ፣ ማከራየትና ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከ3 እስከ 7 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና እስከ ብር 50 ሺህ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡
በተያያዘም የተጭበረበር፣ ሀሰተኛ ወይም በህገወጥ መንገድ መታወቂያ ወይም የጉዞ ሰነድ ማዘጋጀት፣ መስጠት፣ ማቅረብ ወይም ይዞ መገኘት ከ5 እስከ 15 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 10 ሺ እስከ ብር 50 ሺ በሚደርስ መቀጮ የሚያስቀጣ ነው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ከሌሎች ሰዎች ዝሙት አዳሪነት ወይም የሥነ ምግባር ብለሹነት ለመጠቀም ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ስጋ ፍላጎት ለማርካት በማሰብ ሌላኛውን ሰው ለዝሙት ተግባር ማሰማራት፣ ማገናኘት፣ በዝሙት አዳሪ ቤት ማስቀመጥ፣ ንብረቱን ለዚህ ተግባር ማዋል ወይም መፍቀድ እና መሰል ተግባራትን መፈፀም ከ1 እስከ 3 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 10 ሺህ እስከ ብር 50 ሺህ በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ በአዋጁ አንቀፅ 7 ተደንግጓል፡፡
ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት
በአዋጁ አንቀፅ 8 መሰረት ማንኛውም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ሰውን በህገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት አንዲገባ ማድረግ፣ ከኢትዮጵያ አንዲወጣ፣ በግዛቷ እንዲተላለፍ ማድረግ፣ ከአገር ለማስወጣት ዝግጅት ማድረግ፣ በሂደት ላይ መገኘት፣ ማጓጓዝ ወይም መቀበል ከ5 እስከ 10 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 10 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ነገር ግን ወንጀሉ የተፈፀመው በህጻናት፣ በአእምሮ ህመምተኞች ወይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ከሆነ፣ አደንዛዝ እፅ፣ መድኀኒት ወይም የጦር መሳሪያ በመጠቀም ከሆነ፣ ወንጀሉ በመንግስተ ሰራተኛ ወይም ባለስልጣን የተሰጠውን ሀላፊነት መከታ በማድረግ የተፈፀመ ከሆነ እና የውጪ አገር የሥራ ስምሪት ፈቃድ ኖሮት ፍቃዱን ተገን አድርጎ የተፈተመ ከሆነ ቅጣቱ ከ7 እስከ 15 አመት ፅኑ እስራት እና ከብር 20 ሺህ እስከ ብር 150 ሺህ በሚደርስ መቀጮ የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ወንጀሉ በተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን/በመምራት/ በማስተባበር ከተፈፀመ፣ በተጎጂው ላይ የአካል ጉዳት፣ የማይድን በሽታ ወይም ዘላቂ የአዕምሮ ጉዳት ካስከተለ፣ የተጎጂውን ህይወትና ደህንነት አደጋ ላይ ከጣለ ወይም ወይም ለኢሰብዓዊ አያያዝ ከዳረገ ቅጣቱ ከ10 እስከ 20 አመት ፅኑ እስራት እና ከብር 30 ሺህ እስከ ብር 150 ሺህ በሚደርስ መቀጮ የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡ ከዚህም አልፎ ወንጀሉ ተጎጂው ላይ ሞትን አስከትሎ ከሆነ እንደየ ሁኔታው ቅጣቱ ከ15 እስከ 25 አመት ወይም አድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም ሞት እና አስከ ብር 200 ሺህ መቀጮ ያስቀጣል፡፡
በህገወጥ መንገድ መቆየትን ወይም ድንበር ማሻገር ወንጀልን መርዳት
ልክ እንደ በሰዎች መነገድ ወንጀል በዚህ ወንጀል ውስጥ ቀጥተኛ ተካፋይ ባይሆንም ወንጀሉን መደገፍ በራሱ ወንጀል ነው፡፡ በአዋጅ አንቀፅ 9 መሰረት የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ አትዮጰያዊ ያልሆነ እና በአገራችን ውስጥ ለመኖርም ሆነ ለመቆየት የፀና ፈቃድ የሌለውን ሰው በአገራችን ግዛት ውስጥ እንዲቆይ ሀሰተኛ ሰነድ በመስራት፣ በማቅረብ እና በመሰል መንገድ መርዳት ከ5 እስከ 10 አመት በሚደርስ ፅኑ አስራት እና ከብር 10 ሺህ አስከ ብር 50 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ በተያያዘም በህገወጥ መንገድ ድንበር ለመሻገር የሚውል ሀሰተኛ የጉዞ ሰነድ፣ መታወቂያ ሰነድ ማዘጋጀት፣ ይዞ መገኘት፣ ማቅረብ ወይም ማስተላለፍ ከ5 እስከ 10 አመት ፅኑ እስራት እና ከብር 10 ሺህ እስከ 50 ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ከአዋጅ አንቀፅ 10 መረዳት ይቻላል፡፡
በህገወጥ መንገድ ሰውን ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ
በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 3 እና 5 ከተደነገጉት ሁኔታዎች ውጪ ማለትም ሰዎችን ለብዝበዛ አላማ ወይም በህገወጥ መንገድ ድንበር ለመሻገር ሳይሆን በመደበኛው ህጋዊ አሰራር ሰውን ወደ ውጪ አገር ለሥራ የመላክ የፀና ፈቃድ ሳይረኖረው ወይም ፈቃዱ የነበረው ቢሆንም ይሄው ፈቃድ ታግዶ ወይም ተሰርዞ ባለበት ሁኔታ አለያም ከተሰጠው ስምሪት ውጪ ፈቃድ ወዳልተሰጠው አገር ሰውን ለሥራ መላክ ከ7 እስከ 12 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 20 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ በሚደርስ መቀጮ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡
በተጨማሪም ይኸው ወንጀል የተፈፀመው የጉብኝት፣ የህክምና፣ የትምህርት ወይም የመሰል ጉዳዮች ቪዛን ሽፋን በማድረግ ከሆነ ቅጣቱ ከ7 እስከ 15 አመት ፅኑ እስራት እና ከብር 30 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይሆናል፡፡ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ የተላከው ሰው ሰብአዊ መብቱ፣ ህይወቱ፣ አካሉ ወይም ሥነልቦናው ለጉዳት ከተዳረገ የላከው ወንጀለኛ እንደየወንጀሉ ክብደት ከ15 እስከ 25 አመት በሚደርስ ወይም በእድሜ ልክ ፅኑ አስራት እና ከብር 50 ሺህ አስከ ብር 200 ሺህ በሚደርስ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በሰዎች መነገድ እና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል የዜጎችን በተለይም የሴቶችን፣ የህጻናትን እና የአፍላ ወጣቶችን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል በአገርና በህዝብ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝ ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም ማህበረሰቡ የወንጀሉን አስከፊነት አውቆ በወንጀሉ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ልጆቹም ሆነ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ለጉዳት እንዳይዳረጉ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር


