[ዋዜማ ራዲዮ]- ቀድሞ በትግራይ ክልል ስር የነበሩና ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ክልል መተዳደር በጀመሩ አካባቢዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ አከፋፈል በየደረጃው ያሉ ሃላፊዎችን አላስማማም። ከመንግሥት ደሞዝ እየተከፈላቸው ካሉት ሠራተኞች መካከል በሕይወት የሌሉ፣ ወደ ሥራ ገበታቸው ያልተመለሱ እና ከአማፂው ሕወሓት ጋር ወደ በረሀ ወርደው መንግሥትን እየተዋጉ ነው የተባሉ ይገኙበታል።
በትግራይ ክልል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ መደበኛው የመንግሥት ሥራ ከሁለት ወራት በላይ ተቋርጦ ነበር። ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መሰየሙን ተከትሎ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀረቧል። አንዳንዶች ወደ ሥራ ሲመለሱ ሌሎች ሕወሓትን ተከትለው “ወደ በረሀ ወርደዋል”። በጦርነቱ ሒደት ቀድሞ በትግራይ ክልል ይተዳደሩ የነበሩ አንዳንድ አካባቢዎችን በኃይል የተቆጣጠረው የአማራ ክልል መንግሥት በያዛቸው አካባቢዎች ላሉ የበላይ አመራሮች (የፖለቲካ ተሿሚዎች) ደሞዝ መክፈል የጀመረው ብዙም ሳይቆይ ነው። ለበታች ሠራተኞች ደግሞ በትግራይ ክልል መንግሥት በኩል ከፌደራሉ መንግሥት በጀት ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው ተደርጓል።
ዋዜማ በደቡብ ትግራይ (አሁን በአማራ ክልል እየተዳደረ ያለው) የፋይናንስና አስተዳደር ሠራተኞችን ጠይቃ እንደተረዳችው ማን በሥራ ገበታው ላይ እንዳለና እንደሌለ ተገቢ ቁጥጥር ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኗል። በጸጥታ ችግር ምክንያት የተረጋጋ የመንግሥት ሥራ ማካሄድ አለመቻሉ የሠራተኞች ቁጥጥርን አዳጋች አድርጎታል። ክልሉ አሁንም ቀድሞ በነበረው የደሞዝ መክፈያ ሰነድ እየተጠቀመ ነው።
የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ካሳ ረዳ ለዋዜማ ራዲዮ እንደገለጹት ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት የመንግሥት ሠራተኞች ሲከፈላቸው በነበረው የገንዘብ መክፈያ (ፔሮል) ዛሬም (የሚያዚያ ወር መጀመሪያ) በተመሳሳይ መንገድ የፌዴራል መንግሥት እየከፈለ መሆኑን ተናግረዋል።
በራያ ግንባር ጦርነት ሲከፈት አካባቢውን ለቀው የወጡ እና በአሁኑ ወቅት የት እንዳሉ የማይታውቁ የአካባቢ አመራሮች ዛሬም በስማቸው ገንዘቡ ወጥቶ በባንክ ደብተር ቁጥራቸው ገቢ እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ ካሳ ለዋዜማ አረጋግጠዋል። ከእነዚህ አመራሮች አንዳንዶቹ ገና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ እና ትጥቅ ይዘው የጠፉ አመራሮች መሆናቸውን ከንቲባው ጠቁመዋል።
ከንቲባው እንዳሉት ይህንኑ በተመለከተ ለፌዴራል የገንዘብ ሚኒስቴር ማስተካከያ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ገልጸው ይሁን እንጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስካሁን ማስተካከል እንዳልቻለ ተናግረዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደ ትንሳኤ መኮነን በበኩላቸው አላማጣ ከተማን ጨምሮ በባላ፣ ዋጃ እና በሌሎች በዙሪያው በሚገኙ ከተሞች እና ወረዳዎች የሚሰሩ የመንግሥት ሠራተኞችን አስመልክተው በሥራ ገበታቸው የተገኙ እና ያልተገኙ በሚል ለመንግሥት በየወሩ ሪፖርት ቢልኩም የቀድሞው የተከፋዮች ዝርዝር አሁንም አልተስተካከለም።
የአማራ ክልል መንግሥት ደመወዝ የሚከፍለው ለፖለቲካ ተሿሚ የበላይ አመራሮች እንጂ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች አለመሆኑን የገለጹት አቶ ወልደ ትንሳኤ በአላማጣ እና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ከፌደራል መንግሥት በቀጥታ በትግራይ ክልል በኩል እንደሚከፈላቸው ተናግረዋል።
በአላማጣ ከተማ አስተዳደር፣ በዋጃ ፣ በጥሙጋ እና በባላ ከተሞች በተለያዩ የአመራር ቦታዎች የተመደቡ የሥራ ሀላፊዎችን ደመወዝ የአማራ ክልል መንግሥት እየከፈለ እንደሚገኝም የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።
ቀደም ሲል በጦርነት የደመወዝ ክፍያ ተቋርጦ እንደነበር ያስታወሱት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ካሳ ረዳ የአማራ ክልል መንግሥት ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች የሁለት ወር ደመወዝ መክፈሉን እና የሥራ ማስኬጃ በጀት መድቦ ከተማዋ መንቀሳቀስ መጀመሯን ተናግረዋል።
“ በዚያን ወቅት በሥራ ገበታቸው ያልተገኙ የህወሓት አመራሮችን ተከትለው የጠፉ ግለሰቦችን ለይተን ደመወዝ እንዳይከፈል ማድረግ ችለን ነበር ፤ ይሁን እንጂ በፌዴራል መንግሥት እንዲከፈል መመሪያ ሲመጣ ጫካ ገብተው መንግሥትን የሚወጉ የሕወሓት ታጣቂዎች ሳይቀር በባንክ ቁጥራቸው ደመወዛቸውን እንዲያገኙ ሆኗል” ሲሉ አቶ ካሳ ረዳ ተናግረዋል።
ዋዜማ ራዲዮ ይህንኑ በማስመልከት ገንዘብ ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጣት ጠይቃ ነበር ። የተቋሙ ኮሚኒኬሽን ባለሙያ ገንዘቡ በየወሩ ለትግራይ ክልል ገቢ እንደሚደረግ እና በሥራ ገበታቸው የተገኙትን አጣርቶ ደመወዝ መክፈል ያለበት ክልሉ እንጂ የገንዘብ ሚኒስቴር አይደለም ብለዋል። ስለሆነም የትግራይ ክልል ይህንን ችላ ብሎ በሥራ ገበታቸው ያልተገኙ ሰዎች ደመወዝ እየከፈለ ከሆነ መጠየቅ ያለበት ክልሉ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
የትግራይ ክልል ፕላን እና ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ካሕሳይ ብርሃነ በበኩላቸው ለዋዜማ እንደገለጹት ከህወሓት ታጣቂዎች ጋር ተከትለው ወደ “በረሀ የገቡ እና በሕይወት የሌሉ ሰዎች ሳይቀር ደመወዝ ይከፈላቸዋል” የሚለውን እስካሁን እንደማያውቁና የተባለው እውነት ሆኖ ከተገኘ ግን በየወረዳው ተመድበው ይህንኑ መቆጣጠር የነበረባቸው አመራሮች ተጠያቂ ይሆናሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]
- ፖሊስ “ቴዎድሮስ በሚስቱ ሚዲያ ለምን ቤቱ ቅጭ ብሎ መግለጫ አይሰጥም ነበር?ዘፈኑ ገና ከመለቀቁ በፊት ጀምሮ በተከታታይ አየሩን የያዙት መረጃዎች ሁሉ በኦፊሳል ከቴድሮስ ካሳሁን፣ ከባለቤቱ ወይም በህግ የሚታወቁ ወኪሎቹና ተቋማትን ምንጭ ያደረጉ አልነበሩም። ይህ እስከታተመ ድረስ ቴዲም ሆነ የተጠቀሱት አካላት ስለሚሰሙት ቁጥር ስፍር የሌላቸው መረጃዎች በአዎንታም ሆነ በአሉታ አልተነፈሱም። ነገሮችን በጥሞና የሚከታተሉ “ቴድሮስ ራሱ ወይም አግባብነት ያላቸው ሃቁን ለህዝብ ለምን አይናገሩም? ህዝብ ሲተራመስ ዝም የሚሉት ለምንድን… Read more: ፖሊስ “ቴዎድሮስ በሚስቱ ሚዲያ ለምን ቤቱ ቅጭ ብሎ መግለጫ አይሰጥም ነበር?
- ቅዳሜ ምሽት በዋሽንግተን ዲሲ ሂልቶን፤ ሶስት ቀን የተደበቀው “ትኩላ” ዝርዝር ሪፖርትአዲስ ሪፖርተር ዜና – “ቅዳሜ ምሽት፤ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ታዋቂው ሂልተን ሆቴል በደመቀ ድባብ ውስጥ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ታዋቂ ግለሰቦች የኋይት ሃውስ የጋዜጠኞች ማህበርን ዓመታዊ እራት ለመታደም ተሰብስበዋል። ከ2600 ባልይ እንግዶች ፊት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በክብር መድረኩ ላይ ተቀምጠዋል። ሴሽታው እየተጠበቀ ባለበት ሰዓት ድንገት አዳራሹን… Read more: ቅዳሜ ምሽት በዋሽንግተን ዲሲ ሂልቶን፤ ሶስት ቀን የተደበቀው “ትኩላ” ዝርዝር ሪፖርት
- “ኢሳያስ ከአሜሪካ ወዳጅነትን ይፈራሉ፤ ግንቡ ይፈርስባቸዋል” ቲቦር ናጊለሶስት አስርት ዓመታት በማዕቀብ ተቆልፎባት የኖረችው ኤርትራ በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ ሰንሰለቱ ተበጥሶላት ነበር። ጦርነትም፣ ሰላምም ባልነበረበት ሁኔታ ተዘግቶባት የነበረችው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም አውርደው ብዙም ሳይቆዩ አሁን ወዳሉበት ደረጃ ደረሱ። የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምንት መፈረሙን ተከትሎ ያኮረፉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ሰሞኑን አሜሪካ መልሳ ልትዋዳጃቸው ማቀዷ ተሰምቷል። ዜናው መልካም ቢሆንም ኢሳያስ ግን አይቀበሉትም የሚል አስተያየት እየተሰጠ ነው።… Read more: “ኢሳያስ ከአሜሪካ ወዳጅነትን ይፈራሉ፤ ግንቡ ይፈርስባቸዋል” ቲቦር ናጊ
- አውሮፓ ህብረት የጋራ መከላከያ ለማቋቋም የስምምነት ረቂቅ ሊያዘጋጅ ነውቪኦኢ ዜና -በአውሮፓ ህብረት እና በሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) መካከል ያለው ግንኙነት ጥርጣሬ ውስጥ በወደቀበት በዚህ ወቅት፣ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በድንገተኛ አደጋ ጊዜ እርስ በርስ የሚረዱበትን አዲስ የጋራ መከላከያ ስምምነት ረቂቅ ለማዘጋጀት መስማማታቸውን አስታወቁ። በቆጵሮስ አስተናጋጅነት በተካሄደው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተወሰነው ይህ ውሳኔ፣ አውሮፓ በራሷ የመከላከያ አቅም ላይ እንድትተማመን ለማድረግ የታለመ… Read more: አውሮፓ ህብረት የጋራ መከላከያ ለማቋቋም የስምምነት ረቂቅ ሊያዘጋጅ ነው





