የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደመሌ ለፓርቲው በእጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ ውሳኔ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ዛሬ ሰኞ ግንቦት 16 በነበረው የችሎት ውሎው ነው።
ችሎቱ ውሳኔውን የሰጠው የባልደራስ ፓርቲ አመራሮችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈውን እና በስተኋላ ላይም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸደቀውን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ነው። የባልደራስ ፓርቲ እነ አቶ እስክንድር ነጋ በመጪው ምርጫ በእጩነት እንዲመዘገቡለት ምርጫ ቦርድን ቢጠይቅም፤ አመራሮቹ በህግ ከለላ ስር ስለሚገኙ ለምርጫ እጩነት መመዝገብ አይችሉም በማለት ቦርዱ ጥያቄውን ሳይቀበለው መቅረቱ ይታወሳል።
የምርጫ ቦርድን ውሳኔ የተቃወመው ባልደራስ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወስዶት ነበር። ጉዳዩን የተመለከተው የከፍተኛው ፍርድ ቤት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በማጽደቁ፤ ባልደራስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤት ብሏል።
የባልደራስን አቤቱታ በሚያዝያ 29፤ 2013 የተቀበለው የሰበር ሰሚ ችሎት፤ ፓርቲው ያቀረበውን መከራከሪያ መርምሯል። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ላይ ማንኛውም በህግ እና በፍርድ ውሳኔ የመምረጥ መብቱ ያልተገፈፈ ሰው በዕጩነት መቅረብ እንደሚችል መደንገጉን ባልደራስ በአቤቱታው አንስቷል። ድንጋጌው ይህን ቢልም ምርጫ ቦርድ ግን በትርጉም አሳብቦ አዲስ ድንጋጌ በአዋጁ ውስጥ ማካተቱ ተገቢ አይደለም ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የከፍተኛው ፍርድ ቤት እና የምርጫ ቦርድ ውሳኔዎች፤ የተከሰሱ ሰዎች በፍርድ ሂደት ውስጥ ባሉበት ጊዜ ንጹህ ሆኖ የመገመት መብታቸውን (presumption of innocence) በጽኑ የሚጎዳ ነው ሲል ፓርቲው በአቤቱታው ጠቅሷል። ስለሆነም ምርጫ ቦርድ በአራቱ የባልደራስ አባላት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ እና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአብላጫ ድምፅ የሰጠው ውሳኔ ተሽሮ አባላቱ በዕጩነት እንዲመዘገቡ በማለት ጠይቆ ነበር።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የእጩዎችን ምዝገባ በሚመለከት የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሆኑ ፓርቲው ይግባኝ የማቅረብ መብት የለውም በማለት ተሟግቷል። በእስር ቤት የሚገኙ እና የዋስትና መብታቸውን የተከለከሉ የፓርቲው አባላት በምርጫ ሂደቱ በነጻነት የመንቀሳቀስ እና ከመራጩ ህዝብ ጋር መገናኘት እንደማይችሉ አገናዝቦ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔም ተገቢ ነው ብሏል።
የፓርቲው አባላት “በእጩነት ተመዝግበው ቢመረጡ በእስር ቤት እያሉ የመረጣቸውን ህዝብ ማገልገል አይችሉም” መባሉ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጋፋ ውሳኔ አይደለም ሲል ምርጫ ቦርድ በምላሹ ላይ ተከራክሯል። በሌላ በኩል ደግሞ የባልደራስ ፓርቲ፤ አራት አባላቱ በእጩነት እንዲመዘገቡ በጠየቀባቸው የምርጫ ክልሎች ላይ፤ ሌሎች እጩዎችን ያስመዘገበ በመሆኑ ጥያቄው አግባብ አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
አምስት የሰበር ሰሚ ዳኞች የተሰየሙበት የዛሬው ችሎት፤ በምርጫ አዋጁም ሆነ በህገ መንግስቱ ላይ የዜጎች የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብት የሚነፈገው በህግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ ካገኘ በኋላ ነው ብሏል። ስለሆነም በተያዘው ጉዳይ የፓርቲው አመራሮች በህግ የተላለፈባቸው ውሳኔ ባለመኖሩ በእጩነት መመዝገብ ይችላሉ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል። አጠቃላይ የምርጫ አላማ የዜጎችን ተሳትፎ ማረጋገጥ ሆኖ ሳለ፤ በህግ ግልጽ ተደንግጎ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ምርጫ ቦርድ የፓርቲው አባላት በእጩነት መወዳደር አይችሉም ማለቱ የህግ መሠረት የለውም በማለትም ፍርድ ቤቱ የቦርዱን ውሳኔ ውድቅ አድርጎታል።
የባልደራስ ፓርቲ አመራሮች አሁን ለእጩነት ለመመዝገብ በጠየቁበት የምርጫ ክልሎች ላይ ሌሎች ተተኪ ተወዳዳሪዎችን ማስመዝገባቸውን በመጥቀስ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ምላሽም እንዲሁ በሰበር ሰሚ ችሎቱ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ችሎቱ ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሰው፤ ምርጫ ቦርድ ተተኪ እጩዎች ያላቸውን በዝርዝርና በማስረጃ አስደግፎ አለማቅረቡን ነው።
በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞከራሲ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች በአካል ቀርበው ችሎቱን ተከታትለዋል።
በቅድስት ሙላቱ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
- ፖሊስ “ቴዎድሮስ በሚስቱ ሚዲያ ለምን ቤቱ ቅጭ ብሎ መግለጫ አይሰጥም ነበር?ዘፈኑ ገና ከመለቀቁ በፊት ጀምሮ በተከታታይ አየሩን የያዙት መረጃዎች ሁሉ በኦፊሳል ከቴድሮስ ካሳሁን፣ ከባለቤቱ ወይም በህግ የሚታወቁ… Read more: ፖሊስ “ቴዎድሮስ በሚስቱ ሚዲያ ለምን ቤቱ ቅጭ ብሎ መግለጫ አይሰጥም ነበር?
- ቅዳሜ ምሽት በዋሽንግተን ዲሲ ሂልቶን፤ ሶስት ቀን የተደበቀው “ትኩላ” ዝርዝር ሪፖርትአዲስ ሪፖርተር ዜና – “ቅዳሜ ምሽት፤ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ታዋቂው ሂልተን ሆቴል በደመቀ ድባብ ውስጥ ነበር። በመቶዎች… Read more: ቅዳሜ ምሽት በዋሽንግተን ዲሲ ሂልቶን፤ ሶስት ቀን የተደበቀው “ትኩላ” ዝርዝር ሪፖርት
- “ኢሳያስ ከአሜሪካ ወዳጅነትን ይፈራሉ፤ ግንቡ ይፈርስባቸዋል” ቲቦር ናጊለሶስት አስርት ዓመታት በማዕቀብ ተቆልፎባት የኖረችው ኤርትራ በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ ሰንሰለቱ ተበጥሶላት ነበር። ጦርነትም፣ ሰላምም ባልነበረበት… Read more: “ኢሳያስ ከአሜሪካ ወዳጅነትን ይፈራሉ፤ ግንቡ ይፈርስባቸዋል” ቲቦር ናጊ
- አውሮፓ ህብረት የጋራ መከላከያ ለማቋቋም የስምምነት ረቂቅ ሊያዘጋጅ ነውቪኦኢ ዜና -በአውሮፓ ህብረት እና በሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) መካከል ያለው ግንኙነት ጥርጣሬ ውስጥ በወደቀበት… Read more: አውሮፓ ህብረት የጋራ መከላከያ ለማቋቋም የስምምነት ረቂቅ ሊያዘጋጅ ነው

