የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ክልል ልዩ ቦታው 15 ሜዳ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው። የወንጀሉ ሰለባ የሆነችው የ17 አመት እድሜ ያላት አዶናይት ይሄይስ የተከሳሽ ሚካኤል ሽመልስ የፍቅረኛው ልጅ ነበረች።
መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ/ም ከቀኑ 6:00 ሰአት ሲሆን ታዳጊ አዶናይት ይሄይስ መኖሪያ ቤቷ እያለች ተከሳሽ ለምን አስገድዶ ደፈረኝ ብለሽ ለፖሊስ ክስ መሰረትሽ በሚል ሰበብ በቢላዋ የተለያየ የሰውነት ክፍሏን 16 ቦታ በመውጋት ምንም እንዳልተፈጠረ ወደ መኖሪያ ቤቱ በመሄድ ልብሱን በመቀየር ሊሰወር ሲሞክር በአካባቢው ማህበረሰብ እና በወንጀል መከላከል ስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ሊያዝ ችሏል።
ፖሊስም በተያዘው ተከሳሽ ላይ ባደረገው ምርመራ ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም ባልታወቀ ጊዜና ሰዓት ታዳጊዋ ነይ ሱቅ ልላክሽ እና ሌሎች ማታለያዎችን እየተጠቀመ በመኖሪያ ቤቱ በተደጋጋሚ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሲፈፅምባት የቆየ መሆኑንና በወቅቱ እድሜዋ በግምት 10 አመቷ እንደነበረ የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡
ግለሰቡ የእናቷ የፍቅር ጓደኛ የነበረ ሲሆን ይህንን አፀያፊ ድርጊት ለአንድ ሰው ብትናገሪ እናት እና አባትሽን እገላለሁ እያለ ሲያስፈራት የቆየ ስለመሆኑ የሚዘረዝረው የምርመራ መዝገቡ በተጨማሪም ሟችን በሞባይል ካሜራ ቪዲዮ ቀርጬሻለሁ በሚዲያ እና በቴሌግራም እለቀዋለሁ እያለ ለአመታት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሲፈፅምባት መቆየቱንና በዚህም ታዳጊዋ ከተከሳሽ በመፀነሷ ፅንሱን እንድታስወርድ ማድረጉን የተከሳሽ የምርመራ መዝገብ ያስረዳል።
ፖሊስ ባከናወነው ተጨማሪ የምርመራ ስራ ተከሳሽ ሚካኤል ሽመልስ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን አምኖ ቦታው ድረስ በመሄድ መርቶ ያሳየ ሲሆን የምርመራ መዝገቡን በማደራጀትና በማጠናቀቅ ለዓቃቤ ህግ በመላክ ክስ ተመስርቶበታል።
የወንጀል መዝገቡን ሲከታተል የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ሚካኤል ሽመልስ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የሞት ቅጣት እንዲቀጣ እና የዘወትር ህዝባዊ መብቶቹ እንዲሻሩ ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡
በማህበራዊ ህይወታችን ህፃናትና ታዳጊዎችን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ግዴታ ቢሆንም የቅርብ ቤተሰብ ወይም አሳዳጊዎች ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ያስታወሰው ፖሊስ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አዎንታዊ የጠበቀ ቁርኝት ሊኖራቸውና ከተለያዩ የወንጀል ሥጋቶችና ድርጊቶች ሊጠብቃቸው እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ዘገባ፦ ኢንስፔክተር እመቤት ሀብታሙ


