ሁለት ሕጻናት በቀያቸው እየተጫወቱ ነበር። ሲቪል ለብሰው የአልኮል መጠጥ ሲጠጡ የዋሉ ሁለት የኤርትራ ወታደሮች ወደ መኖሪያ ካምፓቸው እያመሩ ሳለ እነዚህን ሁለት ህፃናት እቤታቸው አጠገብ ሲጫወቱ ያገኙዋቸዋል። አንዱ ሞቅታ እየነዳው የነበረው ወታደር ህፃናቱን ከመስደብ አልፎ ይመታቸዋል። ይህን ጊዜ አባት “ለምን ትመታቸዋለህ?” በሚል ጠይቀው ሳያበቁ በጥይት ጭጭ ያደርጋቸዋል።
ነዋሪዎች እንዳሉት ከግድያው አገዳደሉ የከፋ ነው። ከአገዳደሉም በላይ ደግሞ በአገራቸው፣ በመንደራቸው መሆኑ ጥበሳው ክፉ ነው። አሳዛኙ ኝ ክልሉን እመራለሁ የሚለው ትህነግ ዝምታን መመረጡ ነው።
አዲስ የግንኙነት ፖለቲካ መጫወት የጀመሩት ትህነግና ሻዕቢያ ግድያውን አስመልክቶ ምንም አላሉም። ትንሽ ኮሽ ሲል እየጨማመሩ የሕዝብ መብት ተከላከያ እንደሆኑ የሚገልጹ አክቲቪስትና ሚዲያዎችም ጉዳዩን ከፍትህ አንጻር በሚፈለገው ደረጃ አላስተጋቡም። አንዳንድ ለመቃወም የሞከሩ እንዳሉ ቢታይም እንደተፈለገው አለመሆኑ አስገርሟል።
ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምስክሮችን ጠቅሶ እንዳለው ይህ አባት ላይ የተፈጸመ ግድያና የባለቤቷን አስከሬን ለማንሳት በሞከረች እናት ላይ የተፈጸመው የማቁሰል ወንጀል የተፈጸመው በድንበር ከተማዋ ዛላኣንበሳ ሲሆን፣ በአከባቢው የሚገኘውን ህዝብ ክፉኛ አሰቆጥተዋል።
አርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በኤርትራ ወታደር በሲቪል የዛላንበሳ ነዋሪ ባልና ሚስት የተፈፀመውን ግፍ የሚመለከት መረጃ ይፋ ያደረጉት በፍርሃት ለድህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲገለፅ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪዎች ናቸው።
ግድያውን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በቅርብ ርቀት ሲመለከት የነበረው የህፃናቱ ወላጅ አባት ቀረብ ብሎ ” ልጆቹን ለምን መታሃቸው ?” ብሎ ጠይቆ ሳይጨርስ ነው የሰከረው ወታደር የታጠቀው ሽጉጥ አውጥቶ የተኮሰበት። ወዲያም አባትም ይወድቃል። ይህን ያያች እናት በድንጋጤ እየጮኸች ባልዋ ወደ ወደቀበት ስትጠጋ ወታደሩ እሷም ላይ ተኩሶ ያቆስላታል።
አባት በዛው ቅጸበት ትዳሩንና ልጆቹ በትኖ አለፈ። ይህ ሲሆን ልጆች አይተዋል። የሰከሩ የኤርትራ ወታደሮች አባታቸውን በጥይት ሲገሉ፣ እናታቸውን ሲያቆስሉ ነዋሪዎችና ልጆቻቸው አይተዋል። ይህ እጅግ ከባድ ሃዘን እንደሆነ ያመለከቱ እንዳሉት ወንጀሉ የሚረሳ አይደለም።
” ሌላኛው አብሮ የነበረው ወታደር ጉዳዩን ወታደር ከአረመኔያዊ ተግባሩ ባያስጥለው ኖሮ የጉዳቱ መጠን ካጋጠመው በላይ ይሆን ነበር ” ሲሉ በቅርብ ርቀት ክስተቱን ያዩ የአይን እማኞች ለቲክቫህ ነገረዋል።

