የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሀገራዊ የመጅሊስ ምርጫ ምዝገባ ለማጠናቀቅ እና የምርጫ ኩነቶች ዝግጅትን በተመለከተ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ላለፉት አምስት ወራት የቅድመ ዝግጅት ሲደረግ እንደነበረና በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ በኡለማዎች፣ በምሁራን፣ በወጣቶች፣ በሴቶች እና በሥራ ማህበረሰቦች፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምዝገባ ሲካሄድ እንደነበረ የምርጫ አስፈጻሚ ቦርዱ ሰብሳቢ ዶ/ር አብዱልአዚዝ ኢብራሂም ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ለምርጫው ይመዘገባል ተብሎ የተጠበቀው በተለይም ዕድሜው ከ18 በላይ የሆነ እንዲሁም በዕድሜ በመለየት እና ወቅቱ ክረምት ከመሆን እና ማህበረሰቡ በምርጫ ዙሪያ ያለውን ሁኔታ መረዳት እጥረትን ጨምሮ ከ8 እስከ 10 ሚሊዮን ሕዝብ እንደነበረ አንስተዋል።
ነገር ግን በ2017 በሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ በአጠቃላይ 13 ሚሊዮን 151 ሺሕ 889 ሕዝብ ተመዝግቦ፤ ለምርጫ ራሱን ዝግጁ ማድረጉን ሰብሳቢው ለአሐዱ ተናግረዋል።በዚህም መሠረት ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች ላይ ምርጫው እንደሚካሄድ ገልጸው፤ የትግራይ ክልል ምርጫ ባለው የሰላም አለመረጋጋት ምክንያት በክልሉና በክልሉ የምርጫ ቦርድ ጥያቄ መሠረት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን አስታውቀዋል።
ከ60 ሺሕ በላይ መስጅዶችን ለምዝገባ ሲጠቀሙባቸው እንደነበረ ገልጸው፤ ከእነዚህ ውስጥ 49 ሺሕ 92 መስጂዶች ምርጫ እንደሚከናወንባቸው ገልጸዋል።ምርጫው በግልጸኝነት፣ በፍትሐዊነት፣ በአካታችነትና በአሳታፊነት ለማሳካት ስፊ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ቴክኖሎጂን ጭምር በመጠቀም ሲሰራበት ስለመቆየቱ ተናግረዋል።
ምርጫውን ለማስፈጸም ከተቋቋመው የምርጫ አስፈጻሚ አካላት እንደየእርከናቸው በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ 155 ሺሕ 101 ያህል ሰዎች በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ደረጃ ስልጠና መውሰዳቸውንም አክለዋል።”ፍትሐዊነትን ከማስፈን አንፃርም በመቶዎች ከሚቆጠሩ አቤቱታ አቅራቢዎች ጋር ውይይቶች ተደርገው መቀራረብና መረዳዳት ተችሏል” ብለዋል።
በመሆኑም “ምርጫው ነገ ነሐሴ 9 ቀን 2017 ከጁምአ ሰላት በኋላ በመላ ሀገሪቱ ተጀምሮ እንደየ አካባቢው ሁኔታ እስከ እሁድ ነሐሴ 11 ቀን 2017 ድረስ የመስጂድ ደረጃ ምርጫ ይካሄዳል” ብለዋል።
ከዚያ በመቀጠልም የወረዳ ምክር ቤት፣ የዞን ምክር ቤት፣ የየክልል ምክር ቤቶች እና የፌደራል መጅሊስ ምክር ቤት ከነሐሴ 11 2017 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ባሉት ጊዜያት ውስጥ እንደየ ክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ተካሄዶ፤ ነሐሴ 30 ቀን 2017 እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።
መላው ሙስሊም ማህበረሰብ ቀደም ሲል በምዝገባ ያሳየውን ፍቃደኝነት እና ተነሳሽነት አሁንም የምርጫ ግብ የሆነውን መሪዎቹን መምረጥ፣ ሁሉም በነቂስ ወጥቶ እንደየ ማህበረሰብ ክፍሉ ዑለማዕ፣ ምሁሩ፣ ወጣቱ፣ ሴቱ እና የሥራ ማህበረሰብ በየ መስጂዱ ወጥቶ መሪዎቹን እንዲመርጥ የምርጫ አስፈጻሚ ቦርዱ ሰብሳቢ ዶ/ር አብዱልአዚዝ ኢብራሂም ጥሪ አስተላልፈዋል።


