ሞሮኮ ከባሕር ርቀው ለሚገኙት ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል በሚገኙ ወደቦቿ የባሕር በር እንዲጠቀሙ ፈቀደች።
እርምጃው እነዚህ ሀገራት በሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሁም፤ የቀጣናውን ንግድን እና ኢኮኖሚያዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚረዳ ተጠቅሷል።
ሞሮኮ ይህን ውጥን ይፋ ያደረገችው እ.ኤ.አ በ2023 ሲሆን፣ ሀገራቱ ሞሮኮ በገነባቻቸው መሰረተ ልማት አማካኝነት በዳህላ ወደብ በኩል ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ለመጠቀም የሚያስችላቸው ነው።
ይህም እነዚህ ሀገራት ከዓለም አቀፍ ገበያዎች ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ እና በአጎራባች የባሕር ዳርቻዎች ላይ ያላቸውን ጥገኛነት እንዲቀንሱ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ የሮይተርስ መረጃ ያመላክታል።
ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር አሁን በሳህል ሀገራት ሕብረት (AES) የፈጠሩ ሲሆን፣ የሀገራቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትላንት ከሞሮኮው ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ ጋር ተገናኝተው በፕሮጀክቱ ዙሪያ ተወያይተዋል።
በሞሮኮዋ መዲና ራባት ከንጉሡ ጋር ተገናኝተው የተወያዩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ለኢኒሼቲቩ ፈጣን አፈጻጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን የሞሮኮ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ናሰር ቡሪታ እንደተናገሩት፥ የተደረገው ውይይት ሀገራቱ አማራጭ የንግድ መስመር የሚያገኙበትን አማራጭ እውን ያደርጋል።
ውጥኑ በምዕራብ አፍሪካ የንግድ መስመሮችን እና ጥምረቶችን በመቀየር ረገድ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ይህም የቀጣናውን ጂኦፖለቲካዊ ገጽታ በመቀየር ለሳህል ሀገሮች ኢኮኖሚያዊ እድገት ሊያስገኝ የሚችል እንደሆነ ዘ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ዘግቧል።EBC

