ኢትዮጵያ በመጪው ሳምንት ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 760 ሚሊዮን ዶላር እንደምታገኝ የብሔራዊ ባንግ ገዢ ማሞ ምሕረቱ አስታወቁ። ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ካፒታሏ በ235 በመቶ ማደጉም ተመልክቷል። ከሃዋላ ከፍተኛ ገቢ ቢገኝም በቀጣዩ ዓመት ልዩ ማነቃቂያ እንደሚኖር ተጠቁሟል።
የብሔራዊ ባንክን የአስራ አንድ ወራት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የባንኩ ገዢ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሁለቱ ተቋማት የምታገኘው ገንዘብ የሚለቀቀው በሰባትና ስምንት ቀናት ውስጥ ነው። ይህ ገንዘብ በአሁኑ ሰዓት እያደገ ያለውን የአገሪቱን የምንዛሬ ክምችት ከማሳደግ አልፎ በቀጥታ በአገሪቱ ገበያ ላይ በመጨመር የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተመልክቷል።
ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ በፊት ኢትዮጵያ የነበራት የምንዛሬ ክምችት በዓለምአቀፉ ገበያ ለሁለት ሳምንት የሚሆን ወጪዎቿን ብቻ የሚXእፍን ነበር። አቶ ምህረቱ እንዳስታወቁት አሁን ላይ የተያዘው የውጭ ምንዛሬ ክምችት፣ ኢትዮጵያ የሶስት ወራት የውጭ ግብይት ማድረግ የሚያስችል ደረጃ ደርሷል። በዚሁም እንደ ነዳጅ ፣ ማዳበሪያ ፣ መድሀኒት ወዘተ ለመሸመት የሚያስችል የውጭ ምንዛሬ አከማችታለች። የውጭ ምንዛሬ ክምችት ዕድገቱ በመቶኛ ሲሰላ 235% እንደሆነም ከባንኩ ገዢ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አስራ አንድ ወራት
- ከውጭ ንግድ ፣ አገልግሎት ፣ ሀዋላ ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ፣ ብድርና ድጋፍ 32.1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች ።
- የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀጠለው ሳምንት ከአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት 750 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል። በሚቀጥለው አመት ደግሞ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ይደረግለታል።
- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዓመት ለመንግስት የቀጥታ ብድር አልሰጠም። ከገበያው ላይም ከ 750 ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቧል
ይህ የባንኩ ገዢ ከሰጡት ማብራሪያ የተወሰደ ዳታ እንደሚያሳየው የፋይናንስ ዘርፉ ሪፎርም ከተካሄደ በሁዋላ በሃዋላ የተገኘው ምንዛሬ ከፍተኛ መሆኑን ያመልከቱት አቶ ማሞ፣ በቀጣይ ከሃዋላ የሚገኘውን ምንዛሬ ለማስፋት ልዩ ማነቃቂያና ስልት መነደፉን ከፋና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።
በቀጣይ የተጀመሩ የፋይናንስ ጥብቅ አሰራሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በማመልከት ለሃዋላ አድራጊዎች ልዩ ማነቃቂያ እንደሚደረግ ከመጠቆማቸው ውጪ ዝርዝሩን አልተናገሩም። በኢትዮጵያ የኤርትራ መንግስት በቀጠራቸው አማካይነት የብር አተባ እንደሚካሄድ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል።

