በሊባኖስ በሂዝቦላህ ቡድን ላይ ጥቃት እየፈጸመች የምትገኘው እስራዔል በ24 ሰዓታት ውስጥ 185 ያህል የሂዝቦላህ ዒላማዎችን መምታቷን ገለጸች።
የእስራኤል መከላከያ ሃይል ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ በደቡባዊ ሊባኖስ በእግረኛ ሰራዊት እየተካሄደ ያለው ዘመቻ እንዲሁም የአየር ጥቃቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።
በሂዝቦላህና በእስራዔል እግረኛ ሠራዊት መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ የእስራዔል አንድ አዛዥ መገደሉን መግለጫው አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራዔልን የአየር ጥቃት በመሸሽ ከቤታቸው የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያን በጎዳና ላይ ሕይወታቸውን እያሳለፉ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል።
የሊባኖስ መንግስት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ያህል ሰዎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ለመሆን መገደዳቸውን ገልጾ፤ ሶሪያውያንን ጨምሮ 400 ሺህ ያህል ሰዎች ወደ ጎረቤት ሶሪያ መሰደዳቸውን አስታውቋል።
180 ሺህ 700 ተፈናቃዮች በ978 የመንግስት መጠለያዎች ውስጥ የተጠለሉ ሲሆን፤ በርካቶች በጎዳና ላይ ለመጠለል መገደዳቸው ተነግሯል።
ሂዝቦላህ ምክትል መሪ ናይም ቃሲም ቡድኑ በእስራዔል ላይ የሮኬት ጥቃት መፈጸም የጀመረበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ትናንት በቪዲዮ ተቀርጾ በተላለፈው መልዕክቱ፤ ሂዝቦላህ ምንጊዜም የሃማስ አጋር ነው ብሏል።
በመሆኑም በእስራዔል ላይ የሚፈጽመው የሮኬት ጥቃት የሚቆመው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ሲደረግ ብቻ እንደሆነ አስገንዝቧል።
በአሁኑ ወቅት በደቡባዊ ሊባኖስ በእግረኛ ሠራዊት በሂዝቦላህ ዒላማዎች ላይ ጥቃት እየፈጸመች የምትገኘው እስራዔል ንጹሃን ጉዳት እንዳይደርስባቸው አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቋን በዘገባው ተመላክቷል።


