በምዕራባዊው እና በምስራቃዊው የኢትዮጵያ ደጋማ ክፍል መሃል የሚገኘው የአፋር ስምጥ ሸለቆ በየጊዜው የተለያየ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስተናግዳል፡፡
ሰሞኑን በፈንታሌ ተራራ አካባቢ በሬክተር ስኬል እስከ 5 የተመዘገበ እና ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ የተሰማ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂዮ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ተማራማሪ እና መምህር አታላይ አየለ (ፕ/ሮ) ተናግረዋል።
በፈንታሌ ተራራ አካባቢ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ለአንድ ወር ያህል መጠኑ ቀንሶ መቆየቱን ተመራማሪው በተለይ ለኢቢሲ ዶት ስትሪም ገልጸዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ከቅልጥ አለት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከባድ አደጋ ያደርሳል ተብሎ እንደማይጠበቅም ነው የተናገሩት።
ሆኖም ግን በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ እስካሁን ከባድ ጉደት ባያስተናግድም ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
በሰሞኑ የመሬት መንቀጥቀጥ በመተሃራ አካባቢ እና በሳቡሬ ከተማ አንዳንድ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች የመሰንጠቅ አደጋ እንዳጋጠማቸው ከየአካባቢው ነዋሪዎች አረጋገጥናል ብለዋል ተመራማሪው ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ እስካሁን ጉዳት ስለ ማድረሱ የተደረገ ሪፖርት አለመኖሩንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ በተለያዩ አካባቢዎች ያደረሰው ጉዳት ወደፊት የሚጣራ ስለመሆኑም አክለዋል።
በኢትዮጵያ የመሬት መንቀጥቀጥ መቼ እና የት እንደሚደርስ ማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን የተናገሩት አታላይ አየለ (ፕ/ሮ)፤ አሁን የመሬት መንቀጥቀጥ እያስተናገደ የሚገኘው አከባቢ በ1973 ዓ.ም እስከ 3 ወራት የዘለቀ የመሬት መንቀጥቀጥ አስተናግዶ እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ ከጀመረ ከሳምንታት እስከ 6 ወራት ሊቆይም እንደሚችል ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ያለው ለወራት ሊቆይ እንደሚችል ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የመሬት መንቀጥቀጡን አስመልክቶ ሀሰተኛ መረጃ ሲሰራጩ እነደነበር ያስታወሱት ተመራማሪው፤ህብረተሰቡ ይህንን በተመለከተ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂዮ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የሚሰጣቸውን ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ እንዲከታለተል አሳስበዋል፡፡
በላሉ ኢታላ – ኢቢሲ


