በዙፋን ኡርጋ ደራሲነት የተጻፈውን ሌንጮ ለታ ትግል ሕይወቱ መጽሐፍን አነበብኩት። መጽሐፉ በ471 ገጾች እና በሦስት ክፍሎች ተቀንብቧል። የመጀመሪያው ክፍል ከልጅነት እስከ ትግል ዋዜማ የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን፤ ሁለኛው ክፍል ከዩኒቨርሲቲ እስከ ቤተ መንግሥት፤ ሦስተኛው ክፍል ደግሞ ከኦሮሞ ነጻነት ወደ ቀጣናዊ ትብብር በሚል ርዕስና ንዑስ ርዕሶች ስር ሰፊ ምልከታ እና ትንታኔ ተሰጥቶባቸዋል። ከገጽ 359 ጀምሮ የባለታሪኩ ቀደምት ሥራዎች በወፍ በረር ተቃኝተዋል። ይህም አንባቢው በቀደሙት ክፍሎች የተነሱ ጉዳዮችን የበለጠ እንዲረዳ የታሰበ ነው።
እንደኔ አባሪው ለብቻ ከሚሆን እንዲሁም አንባቢን ከማሰልቸት አንዳንድ ሀሳቦችን አስቀድሞ የተነሱት ላይ መጨመሩ ለመጽሐፉ ፍሰትና ያለፈው suspense እንዳይቀዛቀዝ ይጠቅም ነበር እላለሁ። ቢሆንም ፍላጎቱ ያለው እና መጽሐፎቹን ያላነበበ ሰው ጉጉት እንዲያድርበት ስለሚያደርግ ለክፉ አይሰጥም።
የሆነው ሆኖ አስደናቂው የኦቦ ሌንጮ ታሪክ ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ፣ የት/ቤት ቆይታቸውን፣ የፍቅር እና የቤተሰብ ሕይወታቸውን ጨምሮ አብዛኛውን እድሜቸውን የገበሩለትን የኦሮሞ ሕዝብ የመብት ተጋድሎ በቀልድ እያዋዛ ያስኮመኩመናል። እኔም በሕይወት ገጠመኞቻቸው ፈነግ እያልኩ፣ በፍቅር ሕይወታቸው በተለይ ከኩዌ ጋር የተጋቡበትን ሁኔታ ሲጠቅሱ በዛ ዘመን እንዲያ ማፈንገጣቸው እያስገረመኝ፣ ኤርትራዊ ባለሥልጣን ያገባት የድሮ ፍቅረኛቸው እና ግጥምጥሞሹ፣ ከልጆቻቸው ጋር ሲገናኙ የነበረውን ኹነት ከእንባዬ ጋር እየታገልኩ እንዳነባቸው ተገድጃለሁ። ሌላም ሌላም…
በእውነቱ ምነኛ አስደናቂ እና በወጉ የተኖረ ሕይወት ነው!
በተለየ ሁኔታ ግን ሚሲዮናዊያን የነጋሶ ጊዳዳን “ዳንዲ” እያነበብኩ ያለሁ እስኪመስለኝ ድረስ የሁለቱ ታሪክ መመሳሰልና ለትምህርት ሕይወታቸው መቃናት ያደረጉት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
የመጽሐፉ ጥንካሬ
የመጽሐፉ ጥንካሬ ከቃላት አጠቃቀሙ እና አተራኩ ይጀምራል። ሀሳቦቹ ሳይንዛዙና ሳይዛነፉ ተሰካክተዋል። አርትኦቱም ሸጋ ነው። አልፎ አልፎ ከሚታዩ የሆሄያት ግድፈት ውጪ ማለፊያ ባለሞያ እንደተጨነቀበት ያሳብቃል። በምዕራፎቹ መሀል ያለው የሀሳብ ፍሰትም እንዲሁ ያልተዛነፈ ነው። በአጠቃላይ በውብ ቃላትና አገላለዖች ተከሽኖ ለንባብ በሚጋብዝ መልኩ ተጽፉል። ለዚህም ጸሐፊዋ እና በሥራው የተሳተፉ ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባል።
ይህን ካልኩ ዘንዳ፣ እንደ አንድ አንባቢ የታዘብኩትን እና ለወደፊት ቢሻሻሉ የምላቸውን “ህፀፆች” ነቅሼ ለማቅረብ እሞክራለሁ። ይህን ሳደርግ እንደ ባለሙያ ወይም ሀያሲ ሳይሆን የተሰማኝን ለመግለጽ ያህል ብቻ እንደሆነ ልብ እንዲባልልኝ እፈልጋለሁ።
የባሮ ቱምሳን ገዳይ ፍለጋ….
ይህን ግለ-ታሪክ አጓጊና የውዝግብ ማዕከል ካደረጉ ነገሮች አንዱ የባሮ ቱምሳ ግድያ ሁኔታ ነው። የጉዳዩ ስስነት ብቻ ሳይሆን በኦሮሞ የፖለቲካ ጎራ ውስጥ ያስከተለው ውዝግብ እና ጥፋት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እኔም በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቼ ጸሐፊዋ እዚህ ጋር ምን ለማስተላለፍ ፈልጋ ነው እያልኩ በመስመሮች መሀል ሳነብ ነበር። የገባኝ ነገር ቢኖር ጸሐፊዋ በማወቅም ይሁን በሌላ የባሮ ጉዳይ ለተለያየ ትርጓሜና አረዳድ ክፍት እንዲሆን በማድረግ ትልቅ ስህተት ሰርታለች።
ነገሩ ወዲህ ነው….
ገጽ 150 ላይ ባሮ ሌንጮን እንዲህ ይለዋል። “ሌንጮ፥ እዚኽ እኛ ቦታ የለንም”።
ይህን ጉዳይ መጀመሪያ ያነበበ ሰው በቀደሙትና በቀጣይ ክፍሎች ሌንጮ እራሱ እታማበታለሁ ከሚለው አፍቃሬ ወለጋነት እና አካባቢያዊነት ጋር ቢያያይዘው አይፈረድበትም። ነገሩን ገልብጠን ስናየው ግን ባሮ ለማስተላለፍ የፈለገው እና እኔም የተረዳሁት፣ ሸገር ላይ የተመረጠው አመራር እነ በdho ያሉበት ቦታ (ሐረርጌ ላይ) ቦታ እንደሌለው ለማመላከት ይመስለኛል። ይህ ግልጽ መደረግ ነበረበት።
ሌላው ቅር ያለኝ ነገር ቢኖር፣ ሌንጮ ለባሮ ባዘኑበት ልክ ለበዶ አለማዘናቸው አስገርሞኛል። ምስኪኑ በዶ የአእምሮ ታማሚ ተደርጎ ከመሳል ባለፈ ስለሱ ስብዕና አንዲት መስመር እንኳን አለመጻፉ ያሳዝናል። ኦቦ ሌንጮ ድፍን ያለ መልስ ከሚሰጡ ሌላው ቢቀር ወደመገዳደል ያመራው ልዩነት ምን እንደሆነ ቢነግሩን በእድሜያቸው ማምሻ ፅድቅ ይሆናቸው ነበር።
በተረፈ ሌንጮ ብዙ ሰዎችን በስም አንስተው ይጥላሉ። አንዲያውም የቀራቸው የለም ማለት ይቻላል። በተለየ ግን ጃራ አባገዳ እና ዳውድ ኢብሳ ላይ የበረቱበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም። ጃራን አንዳንዴ ከርዕሱ ጋር በማይገናኝ ጉዳይ ሸንቆጥ ያደርጉታል። ዳውድን በአመራር ብቃት ማነስ እና የኦነግን ጦር ወደ ካምፕ በማስገባት ሲከሱት ይታያል።
ከሀሉም በላይ ሌንጮ በተናጠል የሚወስዷቸው እርምጃዎችና በዛ ሰበብ ከአመራርነት እንድነሳ ተደረኩ ሲሉ በበቂ አመክንዮ ሲከላከሉ አይስተዋሉም። በጋራ የመወሰን ችግር ብቻ ሳይሆን ለኦነግ መዳከም ምክንያት የሆኑ እና የእርሳቸው ድርሻ የሆኑ አንኳር ጉዳዮችን ጠቅሰው ይቅርታ መጠየቅ ይችሉ ነበር።
የድርጅቱ ውድቀት ተደርገው የተጠቀሱት አንዳንድ ጉዳዮች የሌንጮ የፖለቲካዊ ብልጠት እጦት፣ ግትርነት፣ ሴረኝነት፣ የውስጥ መገፋፋት እና አጉል ፉክክር ተደርገው ሊገለፁ የሚችሉ መሆናቸውን አንባቢው በቀላሉ መረዳት ይችላል። ለምሳሌ የሰነአፌው ስብሰባ፣ ኢብሳን ለማስፈታት አዲሳባ ድረስ መምጣታቸውና ኋላም ወደ ሀገር ቤት በድብቅ መመለሳቸው፣ ኸርማን ኮኸን በተደጋጋሚ ለሰጠው ማስጠንቀቂያ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው፣ ለሕወሓት የነበራቸው ስስ ልብ… ሲደማመር ሌንጮ ጓዶቻቸው መጽሐፉ ውስጥ እንዳሏቸው እውነትም ፖለቲካ አያውቁም ወይ ያስብላል። በተረፈ ያሳለፉት ውጣ ውረድ፣ ኦነግ የተጓዘው ረዥም መንገድ እና ሌንጮና ጓዶቻቸው የከፈሉት መስዋእትነት ከዚህ በላይ ሊነገር እና ሊጻፍበት እንደሚገባ የመጽሐፉ እያንዳንዱ ገፆች ምስክር ናቸው።
አበቃሁ!


