ቪኦኢ ዜና | Addis Ababa | July 30, 2026 ራሱን የትግራይ የሰላም ኃይሎች ብሎ የሚጠራው ቡድን ትህነግን ከመቀሌ በማስወጣት ከተማዋን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አጠቃላይ ዝግጅት ማጠናቀቁን የቡድኑ ወታደራዊ አዛዥ ለአዲስ ሪፖርተር ገለጹ። ይህ የተሰማው ከትህነግ መውደቅ በኋላ በትግራይ ስለሚከናወነው የመንግስት አወቃቀር ቅድም ዝግጅት መደረጉ ይፋ ከሆነ አንድ ቀን በኋላ ነው።
በቀድሞ የትሕነግ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች በወዲ አንጥሮ፣ በጀነራል ጉዕሽ ገብረ እና በጀነራል ከበደ ፍቃዱ የሚመራው ይህ የሰላም ኃይል፣ መቀሌ መሽጎ የትግራይን ህዝብ እያሰቃየ ያለውን የትሕነግ አንድ ሽራፊ ስብስብ ጠራርጎ በማስወጣት ለትግራይ ህዝብ ሰላምና ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ ሙሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አዛዡ አስታውቀዋል።
ወታደራዊ አዛዡ ለአዲስ ሪፖርተር እንደተናገሩት፣ እስካሁን ባለው መረጃ በማንኛውም ሰዓት የሚሰጠውን ግዳጅ በአግባቡ መወጣት የሚችሉ በርካታ ታጣቂዎች ትሕነግን በመክዳት ወደ ሓራ መሬት በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ።
ይህ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ የትሕነግን መዋቅር ከውስጥም ከውጭም በቀላሉ በጣጥሶ ለመጣል እና ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከትግራይ ምድር ለማስወገድ ምቹ መደላደል የሚፈጥር መሆኑንም አዛዡ አክለው ገልጸዋል። ኦፕሬሽኑ መቼና እንዴት እንደሚጀመር ይፋ ባያደርጉም በመቀለ መንግስት በኃይል ገልብጦ ሕዝብ እያሰቃየ እንደሆነ የገለጹት ስብስብ ከአሁን በኋላ ብዙም እድሜ አይኖረውም።
ከትሕነግ መወገድ በኋላ በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ቅድሚያ የሚሰጣቸው 9 ዋና ዋና መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ተግባራት በዝርዝር መገለጻቸው የሚታወስ ነው።
የፕሪቶሪያን ስምምነት መሠረት በማድረግ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ማቋቋምና የትሕነግን ታጣቂዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ DDR ማስፈጸም የድህረ-ትሕነግ ዋና ዋና ትኩረቶች ሲሆኑ፣ ከትሕነግ ውድቀት ማግስት የትግራይን ሕዝብ ወደ ቀደሞው የማምረት ተግባር ለመመለስና የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን ለማደስ የታቀዱ መዋቅራዊ አቅጣጫዎችም ይፋ ሆኗል
በተጨማሪም ቡድኑ በየቦታው የዘራውን ከፍተኛ የጦር መሣሪያ በመሰብሰብ በክልሉ ሊከሰት የሚችልን ሥርዓት አልበኝነት መከላከል፣ በየምሽጉ የተበተኑትንና በሱዳን የእርስበርስ ጦርነት ያሰማራቸውን ታጣቂዎች ወደ አንድ ማዕከል በማሰባሰብ የDDR ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ሕብረተሰቡ የመቀላቀል ሂደት መፈጸም ለሕግና ሥርዓት መከበር ወሳኝ እንደሆነ ተብራርቷል።
በሌላ በኩል ከትሕነግ ውድቀት ማግስት የትግራይን ሕዝብ ወደ ቀደመ የምርት ተግባር ለመመለስና የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን ለማደስ የታቀዱ መዋቅራዊ አቅጣጫዎች ይፋ ሆነዋል።
በዚህም መሠረት በየመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን በአፋጣኝ ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለስ፣ ሕዝቡን ወደ አምራችነት በማሸጋገር የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መጠገንና ክልሉ ከአዲሱ የቀይ ባሕር የኢኮኖሚ አውታር የላቀ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት ከተቀመጡት ነጥቦች መካከል ይገኙበታል ተብሏል።
በመጨረሻም በሕዝቡ ላይ ሰቆቃ ፈጽመዋል የተባሉ ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ እና ከአዋሳኝ ክልሎች በተለይም ከአማራ ክልል ጋር ያሉ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን በሀገራዊ ምክክርና በሕገ-መንግሥታዊ አሠራር የዜጎችን ፍላጎት ባከበረ መልኩ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ትኩረት የተሰጣቸው አቅጣጫዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ይህ ይፋ በሆነ ማግስት የትግራይ የሰላም ኃይል ብሎ የሚጠራው ቡድን ትህነግን ከመቀሌ በማስወጣት ከተማዋን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አጠቃላይ ዝግጅት ማጠናቀቁን የቡድኑ ወታደራዊ አዛዥ መናገራቸው ዜናውን ተመጋጋቢ አድርጎታል።
የትግራይ ህዝብ፣ በተለይም ወጣቶች በክልሉ ያለውን አፈሳ እና የግዳጅ ምልመላ በመቃወም ትግራይን ጥለው መሸሻቸው፣ መሸሽ ያልቻሉ ለሊት በረሃ እየወጡ በማደር ራሳቸውን እየሸሸጉ ያለበት ሁኔታ የፈጠረው ዓለም ዓቀፍና የውስጥ ተቃውሞ በበረታበት በአሁኑ ወቅት የተሰማው ዜና በበርካታ ሰላም ወዳዶች ዘንዳ ተስፋን ያጫረ ሆኗል።

