የትኛውንም ተስፋፊ ኃይል የሚመክት ሠራዊት ተገንብቷል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።
የምስራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “የምስራቁ ጮራ የኢትዮጵያ ወታደር ነን” በሚል መሪ ቃል በጅግጅጋ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፤ ምስራቅ ዕዝ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል እና በመላ ሀገሪቱ የተሰጠውን ግዳጅ በጀግንነት የፈፀመ ዕዝ ነው ብለዋል።
ዕዙ በምስረታው የሶማሊያን ተስፋፊ ኃይል መጠነ ሰፊ መስዋዕትነት ከፍሎ የመከተ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ያስከበረ የሀገር ኩራት የሆነ የሠራዊቱ ክንፍ ነው ብለዋል።
የተስፋፊነት አመለካከት ለጦርነት የሚጋብዝ መርዛማ አስተሳሰብ መሆኑን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፤ ጦርነት የተስፋፊውን ህዝብና ኢኮኖሚ የሚያወድም መሆኑን ከታሪክ መማር ያስፈልጋል ብለዋል።
በምስራቁ የሀገሪቱ ቀጠና የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ እነዚህ ተስፋፊ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ጠንካራ መከላከያ መኖሩን መዘንጋት የለባቸውም ነው ያሉት።
ምስራቅ ዕዝ ሀገሩን ጠብቆ ምስራቁን አፅንቶ ከሰሜን በድል ሲመለስ የቆየ ጀግና ሠራዊት ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፤የዕዙ ሠራዊት አባላትም ይህን ጅግንነታችሁን ጠብቃችሁ ማቆየት ይገባችኋል ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር ሙስጠፌ ሙሀመድ በበኩላቸው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት በመፈፀም የሀገርና የህዝብ ኩራት መሆን የቻለ ታላቅ ሠራዊት ነው ብለዋል።
ለአብነትም የሰሜኑን የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር፣ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ሰርጎ የገባውን የአልሻባብ ኃይል በመደምሰስ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ መቻሉን አንስተዋል።
ሠራዊቱ ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዎችን እየተወጣ የሚገኝ ሠራዊት መሆኑንም ጭምር አክለው ተናግረዋል።
የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሀመድ ተሰማ፤ የምስራቅ ዕዝ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የተጋረጡ የወረራ ስጋት እና ኢትዮጵያን የማተራመስ እኩይ ዓላማ የያዙ አካላትን መሰዋዕት በመክፈል ጭምር ድል ማድረግ ችሏል ብለዋል።
ሠራዊቱ ከሀገር አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ሰላም የከፈለውን መስዋዕትነት ዘንግተው፣ ቀጠናወን የትርምስ ቀጠና በማድረግ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የሚቋምጡ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በዓሉ በመቀጠል ጷጉሜ 1 እና 2 በሐረር ከተማ በድምቀት እንደሚከበር ከወጣው መርሐ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
(ቴዎድሮስ ታደሰ -ኢቢሲ)

