ኢትዮጵያ አጠቃላይ ካላት የቆዳ ስፋት ግማሽ ያህሉ የስነምህዳር መናጋት የሚታይበት በመሆኑ ማከም ይገባል ሲሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ዛሬ በመላ ሀገሪቱ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሐግብር እየተከናወነ ይገኛል።
አዲስ አበባ በሚገኘው የሁነት መከታተያ ማዕከል በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጽያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብርን እንድትጀምር ያደረጋት የስነምህዳር መጎሳቆል ነው።
ኢትዮጵያ አጠቃላይ ካላት ጠቅላላ የመሬት ስፋት ውስጥ 54 ሚሊዮን ሄክተሩ የተለያየ ዓይነት የስነምህዳር መናጋት የሚታይበት መሆኑ በጥናት የተረጋገጠ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህንን የስነምህዳር መናጋት ለማከም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር እየተተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በችግኝ ለመሸፈን መታቀዱን ገልጸው፤ አንድ ሚሊዮን ሄክታሩ ላይ ችግኞችን መከታተል እንዲያስችል “ጂኦሪፈረንስ” የማድረግ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
የዛሬው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር በስምንት ሺህ 454 ቦታዎች የሚከናወን ሲሆን፤ ይህም 317 ሺህ 521 ሄክታር ይሸፍናል ሲሉ አስረድተዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የተጀመረው የሰነምህዳር መናጋትን ለማከም፣ ምርትና ምርታማነትን እና የደን ሽፋንን ለማሳደግ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሄለን ወንድምነው
ነሀሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

