ሽብርተኝነትንና ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር በሚል ተሻሽሎ በጸደቀው ህግ የተካተተው “በሽፋን/ under cover ” የምርመራ ዘዴ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረግ፣ መረጃን ለማግኘት በጥብቅ ዲሲፕሊን እና በፍርድ ቤት ቁጥጥር ስር የሚከናወን መሆኑን ተመለከተ። አዋጁ ቶርቸርና የሰብአዊ መብትን የሚነካ እንደሆነ በመግለጽ ስጋታቸውን ያቀረቡ ነበሩ።
ህጉን ለቶርቸርና ለመብት ጥሰት በር የሚከፍት እንደሆነ ጠቅሰው በርካቶች ስጋታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው ፍትህ ሚኒስቴርና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በጋራ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ የሰጡት። ስጋት እንዳላቸው ከገለጹት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ለቢቢሲ እንዳሉት “ከግድያ ወንጀል በስተቀር” የሚለው የአንቀጹ ሐረግም ለትርጉም የተጋለጠ መሆኑን አመልክተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው ህግ በሽፋን ሥር (under cover) ምርመራ የሚያከናውን ሰው ከአቅሙ በላይ እና ከፈቃዱ ውጪ ለሚፈጽመው ከግድያ ውጪ የሆነ ወንጀል ክስ እንዳይቀርብበት የሚያደርግ ነው።
ሌላው ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዓለም አቀፍ ወንጀል ሕግ ባለሙያው አቶ ካሳሁን ሞላ ይልማ አቶ ድንጋጌው አንድ በሽፋን ምርመራ የሚያደርግ ግለሰብ “ሕገ ወጥ ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶችን ከመፈጸሙ በፊት በቅድሚያ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው በግልጽ አለማስቀመጡን ጠቅሰው አዋጁን ተችተዋል። ባለሙያው ይህን ሲሉ “በአዲሱ አዋጅ የተካተተው ይህ የምርመራ ዘዴ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረግ፣ መረጃን ለማግኘት በጥብቅ ዲሲፕሊን እና በፍርድ ቤት ቁጥጥር ስር የሚከናወን ነው” ሲሉ ፍትህ ሚኒስቴርና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ማብራሪያ ሲያቀርቡ ማድመታቸውን ወይም ህጉን ሙሉ በሙሉ ማየታቸውን ቢቢሲ አልጠየቀም።
“እንዲህ ዓይነት ጥበቃ ከሌለ (የህግ ማለታቸው ነው )፣ የዳኝነት ወይም የዐቃቤ ሕግ ቁጥጥር ዘዴ የለም” የሚሉት አቶ ካሳሁን፤ “በሌሎች አገራት ያሉ ሕጎች የወንጀል ተጠያቂነት ከመቅረቱ በፊት ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ወይም ከፍትህ አካላት ፈቃድ እንዲኖር ያስገድዳሉ” ሲሉ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ያነሳሉ።
በፍትህ ሚኒስቴር የህግ ጥናትና ማርቀቅ፣ ማረም፣ ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አዲስ ጌትነት በበኩላቸው፤ የልዩ የምርመራ ስርዓት ከመደበኛ የምርመራ ዘዴ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተገደበ ጊዜና ቦታ የሚደረግ መሆኒን አመልክተዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለቱ ባለሙያዎች ይህን ዝርዝር ስለማንበባቸው ጥርጣሬ እንዳላቸው የሚገልጹ፣ ባለሙያዎቹ ማብራሪያውን አድምጠው ቢጠየቁ ሌላ ትንተና እንደሚሰጡ እምነታቸው መሆኑን ሁለቱንም ወገኖች የተከታተሉ ገልጽተዋል።
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የተሻሻለው አዋጅ ሽብርተኝነትንና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ህጎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን የፋይናንስ ደህንነት ኃላፊው አመልክተው፣
ሙሉ መረጃ ሳይያዝበት ሰፊ ቅሬታን ያስተናገደው ህግ፣ ልዩ የምርመራ ዘዴን የሚያከናውን ሰው “የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሠራ” መሆኑን “ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት. . . ወንጀል ቢፈጽም”፤ “ከወንጀል ክስ ነጻ ስለሚሆንበት አግባብ መደንገግ ሥራውን ውጤታማ የሚያደርገው” መሆኑን ኃላፊዎቹ አመልክተዋል።
አዋጁን ” የአተረጓጎም ክፍተቶችን ይፈጥራል። ሌሎች አገራት ‘አስፈላጊነት እና ተመጣጣኝነት’ ያሉ በደንብ የተረጋገጡ የሕግ መስፈርቶችን ይጠቀማሉ፤ ይህም ከክስ ነጻ የመሆኑ መብት በጠባብ መተርጎማቸውን ያረጋግጣሉ” ሲሉ አቶ ካሳሁን ይተቻሉ። አክለውም
አዋጁ አመንጪ የሚባሉ 21 ወንጀሎችን በአባሪነት ያስቀመጠ ብሎም ለትርጉም ተጋላጭ የነበሩ ጉዳዮችን በግልጽ የሚየስቀምጥ መሆኑን፣ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ደንቦች የተካተቱበት፣ ይህም በመሆኑ ተገቢ ምርመራ ለማካሄድ እንደሚጠቅም የፍትህ ሚኒስቴርና የፋይናንስ ደህንነት ኃላፊዎች አመልክተዋል። የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ከነባር አዋጁ 780/2005 በ58 አንቀጾች 14ቱ ላይ ማሻሻያ አድርጓል ብለዋል። መግለጨውን የተከታተለው ኢዜአ የሚከተለውን ጽፏል።
ልዩ የምርመራ ዘዴ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ የሚከናወን መሆኑን የፍትህ ሚንስቴር አስታወቀ
ልዩ የምርመራ ዘዴ ከመደበኛ የምርመራ ስርዓት የተለየና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ በተገደበ ጊዜና ቦታ የሚከናወን መሆኑን የፍትህ ሚንስቴር አስታወቀ።
በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን የአዋጅ ማሻሻያ ተከትሎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚነሳውን ሀሳብ መነሻ በማድረግ ፍትህ ሚኒስቴርና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ተሰጥተዋል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ፤ ከነባር አዋጁ 780/2005 በ58 አንቀጾች 14ቱ ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸው፤ በአዋጁ ማሻሻያ መደረጉ ኢትዮጵያ ለሽብርተኝነት ምቹ ያልሆነች ሀገር እንድትሆን ያስችላል ብለዋል።
በአዋጁ ውስጥ በልዩ ሁኔታ የሚደረግ ምርመራ ስርዓትን እንዲያስፈጽም የተመደበ መርማሪ በግዴታ ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያትና ከፈቃዱ ውጪ በሆነ መልኩ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም የሚለውን ድንጋጌ በተሳሳተ አረዳድ መተርጐሙን ተናግረዋል።
በሽፋን ስር ወይም በልዩ ሁኔታ የሚደረግ ምርመራ ዘዴ ሁሌ የሚፈፀም አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ህግ ላለፉት 12 ዓመታት ይፈፀም የነበረ ቢሆንም ግልጽነት የጎደለውና ብዥታ ያለበት መሆኑን አብራርተዋል።
የሚደረገው ምርመራ ልዩ መሆኑን ተናግረው፤ አዋጁ አንድን ቡድን ለማጥቃት ታስቦ የወጣ አይደለም ብለዋል፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር የህግ ጥናትና ማርቀቅ፣ ማረም፣ ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አዲስ ጌትነት በበኩላቸው፤ የልዩ የምርመራ ስርዓት ከመደበኛ የምርመራ ዘዴ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተገደበ ጊዜና ቦታ የሚደረግ ነው ብለዋል።
የሚፈፀመውም በህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የመሳሪያ ንግድ፣ የዕፅ ማዘዋወርና መጠቀምን ጨምሮ በሌሎች ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ምርመራ ወቅት ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ይህ ማለት የምርመራ ሂደቱ የሚከናወነው ተጠርጣሪው ተይዞ ሳይሆን መርማሪው ከወንጀለኞች ጋር በመመሳሰል በሰርጎ ገብነት የሚያደረገው መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ወቅት መርማሪው በግዴታ ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያትና ከፈቃዱ ውጪ በሆነ መልኩ ለሚወስደው ርምጃ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም ነው ያሉት።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል የቀረበውን የአዋጅ ማሻሻያ 1387/2017 ሆኖ ባሳለፍነው ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም
በአብላጫ ድምጽ ማፅደቁ ይታወሳል።

