ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ቻይና ተጨማሪ ታሪፍ እንደሚጠብቃቸው ከሰሞኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ በመናገር የተጨማሪ ታሪፍ ጦርነቱን አስጀምረዋል።
ትራምፕ በሜክሲኮ እና በካናዳ 25 በመቶ እንዲሁም በቻይና 10 በመቶ ቀረጥ ለመጣል እንዳሰቡ ዋይት ሀውስ አስታውቋል።
ትራምፕም ከቀናት በፊት የካናዳ ዘይት 10 በመቶ ዝቅተኛ ታሪፍ እንደሚጣልበት ተናግረው፤ ይህም ከየካቲት 18 በኋላ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት አሜሪካንን በጥሩ ሁኔታ አላስተናገደም ያሉት ፕሬዚዳንት ትራንፕ፤ ወደፊት በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
ትራምፕ ርምጃው የአሜሪካን ድንበሮች አቋርጠው የመጡትን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ሰነድ አልባ ስደተኞች እንዲሁም ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያለውን የንግድ መዛባት ለመፍታት ነው ሲሉም ደጋግመው ተናግረዋል።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ትራምፕ በቻይና የተሰሩ ምርቶችን እስከ 60 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተው የነበረ ቢሆንም፤ ወደ ኋይት ሀውስ በተመለሱ የመጀመሪያ ቀናቸው ምንም አይነት አፋጣኝ ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ አስተዳደሩ ጉዳዩን እንዲያጠና ትእዛዝ ሰጥተዋል።
ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶችም ከ2018 ጀምሮ መጠናቸው ቀንሷል።
እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገለፃ፣ ይህ የተፈጠረው ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው በጣሉት ተከታታይ ታሪፍ ምክንያት ነው።
አንድ የቻይና ከፍተኛ ባለስልጣን የትራምፕ ወደ ፕሬዝዳንትነት መመለስ በዓለም ሁለት ታላላቅ ኢኮኖሚዎች መካከል ያለውን የንግድ ጦርነት ያባብሰዋል የሚል ስጋት እንዳለቸው ተናግረዋል። ግን አሜሪካን በስም አልጠቀሱም።
በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ንግግር ያደረጉት የቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዲንግ ዙዢያንግ ሀገራቸው የንግድ ውጥረቶችን ለመፍታት “ሁለቱን ወገን አሸናፊ የሚያደርግ” መፍትሄ እየፈለገች እንደሆነና ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች መጠን መጨመር እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
ቻይና፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ቀዳሚዎቹ የአሜሪካ የንግድ አጋሮች ሲሆኑ፤ ባለፈው ዓመት ወደ አሜሪካ ከገቡት ዕቃዎች 40 በመቶ የሚሆኑ ከእነዚህ ሀገራት የገቡ ናቸው።
የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ የፕሬዝደንቱ ውሳኔ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ትራንፕ በውሳኔያቸው ፀንተው ከቀጠሉ እኛም ተመሳሳይ ርምጃ ለመውሰድ እንሰራለንም ብለዋል።
ካናዳ እና ሜክሲኮም ለአሜሪካ ታሪፍ በራሳቸው ርምጃዎች ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡት በአሜሪካ ቻይና ኤምባሲ የሥራ ኃላፊ እንደተናገሩት፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከካናዳ እና ከሜክሲኮ የምታስገባው ዘይት ተጨማሪ ግብር ከተጣለበት ትራምፕ የኑሮ ውድነትን ለማውረድ የገቡትን ቃል እንዳይፈፅሙ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ታሪፍ በውጭ አገር በሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የሚጣል ግብር ነው።
በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ወደ ሀገር የሚገቡ ዕቃዎች ላይ ተጨማሪ ግብር መጣል የሚያስፈልገው ዕቃዎቹ ውድ ስለሚሆኑ ስዎች የመግዛት ዕድላቸው አነስተኛ እንዲሆን ነው።
በምትኩ ዜጎች ርካሽ የሀገር ውስጥ ምርቶችን መግዛት እንዲችሉ ለማድረግ ነው። ይህ የሀገርን ኢኮኖሚ ያሳድጋል።
ነገር ግን ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው የታሪፍ ዋጋ አነስተኛ ነጋዴዎችና ሸማቾች ሊተላለፍ ስለሚችል ከነዳጅ እስከ አነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ድረስ ያለውን ዋጋ ከፍ ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።
ትራምፕ ያስተላለፉት የተጨማሪ ታሪፍ ህግ ተፅዕኖ ለአነስተኛ ሸማቾች ጭምር የሚተላለፍና በግብይት ሂደት ውስጥ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የሚቆይ መስተጓጎል ሊፈጥር ይችላል ተብሏል።
የካናዳ እና የእንግሊዝ ማዕከላዊ ባንኮች የቀድሞ ኃላፊ ማርክ ካርኒ ለቢቢሲ ኒውስ ናይት እንደተናገሩት፤ ታሪፉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንደሚጎዳ እና የዋጋ ንረትን ያባብሳል።
ጀስቲን ትሩዶን በመተካት ቀጣዩ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትርና የሀገሪቱ ሊበራል ፓርቲ መሪነት እየተፎካከሩ ያሉት ካርኒ፤ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ርምጃ “የአሜሪካን ስም በዓለም ዙሪያ የሚያጠለሽ ነው”።
በክብረአብ በላቸው ጥር 27/2017 (ጋዜጣ+)
ብሄራዊ ጥቅም መሰረታችን!! "Reporting with Integrity: National Interest Above All."

