“… ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሃላፊነታቸው በአስቸኳይ ሊነሱ ይገባል። ሲል ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ / ሶስተኛው ወያኔ ትግራይ/ ጥያቄ አቀረበ። ታደሰ ወረደ ከዚህ በላይ በስልጣን ከቆዩ የከፋ ቀውስ እንደሚያስከትሉ አመልክቷል። ኪዳን ትግራይ የተሰኘው የፓርቲዎች ጥምረትም በተመሳሳይ አስቸኳይ የሽግግር አስተዳደር እንዲቋቋም ጥያቄ አቀቧል።

ሳልሳይ ወያኔ “ፕሬዝዳንቱ በስልጣን ላይ ከቀጠሉ በአሁኑ ጊዜ በህዝባችን ላይ ከፈጠሩት ችግር የከፋ ቀውስ በቀጣይ እንደሚፈጥሩ እርግጠኛ ስለሆንን ነው። የትግራይ ህዝብ በድምጹ መሪዎቹን እስከሚረጥ አሰቸኳይ ጉባኤ ተጠርቶ አሳታፊ ጊዜያዊ አስተዳደር ሊደራጅና ፕሬዝዳንት ሊመረጥ ይገባል…” ሲል ከዚህ ድምዳሜ የደረሰበትን ምክንያት ዘርዝሯል።
በተመሳሳይ የትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ውጥረት አሳሳቢ መሆኑን የገለፁ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን መግለጫውን የተከታተለው የጀርመን ድምጽ አመልክቷል።
ባይቶናን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የክልሉን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት አዲስ የሽግግር አስተዳደር መቋቋም አለበት ብለዋል። ከትህነግ ክፍፍል በኋላ በአቶ ጌታቸው ረዳ ከሚመራው ኃይል ጎን የተሰለፉ በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኙ የዞኑ አስተዳደሮችን ከስልጣን ማውረዱን የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር በትላንትናው ዕለት ማስታወቁ ይታወሳል። ይህንኑ ተከትሎ እስካሁን ዝርዝር መረጃ ያለውጣበት ጉዳት መድረሱም እየታወቀ ነው።
የትግራይ ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ ታጣቂዎች ማይጨውን፣መሆኒን እና ጨርጨርን በሀይል በመውረር የጊዚያዊ አስተዳደሩን ማፍረሳቸው በተለያዩ መገናኛዎች እየተገለጸ ነው። ተገባሩ ከፈተኛ ተቃውሞ ቢያስነሳም፣ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ነባሩን የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አስተዳደር ከስልጣን በማውረድ ሌሎች መሾማቸውን ነው ያስታወቁት።
እሳቸው ይህን ቢሉም ማይጨው ከተማ የሚገኘው የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አስተዳደር ፅሕፈት ቤት አድማ በታኝ የተባሉ እና ሌሎች ታጣቂዎች ተቆጣጥረውት እንዳለም፣ ከዚያም ባለፈ ወደ አላማጣ ከተማ ማምራታቸው ተመልክቷል። በአላማጣ የትግራይ ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ የታጠቁ ኃይሎችመመለከታቸውን የሚመሰክሩ የአስተዳደሩን ማኽተም አስረክቡ አናስረክብም ግርግር ተፈጥሮ እንደነበርም ተናግረዋል።
የታጠቁት የትግራይ ኃይሎች፣ በአላማጣ ከተማ የሰፈረውን የፌደራል ፖሊስ ኃይል ካምፑን ለቆ እንዲወጣ መጠየቃቸውን፣ ወዲያውም የፌደራል ፖሊስ በካምፑ አካባቢ የተጠናከረ ጥበቃ እንዳለው ሲረዱ፣ ራስን የመከላከል እንቅስቃሴ የማድረግ ዝግጅት መጀመሩን ሲያስተውሉ ፣ የትግራይ ኃይሎች ማፈግፈጋቸውን እነዚሁ እማኞች አመልክተዋል።
በጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት የተላለፈውን ይህን ውሳኔ በርካቶች ተቃውመው ፖለቲካዊ ውጥረት እንዲጨምር የሚያደርግ ሲሉ ገልጸውታል። ይህን ያሉት በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ተቋማት፥ ታጣቂዎችን በማሰማራት ከሚደረግ የአስተዳደር አካላት የማውረድ ተግባር በመቆጠብ በትግራይ ላሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
በአሁኑ ጊዜ ትግራይ ውስጥ ያለው ጊዚያዊ አስተዳደር ‘በህወሓት የሚዘወር’ እና የህወሓትን አጀንዳዎች ብቻ የሚያስፈፅም ያሉት የተቃዋሚው ባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሴፍ በርሃ፥ በትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችም ከዚሁ ከህወሓት አካሄድ የሚመነጩ ብለዋቸዋል።
ባይቶናን ጨምሮ በሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሰረተው ኪዳን ተጋሩ የተሰኘው የተቃዋሚ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ሕብረት ሁሉን አካታች የሆነ እንዲሁም አጀንዳዎቹ የትግራይን ህዝብ ወቅታዊ ጥያቄዎች ያደረገ የሽግግር አስተዳደር በአፋጣኝ ሊቋቋሚ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በተያዘው አካሄድ ሰላምን ማረጋገጥም ይሁን የትግራይ ወቅታዊ ችግሮችን መፍታት አይቻልም ሲሉ የባይቶናው ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሴፍ በርሃ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በትላንትናው ዕለት በትግራይ ደቡባዊ ዞን ስለነበረው ሁኔታ እንዲሁም በክልሉ በአጠቃላይ እየታየ ነው ስላሉት ፖለቲካዊ ውጥረት መግለጫ ያወጡ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት፥ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ከንግግር ይልቅ በኃይል ለመፍታት መሞከር አደገኛ ሁኔታ እያስከተለ ስለመሆኑ አንስተዋል። የዴሞክራሲ እና ማኅበራዊ ፍትህ ድምፅ የተሰኘ በትግራይ የሚንቀሳቀስ ሲቪል ተቋም ስራ አስኪያጅ አቶ መልዐኩ ኃይሉ ለዶቼቬለ እንዳሉት በተደራራቢ ችግር ላይ ያለን ማሕበረሰብ ለሌላ ችግር የሚዳርግ ፖለቲካዊ ሁኔታ መፈጠር የለበትም ሲሉ ገልፀዋል።
መረጃው ከጀርመን ድምጽና ከተለያዩ የታወቁ የመረጃ ምንጮች የተውጣጣ ነርው


