ራሳቸውን በተቃዋሚነት ሰልፍ የሚያስቀምጡ፣ መሳሪያ የታጠቁና ጦርነት ላይ ያሉ፣ በየቀኑ የሚያወጡት መግለጫና መሪዎቻቸው የሚያሰራጩት መረጃ አነጋጋሪ የመሆኑ ጉዳይ የተለመደ ሆኗል። ሰሞኑን ከሲያትል የወጡ መረጃዎች ግን ግራም ያጋቡ ሆነዋል። የፋኖ መሪ እነ ጃዋር በፈጠሩት ህብረት ውስጥ ያሉትንና አሊ ቢራንና ሃጫሉ ሁንዴን ጨምሮ በርካታ የኦሮሞ ዘፋኞችን በጄኖሳይድ በፈረጁ ማግስት፣ ፋኖ ከህብረቱ ጋር እንደሚሰራ በይፋ አስታውቋል።
የቀደመውን በመተው ሰሞኑን የኦሮሞ ምሁራን ነን ያሉ መንግስት ሲወድቅ ምን መደረግ እንዳለበት በቅድመ ዝግጅት አሳብ ሲመክሩ ከተጋበዙት መካከል “ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ ናት። ኦሮሞ ቁጥሩ ከፍተኛ ነው ምንም ግዜ መሪ መሆን አለበት” የሚሉትንና ፍጹም ጽንፍ የረገጠ ጸረ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ሲራመድ መሰማቱ ይታወሳል። እነዚህ ክፍሎች ናቸው ሕብረት መፍጠራቸውን ያስታወቁት።
የዘንድሮ የኢትዮጵያዊያን ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል በተካሄደባት ሲያትል መሰባሰባቸውን ያስታወቁትና ራሳቸውን “የኦሮሞ ምሁራን” በሚል የሚጠሩት እነ ጃዋር መሐመድ፣ ” የኦሮሞ ምሁራና የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እ.ኤ.አ. ህዳር 31 ቀን 2025 በሲያትል: ዋሽንግተን ግዛት በመገናኘት በኦሮሚያ፣ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይትና ትንተና ካደረግን በኋላ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ ተስማምተን ውሳኔዎች ላይ ደርሰናል” ሲሉ በአማርኛ ቋንቋ መግለጫ በትነው ነበር።
ይህንኑ ተከትሎ የጎጃም ፋኖ ከሰሞኑ ፀረ-ብልፅግና ትግል እንደሚያደርጉ ከገለፁ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች በኩል እየተደረገ ያለውን የትብብር መንፈስ እና የጋራ አቋም በመልካም እንደሚያየው ገልጾ፣ ተጨባጭ ትብብር ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የጎጃም ፋኖ አብሮ እንደሚሰራና በመልካም እንደሚያየው በገለጸው ሕብረት ውስጥ ካሉት መካከል በእስር ላይ ያሉት የፋኖ መሪ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ ኃይለማሪያም በጻፉት መጸሃፍ ላይ በጄኖሳይድ ተከሰዋል። በዚሁ ሲያትል ስፖርት ፊስትቫል ላይ ለሽያጭ በቀረበው “የነጻነት ሰልፍ” የተሰኘው መጽሃፍ ውስጥ በጄኖሳይድ ተፈርጀው “ለታሪክና ለፍርድ” ከቀረቡት መካከል ጃዋር መሀመድ፣ ጸጋዬ አራርሳ፣ ሕዝቅኤል ገቢሳ፣ ብርሃነ መስቀል ሰኚ … እንዲሁም ከጎን ከመጽሃፉ ገጽ 178 ላይ የሰፈሩት ይገኝበታል።
የመጽሐፉ ደራሲ “የአማራን ሕዝብ ተናበውና ተቀናጅተው ጂኖሳይድ እንዲፈጸምበት ያስቻሉ” ሲሉ የከሰሱት ከላይ በመጽሐፉ ገጽ 178 ላይ የተገለጹትን ብቻ ሳይሆን ታዋቂ የኦሮሞ አቀንቃኞችና አክቲቪስቶችና ጸሃፊዎችንም ዘርዝሯል። ሚዲያዎችንም ለቅሞ አስቀምጧል። መጽሃፉ እንደዘረዘረው ሀጫሉ ሁንዴሳ፣ አሊ ቢራ፣ ታደሰ ገመቹ፣ ቻላ ቡልቱሜ፣ አንዷለም ጎሳ፣ ጋላና ጋሮምሳ፣ ኢቲቃ ተፈሪ፣ ጸጋዬ ደንደና፣ ዩሰን ጌታሁን … አማራን በማጥፋት ተግባር ላይ መሳተፋቸውን ያትታል።
የአማራ ፋኖ መሪ የሆኑት ዶክተር ወንዶሰን በመጽሃፉቸው አማራን በማጥፋት በጄኖሳይድ ከከሰሷቸው መካከል ስዩም ተሾመ፣ ኢያስፔድ ተስፋዬ፣ ብርሃኒ ሌንጂሶ፣ ቤተልሄም ታፈሰ ጨምሮ አብበ ቶላ፣ መስፍን ፈያሳ፣ አፈንዲ መተቂ፣ ደረጀ ገረፋ፣ አሕመዲን ጀበል ወዘተ በፎቶ የተዘረዘሩት ከአፈንዲ በስተቀር ይህ እስከተጻፈ ድረስ ምላሽ አልሰጡም።
“እኔ አፈንዲ ለአማራ ሕዝብ ጥላቻ ቢኖረኝ ኖሮ በአማርኛ ቋንቋ መጻፍን የመጀመሪያ ምርጫዬ አላደርግም ነበር። አዎን! በአምስት ቋንቋ መጻፍና ማንበብ ብችልም ዘወትር እየጻፍኩ ያለሁት በአማርኛ ነው (ለሚገባው ሰው ይህ ነጥብ ብቻውን ብዙ ነገር ይናገራል)” ሲል በፊስ ቡክ ገጹ ጽፏል።
አፈንዲ እክለውም “የኔው እንኳ እዳው ገብስ ነው። አሁን በህይወት የሌሉት ተወዳጅ አርቲስቶች “ዓሊ ቢራ” እና “ሃጫሉ ሁንዴሳ” ጭምር የዘር ፍጅቱን የመሩ ተብለው በሰንጠረዡ ላይ ተጽፈዋል” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ፋኖ በጎጃም “የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች በኩል እየተደረገ ያለውን የትብብር መንፈስ እና የጋራ አቋም በመልካም የምናየው መሆኑን እናሳውቃለን” ሲል ለወዳጆቹና ደጋፊዎቹ በመግለጫ አስታውቋቸዋል።
ከዚህ ቀደም በጸብ ተለያይተው የነበሩት የኦሮሞ ምሁራኖች ሚና ለይተው አንዱ ሌላውን ሲያወግዝ እንደነበር ይታወሳል። በተለይም ጃዋር መሐመድ አዲስ አበባ ከገባ በሁዋላ ክህደት እንደፈጸመ በመጥቀስ መጽሐፍ ሲያሳትም በዘመቻ ሲያወግዙት እንደነበር አይዘነጋም። ከመካከላቸው ኢትዮጵያን በኢምፓየርነት የሚከሱ፣ በቅኝ ግዢ መያዛቸውን በመግልጽ በቀርቡ በዙም ባካሄዱት ስብሰባ ሳይቀር ይህንኑ አቋማቸውን ሲገልጹ የነበሩት ኃይሎች ናቸው ሲያትል ተሰብስበው ህብረት ፈጠርን ያሉት።
ይህንኑ ሕብረት ተከትሎ የጎጃም ፋኖ ባወጣው መግለጫ መንግስትን “አብይ አሕመድ” በማለት ጠርቶ እንዳለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች መንግስትን ለማስወገድ ትብብር ማድረግ እንዳለባቸዉ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የገለጸውና እና አቋም የያዝንበት ጉዳይ ነበር” ሲል ቀደም ሲል ጀምረው የተዘጋጁበት ጉዳይ እንደሆነ መግለጻቸው የእነ ጃዋር ሕብረት ሲያትል ሲመሰረት እዚያው ሲያትል ይፋ በሆነው የፋኖ መሪ መጹሐፍ ጋር የሚጣረስ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች እየገለጹ ነው።
ሕብረቱም ሆነ መጽሐፉ ገበያ ላይ ሳይውል፣ “ጦርነት ያብቃ፣ አገዛዝ ይወገድ” በሚል የተሳተፉና የተገኙበት ውይይት ስህተትና ውሸት የተቀላቀለበት መሆኑን ገልጸው ለኢትዮሪቪው መረጃ የሰጡ ጠቅሰን እንዳልነው የኦሮሞ ሕብረት ከዋናው አብሮነት እንዲገነጠል የተወሰነው በስፖንሰር አድራጊዎቹ ዕቅድ መሰረት እንደሆነ አስታወቀን ነበር።

በዚሁ መረጃ መሰረት የኦሮሞ ሕብረት ብቻውን እንዲወጣ የተደረገው “በኦሮሚያ ሕዝብ ሊነሳ አልቻለም” በሚል ድምጋሜ ነው። ኢትዮጵያን ለማወክ በተለያዩ አግባቦች እጃቸውን ወደ ኢትዮጵያ “በኢትዮጵያዊያን” በኩል ያስገቡ አካላት ዋና አላማቸው ኢትዮጵያ ተተራምሳ በጎበዝ አለቆች እንድትመራና እንድትፈርስ እንደሆነ መረጃውን ያካፈሉን አስታወቀው ነበር። ሃያ አንድ ድርጅቶች ያሉበት የማይቆም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ማደረጃት ቀጣዩ አጀንዳ ሲሆን ድርጅቶቹና መሪዎቹ በፍጹም ሊግባቡ የማይችሉ መሆናቸውን እነዚሁ ወገኖች በወቅቱ አስታውቀዋል።
“የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች (ኦነግ-ኦነሠ፣ ኦፌኮ እና ኦነግ) አስፈላጊውን ለውጥ ለማምጣትና መጪውን ሽግግር ስኬታማ ለማድረግ በተደራጀ መንገድ የሚየደርጉትን እንቅስቃሴ በሁሉም ዘርፍ ለመደገፍ ተስማምተናል” ያለውና ጃዋር ያሰራጨው የሲያትል መገለጫ፣ በኦነግ ሸኔነት የሚታወቀውን ኦነግ፣ ከኦነሠ ጋር አንድ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።
“አማራ ተፈናቀለ፣ በጅምላ ተገደለ” በሚል ጠብመንጃ ያነሳው ፋኖ በዋናነት ሲከሰው የነበረው ኦነግ ሸኔን በገሃድ እንደሚደግፍ ይፋ ያደረገውን የኦሮሞ ምሁራን ህብረት እንደሚደግፍና አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ “ጠብ መንጃ አነሳሁበት ያለውን ጉዳይ በምን መልኩ ከኦነግ ሸኔ ጋር ይቋጫል? ወይም ቁጭቷል” ሲሉ ደጋፊዎቹ ሳይቀሩ እየጠየቁ ነው።
ፋኖም ሆነ የኦሮሞ ምሁራን ህብረት ፈጠርን ያሉት አካላት ያወጡት መግለጫ በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለይቶ የሚኮንንና ከስልጣን ለማስወገድ ደጋግሞ የሚያወግዝ በመሆኑ ተመሳሳይ ነው። በተመሳሳይ እንደ አዲስ የተሰራውን የኢትዮጵያን መከላከያ፣ አየር ኃይል፣ ባህር ኃይልና ጥቅል ተቋሙን “የአብይ፣ የብልጽግና፣ የብረሃኑ ጁላ” በማለት ቀደም ሲል “የደርግ” ተብሎ ተፈርጆ እንደፈረሰው የኢትዮጵያን ጦር ኃይል እንደሚፈርስ እነዚሁ ወገኖች ሌላው አንድ የሚያደራጋቸው አሳብ ነው።



