በሕግ የታገደውን የቀድሞውን ትህነግ ፅህፈት ቤት ከትግራይ ውጭ ሰነአፌ መደረጉ በተሰማ ማግስት ሌላ የልዩነት ዜና ተሰማ። በደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ያሰማራውን ጦር የታገዱትን መሪውን ወደ ኃላፊነታቸው መለሰ።
በሳምቱ መጨረሻ የትህነግ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ኤርትራ በማቅናት “ጥምዶ” የሚሉትን ቅንጅት ለማጠናከር ዕቅድ መያዛቸው ይፋ በሆነ ቅጸበት በድንበር ከተማዋ አዲግራት ኤርትራ ድንበር የከተመው የትህነግ ጦር ማፈንገጡን ይፋ አድርጓል።
ይህ ዜና ከተሰማ በሁዋላ ትህነግ ወታደራዊ አመራሮቹን ድንገተኛ ስብሰባ መጥራቱ ተመልክቷል። ስብሰባው ከመጠራቱ ውጪ ሌላ የተባለ ነገር የለም። ባለፈው ሰሞን በኃይል አስተዳደር ለማፍረስ የተደረገውን ኦፕሬሽን የመራው የደቡቡ ወታደራዊ መኮንኖችም በተመሳሳይ ስብሰባ መቅመጣቸው እየተሰማ ነው።
እነ ዶክተር ደብረጺዮን ከሚመሩት የትህነግ ጦር ባለመስማማት ተለይተው ራሳቸውን የትግራይ ሰላም ኃይሎች በማለት የሰየሙትና በአፋር ሓራ መሬት የሰፈሩት ታጣቂዎች መሪ ” ከእነ ደብረጽዮን ጋር ካለው ጦር አመራሮች ጋር ግንኙነት አለን” ማለታቸው አይዘነጋም።
የትህነግና እና የሻዕብያ ግንኙነት ስር እየሰደደ መሆኑን ያመለከቱት የባይቶና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ክብሮም በርሀ ሰሞኑን የትህነግ ፅሕፈት ቤቱን ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ዉጭ በማድረግ በኤርትራ ሰንዓፍ ላይ መክፈቱን ማጋለጣቸው አይዘነጋም።
የጥቂት አመራሮችን ጥቅም ለማረጋገጥ ሲባል ትግራይን ለማውደም እየተሞከረ እንደሆነ አቶ ክብሮም ጨምሮ ገልፆል። “ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ፈጥረናል” በሚል የትህነግ አመራሮች ህዝብን ያለፍላጎቱ ወደ ኤርትራ ድንበሮች እየወሰዱት እንደሆነም አቶ ክብሮም አስታወቀ ነበር።
ይህ ሁሉ ይፋ ከሆነ በሁዋላ ነው በደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ትህነግ የኢትዮ-ኤርትራን ድንበር ላይ ያሰማራውን ጦር የሚመሩት ጀነራሎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ማመጻቸውን ያስታወቁት።
በእነ ደብረጽዮን ላይ ያመጸው ጦር የድንበር ከተማዋን አዲግራትን መቀመጫ አድርጎ በኢትዮ-ኤርትራን ድንበር ጫፍ የሚንቀሳቀሰው አርሚ 15 የሚባለው ነው፡፡
በድንበር አካባቢዎች ላይ የተሰማራው የትህነግ አርሚ 15 ከፍተኛ አመራር ጀነራሎች ማመጻቸውን በመግለጫ አረጋግጠዋል፡፡ አሃዱ እንዳለው ጀነራሎቹ ያመጹት በድረብጽዮን የሚመራው የትህነግ ቡድን ከኤርትራ መንግሥት ጋር ጀምሮታል ያሉትን ግንኙነት በመቃም መሆኑ በአቋም መግለጫ ግልጽ አድርገዋል።
በጀነራል ጉዑሽ ገብረ (ፈንቅል) አዛዥነት የሚመራው አርሚ 15 አመራሮች በትግራይ ውስጣዊና ውጫዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከመከሩ በኋላ ቅርብ ወራ አለ ብለዋል፡፡ አመራሮቹ ይፋ ባደረጉት የአቋም መግለጫ በትህነግ የጦር አመራሮች መካከል ከፍተኛ መከፋፈል መፈጠሩ አሳብቀዋል፡፡
የትህነግ ሰራዊት ማዕካዊ አዛዦች በኢት-ኤርትራ ድንበር ላይ የሰፈረውን ጦር የሚመሩትን ጀነራል ጉዑሽን ለማንሳት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ ጀነራሉ ሳይቀደሙ በዙሪያቸው ያሉ አመራሮችን አስተባብረው በህወሓት ላይ አምጸው መግለጫ አውጥተዋል፡፡
የጦር አመራሮቹ ከኤርትራ ጋር ተጀምሯል ያሉት ግንኙነት ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም የማያስገኝ ሕገ ወጥ ጥምረት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ድንበሩን የተቆጣጠሩት የጦር አመራሮች የህወሓት እና ሻዕቢያ ግንኙነት ሊያስተጓጉሉ እንደሚችሉ ከወዲሁ እየተገለጸ ነው።
በገሃድ ማመጻቸውን የገለጹት የትህነግና ኤርትራን ግንኙነት ጓዳ ጎድጓዳ የሚያውቁት ጀነራሎች መሆናቸው ደግሞ፣ በመቀሌ እና አስመራ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል።
የአመራሮቹ አቋም ከደብረጽዮን ቡድን ጋር አንገት ለአንገት ለመተናነቅ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን የጌታቸው ረዳን ቡድን አቋም የተጋራ ነው፡፡ የጌታቸው ረዳ ቡድን ትህነግ ከሻዕቢያ ጋር የጀመረውን ግንኙነት አጥብቆ እንደሚኮንን ይታወቃል።
የአርሚ 15 አመራሮች በአቋም መግለጫቸው ያነሱት ሌላው ጉዳት የትግራይ ጊዜያዊ አስዳደር ፕሬዝዳንት ጀነራል ታደሰን አስተዳደር የሚኮንን ነው፡፡ ጀነራሉ ከህወሓ ጎን ተለጥፈው የትግራይን አንድነት እየሸረሸሩ መሆኑን አመራሮቹ የገለጹ ሲሆን፣ እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ አጥበቀው ኮንነዋል፡፡
በተለይም ጀነራል ታደሰ የደብጽዮንን ቡድን ፍላጎት ለማሳከት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ትግራይ አካባቢዎች አስተዳደር የመቀየር እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል፡፡ ጀነራል ታደሰ የጀመሩትን አስተዳደር የቀመየር እንቅስቃሴ አጥብቀው የተቃወሙት የጦር አመራሮች፣ በኃይል ለውጥ ማደረጉ በአሰቸኳይ ቆሞ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል፡፡
ጀነራል ታደሰ የሚመሩት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለህወሓት ውገንና ከማሳየት ይልቅ የትግራይን የግዛት አንድነት ለማስመለስ ከፌደራል መንግሥት ጋር እንዲሰራ ጠይቀዋል። የጦር አመራሮቹ አክለውም “የጦርነት እንቅስቃሴ እና የጦርነት ወሬ አቁመን፣ ችግራችንን በሰላማዊ መንገድ እንፍታ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የትግራይ ኃይሎች ከማንኛው የፖለቲካ ኃይል ውግንና ነጻ ሆነው የተፈጠረውን መከፋፈል ለማስቆም በጋራ እንዲቆሙም ጠይቀዋል፡፡ “የትግራይ ሰራዊት” ተብሎ የሚጠራው ኃይል የትግራይ ሕዝብ ጠባቂ እንጂ የማንም ፖለቲካ ኃይል ተለጣፊ አይደለም ሲሉም የጦር አመራሮቹ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
ዜናው አሃዱንና ሌሎች ምንጮችን ያካተተ ነው

