ኢንተር ፖልን ጨምሮ ከተለያዩ ከዓለም አቀፍ የፀጥታና ደህንነት ተቀማት፣ እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት ጋር ግንኙነትና ትብብር በመፍጠር እየሠራ መሆኑን ያስታወቀው የፊደራል ፖሊስ “በማህበራዊ ሚዲያ ሀገሪቱን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ በሚዲያ ዘመቻ በሚያካሄዱ ሰዎች ላይ የተጠናከረ ኦፕሬሸን ይካሄዳል” ተባለ። በተለይ በውጭ አገር ሆነው “የትርምስ ቅስቀሳ ያራምዳሉ” የሚባሉትን ቡድኖችና ግለሰቦች እንዴት ወደ ሕግ እንደሚወስድ አልተገለጸም።
የፌደራል ፖሊስ በውጭና በሀገር ውስጥ ሆነው በማህበራዊ ሚዲያ ሀገሪቱን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የሚዲያ ዘመቻ በሚያካሄዱት ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የተጠናከረ ኦፕሬሸን እንደሚያካሂድ ያስታወቀው፣ ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር ሙከራ የሚያደርጉ ግለሰቦች እና ቡድኖችን ለሕግ የማቅረብ ሥራን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን በገለጸበት ወቅት ነው።
በኢትዮጵያ ስም በመቀየር፣ የማይወክሉትን ብሄር በማስመሰል፣ በተሳሳተና የተጭበረበረ የማህበራዊ ገጽ አድራሻ አስፈሪ፣ አስደንጋጭና እርስ በርስ የሚያጋድልና አገር የሚያተራምሱ መረጃዎችን ማሰራጨት የተለመደ ነው። ባለሙያውች በተደጋጋሚ ባደረጉት ጥናት ይህንኑ አረጋግጠዋል።
በጎረቤት አገራት፣ በአውሮፓ፣ ካናዳና አሜሪካ የሚኖሩ የሚታወቁና የማይታወቁ ግለሰቦችና ኃይሎች በተናበበ መልኩ የጥላቻ፣ የሽብር፣ የሃሰትና አገሪቱን ወደ ትርምስ የሚወስድ ከተለመደው የፖለቲካ ፉክክር አጋብብ ውጭ የሆነ መረጃ ማሰራጨት የተለመደ ነው። በተለይም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሌት ተቀን የሚሰራው ሻዕቢያና ስፖንሰር አድራጊዎቹ አገራት ያሰምሯቸው እንደሆኑ የሚታወቁ ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ የሚያሰራጩት መረጃ አገራቸውን ለሚወዱ እጅግ አስደንጋጭ ነው።
ፖሊስ በእንዲህ መሰሉ የትርምስና የሽብር ተግባር ላይ የተሰማሩትን “ሕግና ሥርዓትን ተከትለን የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን” በማለት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበጀት ዓመቱ መዝጊያ ላይ ተናግረው ነበር። ከሐምሌ እስከ ምስከረም ኢትዮጵያ ታላላቅ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤዎችን ማካሄዷን አስመልክቶ ፖሊስ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ሲያስታውቅ ነው በውጭ ያሉትን አካላትና ቡድኖች ወደ ህግ ለማቅረብ ኦፕሬሽን መጀመሩን ያስታወቀው።
የደረሱበት ይፋ አለሆነም እንጂ ጀርመንን ጨምሮ ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት ጋር ይህንኑ አስመልክቶ ንግግር መጀመሩን፣ ጽንፈኛ የተባሉ አካላትን በገንዘብ የሚደግፉትን የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሆነ፣ በተለይም በአሜሪካ በሕግ አግባብ የሚታዩ ጉዳዮችን በመለየት ከጸጥታ ተቋማት ጋር ግንኙነት ሲደረግ እንደነበር መገለጹ አይዘነጋም። አሁን የተነገረው ዘመቻ የዚሁ አካል ይሁን አዲስ የተባለ ነገር የለም።
“በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያ እንዲሁም በሁሉም መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ አሰሳና ፍተሻ እንደሚካሄድ አስታውቋል። የፌድራል ፖሊስ ዋነኛ ትኩረቴ “በፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ” ነው ሲል ሰላማዊ ዜጎች የተለመደ ተግባራቸውን ያለአንዳች ስጋት፣ በፍጹም ነጻነት እንዲያካሂዱ ብሏል።
ፌደራል ፖሊስ ከሐምሌ እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ስብሰባዎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በተዘጋጀ የፀጥታ ዕቅድ ላይ በተደረገ ውይይት በርካታ መረጃዎች ተሰጥተዋል።
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩትም ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሪፐብሊካን ጋርድ፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተውጣጡ ስትራቴጂክና ከፍተኛ አመራሮች መሆናቸውን ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ውይይቱን በመሩበት ወቅት በቀጣይ ሀገራችን ከሐምሌ እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም የምታስተናግዳቸውን ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ሁነቶች በሰላም እንዲከናወኑ ከእንግዳ አቀባበል ጀምሮ ስምሪቱን በተደራጀ መልኩ መምራትና ማስተባበር እንደሚያስፈልግ መናገራቸውንም መረጃው አካቷል።
ኮሚሽነር ጀነራል የወንጀል መከላከል ኃይላችን በከፍተኛ ደረጃ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም፣ ዘመናዊ ትጥቅ የታጠቀ፣ የሀገርን ሰላምና ደህንነት በማስከበር ለመንግስትና ለህዝብም አለኝታ የሆነ የወንጀል መከላከል ተቋም መገንባቱና በወንጀል ምርመራ ረገድም የፎረንሲክ ምርመራን ዲጂታል በማድረግና በዘመናዊ የምርመራ ሥርዓት የሚመራ፣ የሰብዓዊ መብትን ያከበረ፣ ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር የተላበሰ አመራርና ሙያተኛ በማፍራት፣ ከሌብነት የፀዳ የምርመራ ሥራ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም።


