“የዞኑ ሰላም የተበጠበጠው እና ሕዝቡ እየተሰቃየ ያለው ከራሱ አብራክ በወጡ የውስጥ ልጆች ነው” ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ
በደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር የተለያዩ የፀጥታ ኀይሎች የተሳተፉበት የሰላም ውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ “ሻማን ማን አቃጠለሽ ቢሏት ከተለኮሰብኝ ክብሪት በላይ አቅፌ የያዝኳት ክር ናት” እንዲሉ የዞኑ ሰላም የተበጠበጠው እና ሕዝቡ እየተሰቃየ ኑሮውን የሚገፋው ከራሱ አብራክ በወጡ የውስጥ ልጆች ነው ብለዋል።
“አጥፊ ጠላት ከሩቅ አይመጣም” እንደሚባለው “ዋናው ጠላት ጉያችን ውስጥ ላይ ነው” ሲሉም ነው የገለጹት። ያለውን ችግር እንደሚሻገሩትም ነው ያስረዱት።
ዞኑ የሕግ የበላይነት ማስከበር ተግባርን ለማከናወን እና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት ዕቅድ ይዞ እየተረባረበ ነው ብለዋል።
የራሱን ፍላጎት ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ ያለው የጥፋት ኀይል ላይ አሁን የተጀመረውን እርምት አጠናክሮ ለማስቀጠል የጋራ መግባባት ይጠይቃል ብለዋል።
በፖለቲካ አመራሩ እና በፀጥታ መዋቅሩ ላይ የሚስተዋሉትን የብቃት መጓደል እና የአስተሳሰብ ዝንፈቶችን በማረም ለሕዝቡ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ለነገ የማይባል ተግባር እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው ከአመራር ብቃት መጓደል እና ከአስተሳሰብ ዝንፈት ራስን ለማውጣት ብሎም የተሻለች ሀገር ለመፍጠር የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና መፍጠር የመድረኩ ዓላማ እንደኾነ ነው ያስረዱት።
የችግሮች መውጫ በር የኾነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሰላምን በማስፈን መስዋዕት እየከፈለ አሁን ድረስ አብሮ ስለመዝለቁ ነው የተናገሩት።
የተጀመረው የምልዑነት ምዕራፍ ዕውን እንዲኾን የፀጥታ መዋቅሩ ከምንጊዜውም በላይ ቅንጅታዊ አሠራሮችን በመፈጸም የፀጥታ መዋቅሩ ዝግጁ መኾን አለበት ነው ያሉት።
ከኀላፊነት የተነሱ መሪዎች የመንግሥትን መሳሪያ ለጠላት ግብዓት በማዋል በሥልጣን ላይ እያሉ ያላሳኩትን የጥቅመኝነት ተግባር ለማሳካት እየተጉ ያሉትን እንዲታረሙ እንደሚደረግ ነው ያስረዱት።
የሀገርን እና የሕዝብን ሰላም እየናጡት ያሉት ከሀገር እና ከሕዝብ አብራክ የወጡት የግል ጥቅመኞች ናቸው ብለዋል።
አቶ ጥላሁን አማራን አንሶ ለማሳነስ በሚሠሩ ማናቸውም አካላት ላይ የሚወሰደው የሕግ ማስከበር ተግባር ከመቸውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት።
ማኅበረሰቡ ሎጀስቲክስ አምጣ እየተባለ በጠላት ኀይሉ እየተሰቃየ መኾኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ ለተጀመረው የምሉዕነት ሕግ የማስከበር ተግባር ከመቸውም ጊዜ በላይ ቁርጠኞች ስለመኾናቸው አረጋግጠዋል።
የትምህርት ቤቶችን ቆርቆሮ፣ ወንበር እና የተለያዩ ቁሶችን በመመዝበር እና በማፈራረስ በቆራሊዮ መልክ በመሸጥ ለመበልፀግ የተዘጋጀ የጠላት ኀይል ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰድ እንደሚገባም ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ፀጋዬ ጌቴ እንደ ደቡብ ጎንደር ዞን ፖሊስ አብዛኛው ኀይል እስከ ሕይዎት መሥዋዕትነት ድረስ የሚሠራ አስተማማኝ ቁመና ላይ ነው ብለዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌትነት በዛ “የኔ ሰው ነው የሚለው መቆም አለበት የእናትህ ልጅም ቢኾን ጫካ የገባ ኀይል ሲያገኝ እንደማይምር በመገንዘብ ቆርጠን መሥራት አለብን” ነው ያሉት።
የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፈተው ከባለፈው የሕይዎት ጉዞ በመማር ዞኑ ከገባበት የምስቅልቅል እና የሰቆቃ ሕይዎት ማውጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ከመገፋፋት ወጥተን ራሳችንን መመልከት አለብን፤ ከሕዝባችን ላይ ችግር የለም፤ ያልተፈታው ቋጠሮ እና መሰረታዊ ችግር ያለው ከእኛው ከውስጣችን ነው” ብለዋል።
የፀጥታ ኀይሉ የውስጡን ችግር በማጥራት ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ መኾን አለበት ያሉት አቶ መንበር ወርደን ሰፈር ላይ ከመወሸቅ ወጥተን የጠፋውን የሕዝብ ሰላም መመለስ አለብን፤ ከምንም በላይ “አንድ” መኾን አለብን ማለታቸውን ከደቡብ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
Amhara masmedia


