የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ ሲያካሂደው የነበረው የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ሚያዚያ 4/2017 ዓ.ም ከተጠናቀቀ በሁዋላ ወደ መጡበት ከተመለሱት መካከል የታሰሩ መኖራቸውን ራሱን “ወሎ ቤተ አምሓራ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ” ብሎ የሚጠራው ኃይል አስታወቀ።
በስብሰባው ላይ ተገኝተው የነበሩና በቁጥጥር ስር የዋሉትን በሚያሳይ ቪዲዮ እንደተመለከተው አሳሪዎቹ ሶስት ሰዎችን እያሳዩ ጥያቄ ይጠይቃሉ። ለተጠቀሰው ስብሰባ ባህር ዳር መሄዳቸውን በመኮነን ማብራሪያ ይቀበላሉ።
በክልሉ ከ267 ወረዳዎች በተወከሉ ከ4ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች የአጀንዳ ማሰባሰቢያ የምክክር ሂደቱ ባበህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ተጀምሮ ሚያዚያ 4/2017 ዓ/ም በተጠናቀቀው የአጀንዳ ማሰባሰብ፣ ከማህበረሰብ ተወካዮች በተጨማሪ ተጽዕኖ ፈጣሪ የማህበረስብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካተቱ 6 ሺህ ወኪሎች መሳተፋቸው ተመልክቶ ነበር።
“የተላለፈላቸውን መምሪያ ችላ በማለት የሄዱትን የምክክር ኮሚሽን ተሳታፊዎች በሁሉም ቀጠና በቁጥጥር ስር እየዋሉ ይገኛሉ” የሚለው መግለጫ በስፋት ቢሰራጭም፣ በምስል አስደግፎ ያሰራቸውን በማሳየት ይፋ ያደረገው በኮለኔል ፈንታሁን ሙሀባ የሚመራው የአማራ ፋኖ ወሎ ቤተ አምሓራ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ እንደሆነ ተመልክቷል።
“በድብቅ የምክክር ኮሚሽኑን ተልዕኮ ተቀብለው ሲመለሱ በቁጥጥር ስር ውለዋል” የተባሉት ወገኖች በስልክ በስብሰባው እንዲገኙ መወከላቸው ተነግሯቸው መሄዳቸውን፣ የተነገራቸውም በውል የሚታወቅ የአስተዳደሩ መዋቅር እንደሆነ ስም ጠቅሰው ገልጸዋል።
ለሁሉም ተሳታፊዎች ከመነሻቸው ጀምሮ እስከመዳረሻቸው፣ ስብሰባው ሲጠናቀቅ የመመለሻ ትራንስፖርትና አበል መከፈሉን አውግዞ አሳሪው ወገን እንዳስታወቀው፣ ተሳታፊዎቹ መመሪያ ተላልፈው ስብሰባው ላይ መካፈላቸው ወነጀል ተብሎ ተውስዷል።
ከዚህ ቀደም በጎጃም ለሽምግልና ባህር ዳር ደርሰው የሚምለሱ ነዋሪዎችን በስፍራው የሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎች በእንብርክክ ሲያስኬዷቸው የሚያሳይ በምስል የተደገፈ መረጃ መሰራጨቱ አይዘነጋም።

