የዛሬ አራት ዓመት የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት በጀመረበት ሰሞን (እ.ኤ.አ. በ2022) በደቡብ ኦሞ እና በኦጋዴን የሚገኘውን ሰፊ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በመጠቀም፣ መንግሥት መጠነ ሰፊ የፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ (LNG) ማምረቻ ፋብሪካ እንዲገነባ በፌስቡክ ገጼ ላይ ወትውቼ ነበር። በወቅቱ ለቀድሞው ሚኒስትር ታከለ ኡማም ይህንኑ መልዕክት አድርሼ ነበር።
ያን ጊዜ ስናገር፦ “ይህ ኢትዮጵያ ሀብቷን አልምታ፣ የዓለም የኃይል አቅርቦት በተቃወሰበት ወቅት ራሷን በገበያው ውስጥ የምታስቀምጥበት ወሳኝ ወቅት ነው” ብዬ ነበር። ያ ጥሪ በወቅቱ አስፈላጊ ነበር፤ ዛሬ ግን ዕድሉ ታሪካዊና እጅግ አጣዳፊ ሆኗል።
አሁን በአሜሪካ/እስራኤል እና በኢራን መካከል ባለው ጦርነት ምክንያት፦
* የሆርሙዝ ሰርጥ (Strait of Hormuz) በመዘጋቱ፣ የዓለም 20% የሚሆነው የነዳጅ እና ጋዝ አቅርቦት ተቋርጧል።
* የዓለም ትልቁ የፈሳሽ ጋዝ (LNG) ላኪ የሆነችው ኳታር፣ በራስ ላፋን (Ras Laffan) በሚገኘው ግዙፍ ፋብሪካዋ ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት ምክንያት ምርት አቁማለች።
* የሩሲያ የጋዝ ኤክስፖርት በዩክሬን ጦርነት ምክንያት አሁንም በቀጥታ ለአውሮፓ ገበያ መቅረቡ እንደተቋረጠ ነው።
* ከአሜሪካና ኢራን ጦርነት መጀመር በኋላ በአውሮፓ የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ60% በላይ የጨመረ ሲሆን፣ ይህም ከፍተኛ የኃይል ቀውስ አስከትሏል።
ይህ ለኢትዮጵያ ታሪክን የመለወጫ ወርቃማ ዕድል ነው!
በኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ ግዙፍ ክምችት እንዳለ ተረጋግጧል፤ ኢትዮጵያ በካሉብና ሂላላ እስከ 198.2 ኳድራሊዮን ሊትር ወይም 198.2 ኪውቢክ ሜትር የሚደርስ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንዳላት ተረጋግጧል። በዚህም በአመት እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣውን ለአለም ገበያ እያቀረበች ቢያንስ ለሀያ አመት ያክል ያለማቋረጥ መጠቀም እንደምትችል መረጃዎች ያሳያሉ።
በቅርቡ በካሉብ የመጀመርያው ምዕራፍ የሲ.ኤን.ጂ (CNG) ፕሮጀክት ተመርቆ ሥራ መጀመሩ የሚያበረታታ ቢሆንም መጠኑ እጅግ አነስተኛ ስለሆነና የተፈጥሮ ጋዙን አምቆ ወደ ፈሳሽነት የሚቀይር ቴክኖሎጂ ባለመተከሉ በቀላሉ ለኤክስፖርት የሚበቃ አልሆነም። ስለሆነም አሁን ይህን ሀብት ሙሉ በሙሉ ወደ ኢንደስትሪ ደረጃ የተሸጋገረ የፈሳሽ ጋዝ ማምረቻ (Liquefaction plant) ተገንብቶ የዓለምን የኃይል ፍላጎት ክፍተት በመሙላት ሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ግኝቷ እንድጨምር በከፍተኛ ፍጥነት መንቀሳቀስ ያለብን ወቅት መሆኑን መገንዘብ ያሻል።
በዚህ ወሳኝ ወቅት የማዕድን ሚኒስቴርና ሌሎችም የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት አካላት ቀጥሎ ያሉትን እርምጃዎች በአስቸኳይ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፦

* ከአውሮፓ አገራት (በተለይም ከሩሲያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ ጋዝ አማራጭ ለምትፈልገው ጀርመን) ጋር ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር መጀመር።
* የፈሳሽ ጋዝ ማምረቻ (Liquefaction plant) ፋብሪካ ለመገንባትና ምርቱን ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስፈልገውን መሠረተ ልማት ለመገንባት የሚሆን ፈጣን የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ አጋርነት መፈለግ።
ይህንን ዓለም አቀፍ ቀውስ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስብራት ማስተካከያ ለማድረግ፤ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለመጨመር እንዲሁም የኢኮኖሚ ነፃነታችንን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ሀብቱ አላት፣ ዓለም ደግሞ ፍላጎቱ አለው። ይሄን ለማድረግ ከተጠቀምንበት ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው።
ኢትዮጵያ ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ሊያመልጣት አይገባም። ዓለም የኃይል ዋስትና በፈለገችበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት የኢትዮጵያን እድሎች ለማስፋት በድፍረት እርምጃ ወሶዶ ውጤት የሚያመጣ አመራር ከተገኘ ታሪክ ሁሌም ቢሆን ሲያወሳው ይኖራል። ለዚህ ደግሞ በዚህ ወቅት ዘርፉን ለመምራት ኃላፊነት ላይ ላሉ እንደ ወንድሜ ሀብታሙ ተገኝ ያሉ አመራሮች የማይገኝ እድል ነውና የሚቻለውን ሁሉ ለመሞከር እንዲችሉ በታላቅ አክብሮት ማሳሰብ የዚህ ፅሁፍ ዋነኛው ዓላማ መሆኑን እገልፃለሁ።
እንዲሁም ይህንን ጽሁፍ የምታነቡ ወዳጆቼ በሙሉ፣ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት እንዲደርሳቸው ‘ታግ’ (Tag) በማድረግ ወይም ‘ሼር’ በማድረግ ድምፃችንን እንዲናሰማ አደራ እላለሁ! ![]()
![]()



