“……የሕግ ባሏን እንደተወች አንዱን ወዳ ብዙ ፈተና ተቀብላለች፡፡ አበበ ይባላል ፤ በድንገተኛ የዓይን ግጭት እንደተዋወቁም ትናገራለች፡፡ እየዋለ እያደረ ነው ልቧን ሰንጥቆ የገባው፤ «የፍቅር ሰው ነው፣ ወንዳወንድ ወደድኩት› ትላለች፡፡ ተከተለኝ፡፡ ቀደመኝ፡፡ የፍቅርን መንገድ መራኝ፤ ልቡን ሰጠኝና ልቤን ሠጠሁት፤ ግልፅ ሆነልኝና ግልፅ ሆንኩለት፤ ገላ ለገላ ሳንደባበቅ በብሩህ ብርሃን ተጋለጥን፤ ምንና ምናችንን ሳንደባበቅ መብራት በማጥፋት ሳይሆን መብራት አብርተን ንፁህ የምለው ገላውን ንፁህ ይለዋል (የምለው) ብዬ የማምንበትን ገላዬን ተገላልጠን፣ ተያይተን ተቃቅፈን፣ የፍቅርን ፅዋ እየተጎነጨን አበባ ከንፈርሽ የሚለኝን ከንፈሬን እኔም በተመሳሳይ የምናገርለት ከንፈሩን አጋጥመን ዘላቂ የሆነ የማይሞት ፍቅርን በዕውን ዓለም እንጂ በሕልም ሳይሆን ተመላልሰን ተጎዳንበት” በማለት ትቀጥላለች::
«በቃል ኪዳን ለመተሳሰር ግን አልታደልንም:: ፍቅራችን ምድሯን ለቀን በአየር ላይ ሊያንሳፍፈን ይታገለናል:: አብሮኝ ውሎም ሆነ አድሮ ሊለየኝ አጥንትና ሥጋዬ በድናቸው ይቀራል፤ ልቤም ሆነ የአእምሮዬ ሞተር እሱን ተከትለው ይሄዳሉ፡፡

ይኽም ቢሆን ጭንቀቱም ሆነ ፍቅሩ የኔ ብቻ አይደለም፣ በእሱም በኩል እንዲሁ፧ እኩል ለእኩል ነበርን:: አያስቀይመኝም፣ አላስቀይመውም፤ በተፋቀሩ ጓደኛሞች ዘንድ ያለው ችግር ያው ቅናት ነው::እኔ እንደምወደው ሌላዋም ትወደው ይሆን? ማለት አለ፡፡ በበኩሉም እንደኔ የምትሆንለት፣ የምትንሰፈሰፍለት ይኖራት ይሆን ማለቱ አይቀርም:: ይኽ እሱንም እኔንም ይሸረሽረናል:: ሳያገኘ ኝ፣ ሳያየኝ ከመሸ አለ ነገር እላለሁ፡፡ እሱም እንደዛው ነው፡፡ እንዳሁኑ ሞባይል የለ፡፡ እንኳን ሞባይል ተራው ስልክ ያላቸው ቤቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው:: እንደው ዝም ብሎ እህህ …. እፎይ ማለት ብቻ ነው ትርፉ፡፡
«ደግሞ ምን ይከተል ይሆን ብሎ የውስጥ ስሜትን ማቃጠል፤ ሲጋራን ማጨስ፣ ማቡነን፤ አብሮ ቡንን ማለት፤ አንጎልን ማምከን ነው» ብላ ነው የምትደመድመው:: የደመደመችውን ታሪክ እንደገና ታስታውሳለች:: ኧረ የእሱ ነገር ምን ሥፍር ቁጥር አለው? ልርሳህ!….. አልረሳም፡ ኧረ ከልቤ ውጣ አልወጣም፡፡ ሰውነት መሟሟት ጀመረ:: የማደርገው ነገር ሁሉ ማንንም ግራ የሚያጋባ ሆነ:: እኔ ያለሁበትን ጭንቀት ዘንግቶ ይሆን እያወቀ፣ አንድ ጊዜ ደብዳቤ ፅፎ በላይ መረሳ ለተባለ በአክተርነቱ በተለይ በአስቂኝ ድራማ ውስጥ ከተስፋዬ ሣህሉ ጋር ይቀርብ ለነበረውና በቅርብ ለማውቀው ጓደኛችን ላከልኝ::
ደብዳቤውም የሚለው:-«አስናቀች የእኔና ያንቺ ነገር አበቃ:: ደህና ሁኚ፡፡ እኔ ሚስት ላገባ ጨርሼ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ አንቺንም ይቅናሽ::» ይላል:: ዑዑታዬን አቀለጥኩት፡፡ ኡኡ ኡኡ ስል በላይ መረሳ የእሳት አደጋ እንደደረሰ ዓይነት ራሱን ለማዳን ጥሎኝ ሮጠ፡፡ ወዴት እንደደረሰ ትዝ አይለኝም፡፡
«ሕሊናዬን ሳትኩ:: ልተኛ፣ ልቀመጥ፣ ገደል ልግባ፣ ሜዳ ላይ ልንከባለል አላስታውስም፡፡ ሆነ ሆነ፤ ከእንቅልፉ እንደነቃ ደካማ ሰው እየተንገዳገድኩ አጠገቤ ከነበሩ ሰዎች በተሠጠኝ እንክብካቤ ደጋግፈው ወደ መኝታዬ መወሰዴ ትዝ ይለኛል::» ትላለች አስናቀች::
የሱ ታሪክ በዋዛ አለቀቃትም:: እንደገናም እየተመላለሰ አብረው በፍቅርጎዳና ሲወጡ ሲወርዱ እንደተሸነፈች ስላወቀ የበላይነቱን ለማረጋገጥ ጥረቱን ያካሂድ ጀመር:: አንድ ቀን ጓደኞቿ ፊት ነገርን በነገር እየጫረ ከእሷ, የከረረ መልስ ሲገጥመው አፍንጫዋን ያጣምማል፡፡ ደም በደም ትሆናለች::
ይህን የተመለከተች ጓደኛ «በሽታ ይምታህና ለምን እንደዚህ ትመታታለህ?» ብላ እሳት ጎርሳ እሳት ለብሳ ትናገራለች:: አስናቀችም በቁጣ ‹‹ደግ አረገ! … እንኳን መታኝ ደግ አረገ» ትላለች፡፡እሱም ድርጊቱ የፀፀተው በመምሰል መሐረቡን አውጥቶ ያቀብላታል፡፡ ደሟም በእሱ መሐረብ እየተጠረገ ፊቷ ንፁህ ይሆናል:: ዱላው እራሷ ላይ እንዳረፈ ሁለቱም ዘንግተው ተያይዘው ወደ እሱ ቤት ጉዞ ይሆናል:: በዚያው ዕለት የፈሰሰው ደሟ በትክክል ሳይደርቅ ወደ እሱ ቤት መሄዷ ለጓደኞቿ አስናቀች በጣም ከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቋ የአደባባይ ሚስጥር ነው የሆነባቸው::
ሌሎች ይወዷት የነበሩ ወዳጆቿ ራቋት:: ለነገሩ እሷ ደስታዋ ነበር፡፡ ውሎ አድሮ ግን ነገር ዓለሙ መልኩን እየለወጠ ሄደ፡፡ አንዳንድ ለእሷ የማይጥም ነገር እያየች ሄደች:: እግሯን አሳጠረች:: ልቧን አጠቆረች:: መሰብሰብ ጀመረች:: መንገዷን ቀየረች:: የእሱ ያለህ ማለት ተወች፡፡ ሕይወቷ ፍቅር ነው ቢባልም እየወደቀ ለሚሄድ ፍቅር አብራ ከመውደቅ ለመዳን የሆነ ግድግዳ ተደግፋ መቆም ግድ ሆነባት::በቃኝ አለች::ከብዙ ትዕግስት በኋላ ወሰነች፡፡ ሲበቃ በቃ ነው አለች::
የሁለቱ ጉዞ በእንደዚህ ሁኔታ እየሄደ እያለና እሷ ከበቃት በኋላ አቶ ፍቅረኛ መልዕክት ያስተላልፍላታል:: «አስኒ እኔ እወድሻለሁ፡፡ እባክሽን ይቅር በይኝ:: ልፈትንሽ ብዬ ነው ገለል ያልኩት፤ እንደ አንቺ የምወደው የለኝምና እንደገና እንደቀድሟችን እንሁን» ይላታል:: አስናቀችም «ይህ አባባል በጣም ዘግይቶ የመጣ ነው፤ ቀደም ብለህ ይህን ብትለኝ ኖሮ አገር የገዛሁ በመሰለኝ ነበር፡፡ አሁን ሞቶ የተቀበረ ፍቅር ከመቃብር አውጥቼ ነፍስ ልዘራበት አልችልም:: የኃዘን ልብሴን በልቤ ውስጥ ስቅያለሁ፤ ደህና ሁን› ብላ እንደገና የፍቅር ብርሃኗን አጨለመች:: ተለያዩ:: እሱም ከእሷ አራርቆት የነበረ እንቅፋት አደናቅፎት፣ ከእሷም ሆነ ይጓዝበት ከነበረው ልዩ መንገድ በሞት ተለየ፡
ይኼውም በተፈለገበት ሕግ የመጣስ ወንጀል ተከሶ መሆኑን ከቅርብ ጓደኞቹ ሰማች፡፡ አስናቀችም ወዳው የነበረው፣ ወዷትም የነበረው ሰው በቁም ተለያይተው በተሰጠው ፍርድ የስቅላት ሞቱን ለማየት ከጓደኛዋ ጋር ሄዳ ተሰቅሎና ተንጠልጥሎ ለመጨረሻ ተሰናብታዋለች፡፡
ታላቋ የኪነጥበብ ሰው አርቲስት አስናቀች ወርቁ ለመውደድ ብዙ ወዳለች፤ በብዙዎችም ተወዳለች፧ እውነተኛ ፍቅሯን በዚህ ሁኔታ አጥታለች፡፡ ምናልባት ለዚህ ያበቃቸው ሁለቱም በፍቅር ላይ የሰሩት በደል ይሆናል:: ማን ያውቃል? ለነገሩማ ፍቅር ብርሃን እንጂ ጨለማ አይደለም::የፍቅርን ብርሃን የሚያጨልመው ሞት ብቻ ነው::
ጌታቸው ደባልቄ-1996፣አስናቀች ወርቁ፣ሻማ ቡክስ

