ቪኦኤ ዜና – አዲስ አበባ ባለፈው ሳምንት የሱዳንን የተበታተነ የፖለቲካ መልክዓ ምድር በአንድ ጠረጴዛ ለማሰባሰብ ያለመ መድረክ አስተናግዳለች። ይህ መድረክ በ5ቱ አደራዳሪ አካላት/ Quintet (አፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድ፣ አውሮፓ ህብረት፣ ተመድ፤ አረብ ሊግ) አስተባባሪነት የተዘጋጀ ነው።
የሱዳን-ለሱዳን ብሔራዊ ውይይት መድረክ ለማካሄድ ታስቦ የተዘጋጀው ይኸው የምክክር መድረክ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ረጅም ርቀት እንደሚቀር ባሳየ መልኩ ተጠናቋል።
መድረኩ ከጅምሩ በተቃውሞ የታጀበ ነበር። የዲሞክራቲክ ብሎክን (ከጄኔራል አብዱልፋታህ ቡርሃን እና SAF ጎን የቆመ) ጨምሮ፣ ውይይቱን ከጅምሩ ቃውመዋል። መነሻቸውም አምስቱ አወያይ አካላት የውይይት አጀንዳውን በራሳቸው ወስነው ማቅረባቸው ሲሆን አጀንዳውንም ውድቅ አድርገዋል።
በተጨማሪም የዲሞክራቲክ ብሎክ አባላት የሱዳን ፋውንዲንግ አሊያንስ/ታሲስ (በጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው RSF ደጋፊ ጥምረት) አባላት በውይይቱ መጋበዛቸውን ተከትሎ በአንድ ጠረጴዛ ቁጭ ብሎ ለመምከር ሳይፈቅዱ ቀርተዋል።
የውዝግቡ ዋነኛ መነሻ የሆነው “የሱዳን ፋውንዲንግ አሊያንስ” (ታሲስ) በRSF ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የራሱን ትይዩ አስተዳደር እየገነባ እንደሚገኝ ይገልጻል።
በዚህም በኒያላ መቀመጫውን በማድረግ፤ የሀገሪቱን “50 በመቶ በላይ በእኛ ሥር ነው” ሲል፥ በእርሱ ቁጥጥር ስር ባሉ አከባቢዎች የሲቪል መንግስት በማዋቀር ላይ እንደሚገኝ በአዲስ አበባ በነበረው መግለጫ ገልጿል።
በአዲስ አበባ የተካሄደው ይህ የውይይት መድረክ ከጅምሩ ሁሉን በአንድ ለማነጋገር ታቅዶ የተካሄደ ቢሆንም፤ በተለያዩ መግለጫዎችና ለሁለት በተከፈለ ውይይት ተጠናቋል።
በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል በተካሄደው ምክክር የሲቪል ዲሞክራቲክ አሊያንስ ኦፍ ሪቮሉሽነሪ ፎርሰስ አሊያንሰሰ /Somoud እና ከፊል የዲሞክራቲክ ብሎክ አባላት በቀጣይ ሂደቶች ላይ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በዚህም ሁለቱ አካላት 40 አባላት ያሉት የቅድመ ዝግጅት ኮሚቴ ማቋቋም፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትና የፖለቲካ ንግግሮችን የሚያካትት እንዲሁም የቀድሞውን የኢስላሚክ ንቅናቄና የናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ አባላትን ከማንኛውም የሽግግር ሂደት ማግለል የተሰኙ ስምምነቶችን በማድረስ ለቀጣይ ሐምሌ ቀጠሮ ሰጥተዋል።
በሌላ ወገን የታስ ቡድን ከዚህ ምክክር ለጊዜው ውጪ መሆኑን ሁለቱ ቡድኖች መስማማታቸውን ተከትሎ በስካይ ላይት ሆቴል በሰጠው መግለጫ ገልጾ ነበር። ቀጥሎም ከ5ቱ አደራዳሪ አካላት/ Quintet ጋር ለብቻ በስካይ ላይት ሆቴል የተወያየ ሲሆን ራዕዩንም ለቡድኑ አቅርቧል።
የጥምረቱ ቃል አቀባይ የሚካሄደው ውይይት ጥምረቱን የማያካትት ከሆነ “የህዝብ ግንኙነት ፕሮጀክት ብቻ ሆኖ ይቀራል” ሲሉ በመሬት ላይ ሊተገበር የሚችል ውጤት እንደማያመጣ ገልጸዋል።
አክለውም ጥምረቱ፥ “ከሱዳን ጦር ሰራዊት እንዲሁም በፖርት ሱዳን ካለው ዲፋክቶ አስተዳደር ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ግንኙነት የለውም” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እየተካሄደ ያለው፣ ሱዳን ለአራተኛ ዓመቷ በገባቸው የውስጥ ጦርነት እየፈራረሰች ባለችበት ወቅት ነው።
ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ከ400,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል። ወደ 34 ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናውያን (ከህዝቡ 65 በመቶ) አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ ይፈልጋሉ።
በ2026 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ብቻ 245 ህጻናት በድሮን ጥቃት ተገድለዋል ወይም ተጎድተዋል።
አምስቱ አደራዳሪ አካላት (Quintet) በሐምሌ ወር ተጨማሪ የምክክር ዙሮችን ለማድረግ አቅደዋል። ሆኖም፣ አንድ መድረክ ላይ መቀመጥ የተሳናቸው ወገኖች፣ ልዩነታቸውን ካላጠበቡ ሱዳን ወደ ሰላም የምታመራበት መንገድ አሁንም ጭላንጭል ሆኖ ይቀጥላል።
በአዲስ አበባ የተካሄዱት የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች የምክክር መድረክ ምንም እንኳን የታሰበውን ያክል ባይሄድም አሜሪካን ጨምሮ በ7 ሀገራት እውቅና ተሰጥቶታል።
ሀገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉን ያሳተፈ የሱዳን ብሔራዊ ምክክር መድረክ መዘጋጀት እንዳለበት ገልጸው ይህም በ6 ወር ውስጥ መከናወን እንዳለበት ሀሳብ አቅርበዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ይህንን ዘገባ ሲያዘጋጅ ቡድኖቹና አደራዳሪዎቹ የሰጡትን መግለጫዎች የተከታተለ ሲሆን የሱዳን ትሪቢዩን፣ ዘ ሱዳን ታይምስ እና ዳቦንጋ ሱዳን ዘገባዎችን በምንጭነት ተጠቅሟል።
ፎቶ: የታሲስ መግለጫ: ስካይ ላይት ሆቴል አዲስ አበባ /ቲክቫህ ኢትዮጵያ



