‘በቡና መፈልፈያና ማጠቢያ ኢንቨስትመንት ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መንግስት ከሊዝ ነጻ መሬትና ብድር ያመቻቻል’ – ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ
የቡና ምርታማነትና ጥራት ማሻሻያ የንቅናቄ መድረክ በነቀምቴ ከተማ ተካሂዷል።
መድረኩን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከግብርና ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር አዘጋጅተዉታል።
በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዶ/ር አዱኛ ደበላን ጨምሮ የተለያዩ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ፤ቡና ላኪዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር የኦሮሚያ ክልል በቡና ምርትና ምርታማነት ላይ ያለውን ከፍተኛ አቅም በበቂ አመራር ሰጪነት መጓደል ምክንያት በሚፈለገው ልክ ወደ ትሩፋት ሳንቀይር ቆይተናል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄን ታሪክ ለመቀየር በከፍተኛ ትኩረት አየተሰራ ይገኛል ብለዋል። በቡና ላይ የሚነሳው የጥራት ጥያቄ በዋናነት በ3 ምክንያቶች የሚከሰት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
እነዚህም ጉዳዩ የአመራር አጀንዳ አለመሆኑ፤ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በሚፈለገው ልክ ማሳደግ አለመቻልና የንግድ ስርአቱ መበላሸት ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የቡና ምርትና ምርታማነትን ብሎም ጥራትን ለማረጋገጥ አመራሩ ጉዳዩን በእቅድ መምራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ማሳደግና የንግድ ስርአቱን ማስተካከልም በልዩ ሁኔታ ሊሰራበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። የቡና ምርታማነት እና ጥራት ማሻሻያ ንቅናቄ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር መውረድ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
በዘንድሮ አመት በቡና መፈልፈያና ማጠቢያ ኢንቨስትመንት ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መንግስት ከሊዝ ነጻ መሬትና ብድር እንደሚያመቻች ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል።
አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የቡና ምርት ከአመት አመት እየጨመረ እንደሚገኝ የተናገሩት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ከዚህ ውስጥም የኦሮሚያ ክልል ሰፊውን ድርሻ እንደሚወስድ አብራርተዋል።
2000 አርሶ አደሮች ንግድ ፍቃድ አውጥተው በቀጥታ ቡናን ወደ ውጪ እንዲልኩ መደረጉን ያስረዱት ዶ/ር አዱኛ የአገሪቱን 60 በመቶ የቡና ምርት ወደ ስፔሻሊቲ ቡና እንዲቀየር ተደርጓልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ከአለም አቀፉ የኒውዮርክ የጨረታ ገበያ ተላቆ በድርድር የሚሸጥበትን መደላድል ለማመቻቸት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ ይህን ለማሳካት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል በ2016 በጀት አመት እንደ አገር ከተመረተው 391,793 ኩንታል የቡና ምርት ውስጥ 57,811 የታጠበ፤ 233,944 ያልታጠበ በድምሩ 290,755 ኩንታል ቡና ለገበያ ማቅረቡ በመድኩ የተመላከተ ሲሆን ይህም 74 ከመቶ የሸፈነ መሆኑ ተገልጿል።
እንደ አገር በ2024/25, 326,000 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱ በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን ይህን አሃዝ በ2029/30 4 ቢሊየን ለማድረስም በትኩረት እንደሚሰራ በመድረኩ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት አመት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ299ሺ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1.43 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቷ የሚታወስ ነው። ተሾመ ሀይሉ
Obn



