የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት ከ110 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን ማስተናገድ የሚያስችል በአፍሪካ ትልቁ አየር ማረፊያ በ5 ቢሊዮን ፓውንድ እያስገነባ ነው፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው በአምስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል፡፡
ኤክስፕረስ ኒውስ እንደዘገበው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሀገሪቱን በአፍሪካ የአቪዬሽን ዋና ማዕከል የሚያደርግ ግዙፍ አየር ማረፊያ ለመገንባት ካለው ትልቅ እቅድ ጋር እንዲሁም በቀጣናው የአቪዬሽን ገጽታ ላይ ጉልህ አሻራ ሊያሳርፍ የሚያስችል ነው።
በቢሾፍቱ አቡሴራ አካባቢ የሚገኘው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት አየር መንገዱ የአለም መሪ የአቪዬሽን ሃይል ለመሆን ለያዘው የ15 አመት ስትራቴጂ ዕቅድ የማዕዘን ድንጋይ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የአየር መንገዱን ዲዛይን ለማዘጋጀት ዱባይ ከሚገኘው አማካሪ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል።
እ.ኤ.አ. በ 2029 የሚጠናቀቀው ይህ አየር ማረፊያ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል ። ወደፊት ይህንን አቅም በማሳደግ በዓመት ወደ 110 ሚሊዮን መንገደኞች ያሳድጋል ብለዋል ።
በዛሃ ሃዲድ አርክቴክቶች (ZHA) እና በዳር አል-ሃንዳሳ አማካሪዎች እንደገለጹት፤ የኤርፖርቱ ተርሚናል ከ600 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እና 126 ሺህ ካሬ ሜትር የአየር መንገድ ድጋፍ ሰጭ ቦታን ይሸፍናል።
አቀማመጡ የሚታወቅ ፣ ሰፊና በብርሃን የተሞላ ተርሚናል ያካተተ ሲሆን ለተሳፋሪዎች እንከን የለሽ የእንቅስቃሴ ፍሰት ለማቅረብ ያለመ መሆኑንም አመላክተዋል ።
አውሮፕላን ማረፊያው ከዋና ከተማው አዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ ይገነባል።
በ35 ካሬ ኪሎ ሜትር (13.5 ካሬ ማይል) ላይ የሚዘረጋው አየር ማረፊያ ሁለት ትይዩ ማኮብኮቢያዎች የሚኖሩት መሆኑንም አቶ መስፍን አብራርተዋል።
የዜድኤ አቪዬሽን ዳይሬክተር ክሪስቲያኖ ሴካቶ በበኩላቸው፤ አውሮፕላን ማረፊያው ኢትዮጵያን የአህጉሪቱ የትራንስፖርት ማዕከል ያደርጋታል ብለዋል።
ይህም ለአፍሪካ ዓለም አቀፋዊ መግቢያ ሆኖ ኢትዮጵያን የአህጉሪቱ የትራንስፖርት አውታሮች ማዕከል የሚደርግ መሆኑን አንስተው፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ ማህበረሰቦችን በተቀናጀ የአየር ትራንስፖርት ሥርዓት ያገናኛል ሲሉም ገልፀዋል።
ከ150 በላይ በሆኑ መዳረሻዎች ዓለምን በማገልገል ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2023/24 ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ መሆን የቻለ ሲሆን ለ17 ነጥብ 1 ሚሊዮን መንገደኞች አገልግሎት በመስጠት 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ነሐሴ 3 ቀን 2016 በይፋ ስራ የጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና የዳር ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ታሪቅ አል ካኒ መካከል ስምምነት ተፈርሟል።
በማህሌት ብዙነህ (ጋዜጣ+)



