VOE OPINION | ADDIS ABABA | July 31, 2026 – በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት ከሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ በይፋ የተጀመረውና በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ የሚገኘው አገር አቀፍ የውይይት መድረክ፣ በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እጅግ ወሳኝና አዲስ ምዕራፍ ከፋች ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል። ለአገራቸው ቀና የሚያስቡ “ዳግማዊ አደዋ” እያሉትም ነው።
ለዘመናት የዘለቁ፣ ሀገራዊ አንድነትንና የሕዝቦችን አብሮነት ሲፈታተኑ የቆዩ፣ እንዲያውም ለበርካታ ደም አፍሳሽ ግጭቶችና የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የሆኑ መሠረታዊ ጥያቄዎች በሰለጠነ መንገድ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ እና በሕዝብ ተወካዮች አማካኝነት በይፋ እንዲዳሰሱ መደረጉ እንደ ትልቅ ታሪካዊ እጥፋት የሚወሰድ ነው ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ በላይ ተወካዮች በ80 ንዑስ ቡድኖች ተከፋፍለው በውይይት ላይ ከሚገኙባቸው 8 ዋና ዋና አገራዊ አጀንዳዎች መካከል የፖለቲካ ሥርዓት፣ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ እና ብሔራዊ ምልክቶች” የሚለው አርእስት ዋናውና ከፍተኛ የሃሳብ መፋጨት የሚታይበት ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል።
በዚህ ሥር በዋናነት ቀርበው ክርክር እየተደረገባቸው ያሉትን ሦስት አበይት ጉዳዮች ማለትም፤ የመጀመሪያው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 39 እና የብሔር-ብሔረሰቦች መብት ሲሆን፣ የዚህ ድንጋጌ አስፈላጊነት፣ አተገባበር እና በሀገራዊ አንድነት ላይ ያለው ተፅዕኖ በጥልቀት እየተገመገመ ይገኛል። ይህ ኢትዮጵያን ሰላም የነሳ አንቀጽ እጣ ፈንታውን ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀው ቢሆንም “አብረነው እንቀበር” የሚሉ ጥቂት የቀደመው አመለካከት ውጤቶች መንገራገጭ አየፈጠሩ ነው።
ሁለተኛው አጀንዳ ሀገሪቱ ወደፊት በምን ዓይነት የመንግሥት መዋቅር ብትመራ የተሻለ አገራዊ መረጋጋትና ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል ማምጣት ይቻላል በሚለው ዙሪያ የአሁኑን ፓርላማዊ ሥርዓት ማስቀጠል ወይስ ወደ ጠንካራ ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት መቀየር የተሻለ እንደሆነ የሚደረገው ክርክር ነው።
ሦስተኛው ደግሞ የሀገሪቱ የጋራ መታወቂያ የሆኑት ብሔራዊ ምልክቶች በተለይም በባንዲራው ላይ ያለው አርማና ተያያዥ ምልክቶች የሁሉንም አካላት ማንነትና ታሪክ በትክክል ይወክላሉ ወይስ ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል የሚለው ነጥብ ይጠቀሳል። የአዲስ አበባም ጉዳይ እንዲሁ የሚጠበቅ ነው።
እነዚህ አጀንዳዎች የሀገሪቱን የወደፊት ህልውናና የፖለቲካ ካርታ የሚወስኑ በመሆናቸው፣ በሁለት ተቃራኒና የካረሩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች መካከል የሚደረጉት ክርክሮች እጅግ የጠበቁ ናቸው።
በአንቀጽ 39 በኩል የፌዴራሊስትና የማንነት ፖለቲካ አቀንቃኞች ድንጋጌው ለዘመናት የተካሄደ የትግል ውጤት፣ የመብቶች ሁሉ ማረጋገጫና የአብሮነት ዋስትና በመሆኑ ሊነካ አይገባም ሲሉ ይከራከራሉ።
በአንፃሩ የሀገራዊ አንድነትና የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች ይህ አንቀጽ ሀገርን ለቋሚ ክፍፍልና ለብሔር ግጭት የሚዳርግ የመፈራረስ የጊዜ ቦምብ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ወይም ወደ አካባቢ አስተዳደርና ባህላዊ መብቶች ብቻ እንዲቀየር ይግፋሉ።
በመንግሥት ቅርጽ በኩልም የፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት ደጋፊዎች አሁን ያለውን የጸጥታና የፖለቲካ አለመረጋጋት ለመግታት ጠንካራና ፈጣን ውሳኔ የሚሰጥ አስፈጻሚ አካል ያስፈልጋል ሲሉ፣ የፓርላማዊ ሥርዓት ደጋፊዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ስብጥር ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት ወደ አምባገነንነት ሊያመራ ስለሚችል የሥልጣን መጋራትና ብዝሃነትን የሚያስተናግደው ፓርላማዊ ሥርዓት ተሻሽሎ መቀጠል አለበት የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።
በባንዲራውና ምልክቶቹ ዙሪያም የነባሩ ባንዲራ ደጋፊዎች አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ አላማ ያለ ምንም አርማ የረጅም ዘመን የነጻነትና የጋራ መስዋዕትነት ምልክታችን ነው በሚሉበት ወቅት፣ የአሁኑ አርማ ደጋፊዎች ደግሞ አርማው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእኩልነት መግለጫ በመሆኑ ሊቀጥል ወይም ሁሉንም የሚያስማማ አዲስ ምልክት ሊቀረጽ ይገባል የሚል ተቃራኒ ሃሳብ ያንጸባርቃሉ።
ኮሚሽኑ ባወጣው የሕግ ማዕቀፍ መሠረት በማንኛውም አጀንዳ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ከ70 እስከ 75 በመቶ የሚሆን የተሳታፊዎች ስምምነት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በእነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ በውይይት መግባባት ላይ መድረስ ካልተቻለ ግን ጉዳዩ በቀጥታ ወደ አጠቃላይ ሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ተመርቶ በሕዝብ ድምፅ እንዲወሰን ይደረጋል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በሐምሌ 22 ቀን በሰጡት መግለጫ እንዳረጋገጡት፣ እስካሁን ድረስ በምንም አጀንዳ ላይ የተደረሰ የጋራ ስምምነት ወይም የተወሰነ የመጨረሻ ውሳኔ ሳይኖር ሂደቱ የሃሳብ ልዩነቶችን የማቀራረብ ምዕራፍ ላይ ብቻ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይቱን መቀላቀላቸውና ኮሚሽኑ አሁንም ቢሆን ከመሣሪያ ያነገቡ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ውይይት በማድረግ ወደ ምክክሩ ለማስገባት ጥረቱን እንደሚቀጥል ማስታወቁ ሂደቱን የበለጠ አሳታፊ የሚያደርግ አወንታዊ እርምጃ ነው።
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 39፣ በመንግሥት ቅርጽ እና በብሔራዊ ምልክቶች ዙሪያ የሚታዩት ተቃራኒ ሃሳቦች ከ70 እስከ 75 በመቶ ስምምነት ካልተገኘባቸው በቀጥታ ወደ ህዝበ ውሳኔ የሚያመሩ በመሆናቸው፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የመወሰኑ ድምፅ በመጨረሻም ወደ መላው ሕዝብ ሊመለስ እንደሚችል ይጠበቃል። ኮሚሽኑ በሚወጡ አዳዲስ የውይይት መርሃ-ግብሮችና መረጃዎች ላይ የሚያደርጋቸውን ሂደቶች እየተከታተልን ለእናንተ ለማድረስ ዝግጁ ነን።

