በቀን 150ሺህ ኩንታል የማምረት አቅም ያለውን የለሚ ብሔራዊ የሲሚንቶ ፋብሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል። ፋብሪካውን አስመልክቶ ” ይህ ሜጋ ፕሮጀክት የመንግሥታችን በፍጥነት፣ በግዝፈት እና በንፅህና የመገንባት ጽኑ አቋም ማሳያ ነው” ሲሉ በግል የማህበራዊ ገጻቸው አድንቀው ጽፈዋል።
ከአዲስ አበባ ከ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን አንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ ውስጥ በለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የተገነባው ይህ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሲሚንቶ አቅርቦት ችግርን ይቀርፋል በሚል መንግስት ከፍተኛ ክትትል እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል በጉብኝታቸው ወቅት አስታውቀው ነበር።
እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት እና በብቃት አጠናቅቆ ዝግጁ የማድረግ ተምሳሌት መሆኑንም ገልፀው ባስራጩት መልዕክት ይህ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ተደምረው የሚያመርቱትን 50 ከመቶ የሚያመርት ፋብሪካ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ በሙሉም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በግንባታ ላይ እያለ የዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ፕሬዚዳንት ሚስተር ዋንግፋይ ፋብሪካውን አቅም በተመለከተ መረጃም ሲሰጡ በአፍሪካ በምርት መጠኑ ከፍተኛ የሆነውን ፋብሪካ መገንባት መቻላቸው ለኩባንያቸው ትልቅ ስኬት እንደሆነ አምልክተው ነበር። በአፍሪካ ደረጃ ለሚ ናሽናል የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊያመርት የሚችለውን ያህል ሲሚንቶ የሚያመርት ፋብሪካ አለመኖሩን ሚስተር ዋንግ በወቅቱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አበባየው በቀለ (ኢንጂነር)፣ ፋብሪካው ከአፍሪካ ትልቁ ነው የተባለው ተጨባጭ መረጃ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሲሚንቶ ፋብሪካ የሚለካው በቀን በሚመርተው የአሊንከር መጠን ነው፡፡ አሊንከር ዋና የሲሚንቶ ጥሪ እቃ ኮምፖነንት ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን 10 ሺሕ ቶን አሊንከር የሚያመርት በመሆኑ ይህ የአሊንከር መጠን ወደ ሲሚንቶ ሲቀየር 15 ሺሕ ቶን ሲሚንቶ ወይም 150 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ በቀን ያመረታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት በዚህን ያህል ደረጃ የሚያመርት ፋብሪካ በአፍሪካ የሌለ በመሆኑ የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ግዙፉ አፍሪካ ሲሚንቶ ፋብሪካ ያደርገዋል በማለት ፋብሪካው ያለውን የማምረት አቅም ገልጸዋል።
“ከሁለት አመታት በኋላ ወደዚህ ስፍራ ስመለስ የአመራር መርሆዎቻችን ማሳያ በሆነው በሥራው ፍጥነት ተደንቄያለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፕሮጀክቱ በመሰል ጠንካራ ሥራ መጪው ትውልድ ድህነትን እንደማይወርስ ይልቁንም ለእድገት እና ብልጽግና ጥሩ መደላድል እንደሚጠብቀው ያሳያል” ብለዋል።
እንደ ለሚ ያሉትን የኢንደስትሪ ፕሮጀክቶች በመላው ሀገሪቱ ካባዛን በሥራ ፈጠራ እና በሀገራዊ እድገት ላይ የሚኖረው የመባዛት ፍሬ አቻ የማይገኝለት ይሆናል ሲሉም ነው የገለፁት። በተለይም በብረት ምርት፣ በማዳበሪያ ምርት ብሎም በሰፊው የኢንደስትሪ እና ግብርና ልማት አብዮት የሚኖረው ተፅዕኖ ሰፊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትልቅ ሀገራትን የሚገዳደሩ ፈተናዎች ከፍ ያለ ደረጃ ያላቸው መፍትሔዎችን ይሻሉ ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ(ዶ/ር)÷ በመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የሚኖር የጋራ ትብብር እምቅ ሀብትና እድሎችን ለመጠቀም ብሎም ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሰል ሥራዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የብዙ ዜጎችን ሕይወት ማሻሻል እንዲሁም ክብር ያለው አኗኗር እንዲኖሩ ማድረግ እንደሚቻልም ነው የጠቆሙት፡፡

