የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ንግግር ላይ ለመሳተፍ ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ማይክ ዋልትዝ ጋር ወደ ሳዑዲ እንደሚያቀኑ አስታውቀዋል፡፡
የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በሚቻልበት አገባብ በሳዑዲ አረቢያ ተገናኝተው ለመነጋገር እቅድ መያዛቸው ሲነገር ከሟል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለውን ጦርነት ማስቆም በፍጥነት እንዲጀመር ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መነጋገራቸውን ከቀናት በፊት ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ”ቡድኖች ተዋቅረው በአስቸኳይ ድርድር እንዲጀምሩ ተስማምተናል፤ ለዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ዘሌንስኪም ደውለን ስለ ውይይቱ እናሳውቀዋለን፤ ይህም እኔ የማደርገው ነገር ነው” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ክሬምሊን ፑቲን እና ትራምፕ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል በስልክ መነጋገራቸውን እና ለመገናኘት መስማማታቸውን አስታውቋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል። ዶናልድ ትራምፕ እንዴት እንደሚያሳኩት ግልጽ ባይሆንም የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን በፍጥነት እንደሚያስቆሙ ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወቃል።
አሜሪካና ሩሲያ ለንግግር መስማማታቸውን ተከትሎ የአውሮፓን አገራት ባይተዋርነት እንደተሰማቸው እየተገለሸ ነው፡፡ በዚሁ ስሜት ሳቢያ ስጋት የገባቸው የአውሮፓ አገራት አስቸኳይ ስብሰባ በፓሪስ ለማድረግ ወስነዋል፡፡ እንግሊዝ ጉዳዩን በቀላሉ እንደማታየውና ለዩክሬን የወታደር ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል አስታውቃለውች፡፡
ዩክሬን በትራምፕ የተናጥል ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑት ፕሬዝዳንት ዘለነስኪ “እኛን ያላማከለ ድርድርን አንደግፍም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሁሉም ያሻቸውን ይበሉ እንጂ ሩሲያና አሜሪካ የጀመሩትን የርቀት ንግግር አገባደው ሳኡዲ አረቢያ ለመገናኘት ቀን ቆርጠዋል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ ወደ ሳዑዲ እንደሚጓዙ ለፎክስ ኒውስ አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ማረጋገጫ ንግግሩን አስመልክቶ የተሰጠ የመጀመሪያ ይፋዊ መግለጫ ነው፡፡
ስቲቭ በፎክስ ኒውስ አማካይነት “በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መመሪያ መሰረት ስብሰባውን እናደርጋለን” ብለዋል፡፡ በንግግሩም መልካም ውጤት ላይ እንደሚደረስ ተስፋ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
“ተደውሎ ይነገራቸዋል” የተባሉት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ግን ሀገራቸው በሳዑዲ አረቢያ በሚደረገው የአሜሪካ እና ሩሲያ ንግግር ላይ እንድትገኝ እንዳልተጋበዘች ተናግረዋል። አክለውም ዩክሬን ከአውሮፓ አጋሮቿ ጋር ሳትመክር ከሩሲያ ጋር እንደማትገናኝ ገልጸዋል። የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አሜሪካና ሩሲያ በደረሱበት የድርድር ጉዳይ የአውሮፓ መሪዎችን ለአስቸካይ ስብሰባ መጥራታቸው ከንግግሩ ዜና ጎን ለጎን ይፋ ሆኗል፡፡
ቢቢሲ እንዳለው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ወር መጨረሻ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ትራምፕን በዋይት ሀውስ እንደሚያገኟቸው ይጠበቃል።
በዚያን ወቅት ዋናው አጀንዳቸው የሚሆነው የአውሮፓ መሪዎች በዩክሬንና በኔቶ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አስተያየት ለትራምፕ ማስረዳትና ማሳመን ነው። ሰር ኬር ከዋሽንግተን ከተመለሱ በኋላ ደግሞ የአውሮፓ መሪዎች፣ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር ተገናኝተው ተጨማሪ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ሰር ኬር ዩናይትድ ኪንግደም “አሜሪካን እና አውሮፓ በአንድ እንዲሆኑ ለማድረግ ትሠራለች” ሲሉ ተናግረዋል። አሜሪካና አውሮፓ በውጫዊ ጠላት የተነሳ መሀላቸው ንፋስ ሊገባ አይገባም ብለዋል። በዚህ ሳምንት መጨረሻ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ‘የተባበሩት አውሮፓ ጦር’ እንዲቋቋም ጠይቀው ነበር። ይህም የሆነው አሜሪካ ለዩክሬን ከዚህ በኋላ ወታደራዊ ድጋፍ እንደማታደርግ ከገለጸች በኋላ ነው።
ዘለንስኪ በሙኒክ የሰላም ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በጉባኤው ያሰሙት አስደጋንጭ ሐሳብ ከዚህ ወዲያ አሜሪካና አውሮፓ እንደከዚህ ቀደሙ እንደማይቀጥሉ ፍንጭ ሰጥቷል ብለዋል።
ስለዚህም አውሮፓ አህጉር ከአዲሱ እውነታ ጋር ራሱን ማስታረቅና ለአዲሱ እውነታ አይኑን መግለጥ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል። ዘለንስኪ፣ አሜሪካና ሩሲያ ከዩክሬን ጀርባ መደራደር መጀመራቸውን ነቅፈዋል።
ትራምፕና ፑቲን ከሰሞኑ ዘለግ ያለ የስልክ ውይይት ማድረጋቸው አይዘነጋም። በዚህ የስልክ ንግግራቸው የዩክሬንን ጦርነት በአስቸኳይ ማስቆም እንደሚገባ ተማምነዋል። ምናልባትም ሁለቱ መሪዎች መጀመርያ በሳኡዲ ሊገናኙ እንደሚችሉ መረጃዎች ጠቁመዋል። ምናልባትም ሁኔታዎች ከሰመሩ ፑቲን ዋሺንግተንን፣ ትራምፕ ደግሞ ሞስኮን እንደሚጎበኙም ይጠበቃል።
ዶናልድ ትራምፕ ይህን ለ90 ደቂቃ የዘለቀ ከፑቲን ጋር ያደረጉትን የስልክ ውይይታቸውን ለፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አስረድተዋቸዋል። ሆኖም ዩክሬን በዚህ ድርድር ቀጥተኛ ተደራዳሪ እንደትሆን የተፈለገ አይመስልም።
ዶናልድ ትራምፕ ነገሩን በቀጥታ ለመጨረስ የፈለጉ ይመስላል። መከላከያ ሚኒስራቸው ብራስልስ ላይ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ዩክሬን ኔቶን የመቀላቀሉ ሐሳብ ‘የማይጨበጥ እና ከእውነታው የራቀ’ ሲሉ ተችተውት ነበር።
ሩሲያ በኃይል የያዘቻቸውን ሰፋፊ የዩክሬን ግዛቶችን ለ’ቃ የመውጣቷም ነገር ‘የማይመስለ’ ብለውታል። ይህ ማለት ዩክሬን በዚህ ድርድር ተሸናፊ ሆና የምትጨርስ ይመስላል። ዶናልድ ትራምፕ ከአውሮፓ አገራት በተለይም ከኔቶ አባል አገሮች ጋር ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም።
በመጀመርያው የግዛት ዘመናቸውም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር። ከታሪፍ ጋር በተያያዘና ከኔቶ መዋጮ ጋር ተያይዞ ዶናልድ ትራምፕ የአውሮፓ አገራት የሚጠበቅባቸውን እያደረጉ አይደለም ብለው ያምናሉ።
ትራምፕ 23 የኔቶ አባል አገራት መዋጮ ከ2% ወደ 5% እንዲያሳድጉ ይፈልጋሉ። ኔቶ በአሜሪካ ጫንቃ ላይ ወድቋል የሚል አቋም አላቸው። ከትናንት በስቲያ በተደረገው የሙኒክ የሰላም ጉባኤ የአውሮፓ መሪዎች ከፍ-ዝቅ እያደረጉ የወረፉት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ አውሮፓዊያን ትልቁ ስጋታችሁ የሚመነጨው ከቻይና ወይ ከሩሲያ አይደለም ብለዋል።
“ትልቁ አደጋ የተደቀነው ከራሳችሁ ከውስጣችሁ ነው፣ የመናገር ነጻነት ትገድባላችሁ” ሲሉ አክራሪ ፓርቲዎችን በመንግሥታቸው እንዲያሳትፉ መክረዋል።
ቫንስ ከዚህ ሌላ በጀርመን ዋና ቀኝ አክራሪ ከሚባለው ፓርቲ መሪ ጋር መነጋገራቸውም ድንጋጤን ፈጥሯል። ቫንስ አውሮፓ በስደተኞች ላይ ጥብቅና የማያዳግም እርምጃ እንድትወስድም አሳስበዋል።

