የኦሞ ወንዝ በመሙላቱ ከቁጥጥር የአካባቢው አርሶ አደሮች ባገኙት አቅጣጫ አካባቢዉን እየለቀቁ መውጣታቸው እየተሰማ ነው። እንግልትና ከፍተኛ ችግር ተከስቷል።
ችግሩ እንደሚከሰት ታውቆ ቅድመ ዝግጅት ቢደረግም የኦሞ ወንዝ መጠን ከተለመደውና ከታሰበው ውጭ መሆኑን ተከትሎ አደጋው ለዞኑ፣ ለመንግስትና ለተለያዩይ ግብረሰናይ ድርጅቶች ሰብአዊ ተግባር አስቸጋሪ ሆኗል።
የወንዙ ሙላት ከባድ መሆኑን በመግለጽ አሁን ላይ አርብቶ አደሩን በአራት ጊዜያዊ መጠለያ እንዳስቀመጡትና ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያሻዉ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማልኮ ገልጸው ” በአሁኑ ወቅት የውሃው መጠን ከተለመደው ውጪ እየጨመረና ሰፊ ቦታ እየያዘ ከመምጣቱ የተነሳ ለኦሞራቴ ከተማ ማህበረሰብ እንደሚያሰጋ ” ተናግረዋል ።
ችግሩ እየባሰ የመጣው የውሃውን አቅጣጫ የማስቀየርና የማፍሰስ ስራዎች በኢንቨስተሮች እርሻ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያስከተለ ነው በሚል በጅምር በመቆሙ መሆኑን የሚያነሱት የአካባቢዉ ነዋሪዎች በበኩላቸው ችግሩ በየአመቱ የሚፈጠር በመሆኑ ኑሯቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገዉ ይገልጻሉ።
በመሆኑም አሁን ላይ ማህበረሰቡ ቤቱ እየተዋጠበት ከብቱ እየሞተበትና የሚቀምሰውም በመጥፋቱ ተስፋ በመቁረጥ አካባቢውን ጥሎ መሸሽ መጀመሩ ተሰምቷል።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከኦሞ ወንዝ ሙላት ጋር ተያይዞ በአከባቢው በተደጋጋሚ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ሲከሰት እንደነበር የገለጹት የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሀቴ በበኩላቸው አምና ከ79 ሺህ በላይ አርብቶ አደሮች በወንዙ ሙላት መጥለቅለቅ ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውን ይናገራሉ።
እነዚህ አርብቶ አደሮች እስከ ዛሬ በጊዜያዊ ማቆያ ስፍራ እንዲቆዩ የተደረገ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ታደለ ለእርሻ ስራ በሚል ወደ ቀድሞ ቀያቸው በተመለሱት ላይ አሁንም ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል ።
አሁን ላይ ወንዙ መደበኛ የፍሰት አቅጣጫውን በመልቀቅ የጉዳት መጠኑን አስፍቶና አርብቶ አደሩን አፈናቅሎ ለማህበራዊ ችግር እየዳረገ ሲሆን በኢፌዴሪ ውሃና ኢነሪጂ ሚኒስቴር አማካኝነት ችግሩን ለመቅረፍ የተጀመረው የመከላከያ ፕሮጀክት መፍትሄ ያመጣል ቢባልም ሊጠናቀቅ አልቻለም።
በዚህ ምክኒያትም አሁን ላይ በ33 ቀበሌዎች የነበሩ መሠረተ ልማቶች ትምህርት ቤቶች ጤና ኬላዎችና መኖሪያ ቤቶች በውሃ ሊከበቡና ነዋሪው ለከፋ ችግር ይጋለጥ ዘንድ ምክኒያት ሆኗል።
ዜናው ከቲክቫህ የተወሰደና መጠነኛ መሻሻል የተደረገበት ነው።


