የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል በተባሉ ስድስት ግለሰቦች ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ክስ ተመሰረተ።
የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በነ ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል) መዝገብ በስድስት ተከሳሾች ላይ አውሮፕላንን ያለአግባብ መያዝ ወንጀል፣ የመንግስት ሰራተኛ የስራ ግዴታውን እንዳይፈጽም መቃወምና አለመታዘዝ ወንጀል ክስ በተጨማሪም በ1ኛ ተከሳሽ ብቻ ደግሞ የአየር መንገዱን መልካም ስም ለማጉደፍ ተንቀሳቃሽ ምስል በኮምፒውተር ስርዓት አማካኝነት ማሰራጨት ወንጀል የሚል ክስ አቅርቧል።
ተከሳሾቹ ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤልያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው በ1ኛ ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን ይኸውም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (ንዑስ ቁጥር 1/ሀ)፤ አንቀጽ 35 እንዲሁም አንቀጽ 507 ንዑስ ቁጥር 1 ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።

