እራሱን “ነብይ” አድርጎ የሚጠራውና በርካታ ተከታዮች ያሉት ኢዩ ጩፋ አዲስ አበባ የሚገኘው ክርስቲያን አርሚ የተባለው ቤተክርስቲያኑ መታገዱ ተገለጸ። ቀደም ሲል ከእገዳው በፊት በሃዋሳ በተደረገለት አጀብና በባንድ የተደገፈ አቀባበል የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ቅሬታ አሰምቶ ነነር። አዩ ጩፋም ዘጠኝ ደቂቃ በቆየ የቪዲዮ ምላሽ የጠጠረ ቃላትን በመጠቀም ምላሽ ሰጥቷል።
ይህንኑ ተከትሎ ካውንስሉ እገዳ መጣሉን ለሰላም ሚኒስትር፣ ለሁሉም የክልልና ከተማ አስተዳደሮች፣ ለካውንስሉ መዋቅሮች፣ ለካውንስሉ ስነ መለኮት ኮሚሽን፣ ለካውንስሉ ህግ ኮሚሽን ግልባጭ ባደርገበት ደብዳቤው አሳውቋል።

ክራይስት አርሚ ኢንተርናሽናል ቸርች በካውንስሉ በምዝገባ ቁጥር 03111 የተመዘገበች የሃይማኖት ተቋም መሆኗ ናት። ካውንስሉ ደግሞ በአዋጅ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሙሉ ስልታን የተሰጠው አካል መሆኑ ይታወሳል፡፡
ቤተክርስቲያኒቱ የካውንስሉ አባል ስትሆን ልታከናውናቸው ከሚገቡ መመሪያዎችና ደንቦች መካከል አንዱ የካውንስሉ አባላት ስነ ምግባር መመሪያ ሲሆን በስነ ምግባር መመሪያው አንቀጽ 9.3 ላይ የስነ ምግባር ግድፈቶች ተብለው በዝርዝር የተገለጹትን ተግባራት በቤተክርስቲያኒቱ መሪ መፈጸሙን መረጋገጡ በዕግዱ ደብዳቤ ላይ ተመልክቷል።
በመሆኑም ጉዳዩ በካውንስሉ ሥነ መለኮት ኮሚሽን እና የሕግ ኮሚሽን ታይቶ በሚመለከታቸው አካላት የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ የቤተክርስቲያኒቱ ፈቃድ ታግዶ የሚቆይ ሲሆን ሁሉም የካውንስሉ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና የሚመለከታችሁ የመንግስት አካላት ይህንንና ከዚህ በኋላ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን እንድታስፈጽሙ በግልባጭ እንደተመዘገበላቸው ደብዳቤው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ቀደም ሲል አዩ ጩፋ ሃዋሳ ለኮንፍራንስ በገባበት ወቅት በማርሽ የተደገፈ፣ በወታደራዊ አጀብና ስርዓት የተደረገለት አቀባበል ክርስቲያናዊ ስርዓትና አግባብ እንዳልሆነ ጥቅሰው የካውንስሉ አባል መግለጫ ሰጥተው ነበር።
ይህንኑ የተግሳጽ መግለጫ ተከትሎ ነብይ ኢዩ ጩፋ ለኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ካውንስል ምላሽ ያለውን የዘጠኝ ደቂቃ ቪዲዮ አሰራጭቶ ነበር።
ነብይ ኢዩ ጩፋ፣ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ካውንስል በጦር መሳሪያ የታጀቡ የአገልጋዮች ጉባኤዎች ከወንጌል አስተምህሮት ውጭ ናቸው በማለት ለሰጠው መግለጫ ምላሽ ሲሰጥ “ስራችሁን ስሩ” በማለት ዘልፏል።
“አንድ ነብይ በፓትሮል መታጀቡ አይግረማችሁ፣ መታጀብ ከፈለጋችሁ ስራ ስሩ፣ የክርስቶስ አገልጋይ መጣ ሲባል ማርሽ ባንድ አይደለም ካላንደር ሁሉ ሊዘጋ ይችላል” ሲል የተገሰጸውን ተግባሩን አሞካሽቶ አዩ ጩፋ ምላሽ ሰጥቷል።
“ብታምኑም ባታምኑም በኢትዮጵያ ምድር በራሳቸው ጄት እየተንቀሳቀሱ የሚያገለግሉ አደገኛ ሰዎች ይነሳሉ” ያለው ኢዩ፣ ከዚህ በኋላ የሚኖሩ ፕሮግራሞች ከዚህ የበለጠ እንደሚሆኑ አመልክቷል። በተራ ጫጫታ እንደማይጠፋም ገልጿል።
ከዕግዱ በሁዋላ ምን ሊሆን እንደሚችል ጠይቀን ባገኘነው መረጃ አዩ ጩፋም ሆነ ቤተክርስቲያኗ እገዳው እስካልተነሳ ድረስ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ኮንፍራንስ ማካሄድ፣ በሌሎች አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች ትምህርት መስጠት፣ ከምንግስታዊ ተቋማት ምንም ኣይነት ድጋፍ መጠየቅ፣ በአገልግሎት ዙሪያ ለሚገጥመው እክል ኃላፊነት የሚወስድለት አካል አያገኝም የሚሉና ተመሳሳይ ጉዳዮችን እንደሚነፈግ ለማወቅ ተችሏል። ጊዚያዊው እገዳ ወዴት እንደሚያመራ ለጊዜው አልታወቀም።ራሱን “ነብይ” የሚለው አዩ አዲስ አበባ እጅግ ዘመናዊ ቤተክርስቲያን ያለው ሲሆን ዘይት በመሸጥና በታምራት አገልግሎት ከፍተኛ ሃብት እንዳገኘ በተለያዩ ግዚያት ምስክር የተሰጠበት እንደሆነ የሚታወስ ነው።
በዝርዝር ባነሱት ሃሳብ ምን ብለው ነበር ?
” የመንግስት አካላት አንድ አገልጋይ ወደ ከተማ ሲገባ ፖሊስ አሰልፈው፣ መሳሪያ አስታጥቀው፣ አጀብ ፈጥረው ግርግር በማድረግ ከተማው ላይ ሌላ አካል የገባ እስኪመስል ድረስ ማድረግ ተገቢ ነው ብለን አናምንም።
ይህን ማድረጋቸው ለወንጌል አማኞች ክብር መስጠትም አይደለም የመቃብር ስፍራ አጥቶ የሚቸገር የወንጌል አማኝ ስላለ የመንግስት አካላት እሱን ያድርጉልን።
በተደጋጋሚ እንደዚህ የሚያደርጉ የተለያዩ ስያሜ ያላቸው አገልጋዮች ሊታረሙ ይገባል ብለን በጥብቅ ነው የምንቃወመው ፈጽሞ የወንጌል አማኞች ኢሜጅም አይደለም ።
በመሳሪያ ታጅቦ በዛ ሁሉ ግርግር ወደ አንድ ከተማ መግባት ምንድነው ትርጉሙ …ለእኛ ትርጉም አልባ ነው።
እንደዚህ አይነት ነገሮችን አስመልክቶ በቅርቡ መግለጫ እንሰጣለን መታገድ ያለባቸው ካሉም ይታገዳሉ በፍጹም ኮምፕሮማይዝ አናደርግም ምክንያቱም በካውንስሉ አብረን ስናመልክ ካውንስሉ ለእንደዚህ አይነት ነገሮች ጥላ ሆኖ አይደለም።
እንዲታረሙ፣ እንዲመለሱ ፣ እንዲስተካከሉ በተደጋጋሚ በፅሁፍ፣ በአካል ተነግሯቸዋል ሰርተፍኬት ሲወስዱ ፈርመዋል ይሄ ሁሉ ተደርጎ ‘ አንመለስም ‘ ብለው የዘይት ንግዳቸውን ከቀጠሉበት ዘይት መነገድ በካውንስሉ ፈቃድ ፈጽሞ አይቻልም።
ለሁሉም ክልሎች ይፋዊ ደብዳቤ ጽፈናል ቢጠየቁም እንኳን የመንግስት አካላት እንደዚህ አይነት መሳሪያ ይዞ ማጀብ ተገቢ አይደለም። ” ነበር ያሉት።
የካውንስሉን መግለጫ ተከትሎ ነቢይ እዩ ጩፋ በትላንትናው ዕለት በድምጽ መልእክት ሃሳባቸውን ሰጥተው ነበር።
በዚህም ” የክርስቶስ አምባሳደር ወደ ከተማ ይመጣል ተብሎ ማርሽ ባንድ ብቻ አይደለም ካላንደር ሊዘጋ ይችላል ፤ ገና መድፍ ይተኮሳል ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ነቢይ እዩ ጩፋ በዝርዝር ምን አሉ ?
” በመጀመሪያ የመንግስት ፓትሮል የሚወጣው ዌልካም ለማለት የሚወጣውን የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ነው ይህ የመንግስት ተቀዳሚ ሃላፊነት ነው በመቀጠል አምላክ የላከው አገልጋይ ወደ ከተማ ሲገባ ዌልካም ለማለት ነው የሚወጣው።
ከዚህ በኋላ ቪ8 ቶች (መኪኖች) ቪ8 ቶች ብቻ አይደለም በዚህ ዘመን የተፈጠረም ነገር ካለ ተጨምሮ አገልጋዮች ዌልካም ይባላሉ።
ለመቀበል እንደምትቸገሩ አውቃለሁ ነገር ግን ምርጫ የላችሁም አገልጋዮችን በንቀት አትዩ።
አገልጋዮች የእግዚአብሔር ድምጽ ፣ቃል አቀባዮች እና ምልክቶች ናቸው።
በማስፈራራት እና በማስጨነቅ ቀጥሎ የሚነሳውን ትውልድ ተስፋ ለማስቆረጥ የምትፈልጉ ሰዎች እኔ አለሁ ከዚህም በኋላ ፊት ለፊት ቆሜ ለሚመጣው ትውልድ በር ለመክፈት ከፊት አለሁ።
አንዳንድ ሰዎች ዘመኑ በሚመጥን መልኩ መንቀሳቀስን እንደ ሃጥያት ያያሉ።
ሰባት እና ስምንት ፓትሮል ለምን ይመደባል ? በዚህ ልክ መታጀቡ ለምን አስፈለገ ? የምትሉ ሰዎች ለአገልጋዮች መንግስታዊ የሆነ ጥበቃ ፣ ከለላ፣ ዌልካም ያስፈልጋል።
አንድ በእግዚአብሔር ለተሾመ አገልጋይ ምን ያህል ክብር እንደሚገባ መንግስት እና መንግስታዊ የሆኑ መዋቅሮች በተረዱበት በዚህ ጊዜ የቤተክርስቲያን መሪዎች አይናቸው መከደኑ ከምንም በላይ የሚያስገርም ነው።
ቪ8 በዛ፣ ፓትሮል በዛ የምትሉ ሰዎች እግዚአብሔር ባንተ ኮልኮሌ እንዲታጀብ ነው የምትፈልገው ? እግዚአብሔር በፓትሮል የሚታጀብ አምላክ አይደለም ፓትሮሉም ለኛ ነው እኛ ነን የምንታጀበው ከዚህ በኃላ።
ብታምኑም ባታምኑም በኢትዮጵያ ምድር በራሳቸው ጀት እየተንቀሳቀሱ የሚያገለግሉ አደገኛ ሰዎች ይነሳሉ።
የምታስተላልፉት መልዕክት ተስፋ ከመቁረጥ የመነጨ ይመስላል።
ሀዋሳ ስንገባ የተደረገልን አቀባበል ያስደነገጣችሁ ሰዎች ሰላም ናችሁ ? ለማንኛውም ከዚህ በኃላ በሚደረጉ ክሩሴዶች ከዚህ የበለጠ ነገር እንደሚሆን እንዳትጠራጠሩ ከወዲሁ አረጋግጥላችኋለሁ።


