ቪኦኤ – በዲፕሎማሲ የሚመለሰው መብት፡ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ
የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ከቀይ ባሕር እና ከአፍሪካ ቀንድ የባሕር ዳርቻዎች ጋር የተሳሰረ ለመሆኑ ታሪክ ይመሰክራል።
በጥንትና በመካከለኛው ዘመን የነበሩት የሀገር ውስጥ ታሪካዊ ሱልጣኔቶችና መንግሥታት የዘይላ፣ የምጽዋ፣ የታጁራ እና የበረበራ ወደቦችን የኢትዮጵያ የሕይወት እስትንፋስ አድርገው ተጠቅመውባቸዋል።
ይሁንና ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የተፈጥሮ ሕግን እና ታሪካዊ እውነታን በተጻረረ መልኩ በተፈፀመ ከባድ ፖለቲካዊ ሴራ፣ ኢትዮጵያ ያለ አግባብ ባሕር በር አልባ እንድትሆን ተደርጋለች።
ይህ ክስተት የሺህ ዓመታት የታሪክ፣ የባህል እና የደም ትስስርን የካደ አሳዛኝ ስብራት ከመሆኑም በላይ፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትንና በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች ሀገርን የኢኮኖሚ አንገት ያነቀ ክስተት ሆኗል።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የምታነሳው የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ወይም የሌሎችን ሉዓላዊነት የመጋፋት ፍላጎት ሳይሆን የሀገር ሕልውና ጉዳይ እንዲሁም ፍጹም ታሪካዊና ሕጋዊ የሆነ መብትን የማስከበር አጀንዳ ነው።
በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግጋት እና በተባበሩት መንግሥታት ድንጋጌዎች መሠረትም ቢሆን፣ ባሕር በር አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስ ሕጋዊ መብት ያላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ጥያቄም ከዚህ ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ እና ከተፈጥሯዊ ፍትሕ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።
መላው የገቢ እና ወጪ ንግዷ፣ ደህንነቷ እና የነገ ተስፋዋ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ታንቆ እንዲኖር መፍቀድ በየትኛውም የሞራል፣ የሕግ እና የፍትሕ ሚዛን ተቀባይነት የለውም።
ጉዳዩን ከዓለም አቀፍ ጂኦ-ፖለቲካዊ ስሌት አኳያ ስንመለከተውም፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለቀይ ባሕር ቀጣና መረጋጋት እና ደህንነት ወሳኝ ነው።
ቀይ ባሕር የዓለም አቀፍ ንግድ የደም ሥር በሆነበት በዚህ ዘመን ቀጣናው ከሚያስተናግደው የጸጥታ ስጋት አንጻር ኢትዮጵያ የራሷን እና የቀጣናውን ደህንነት የማስጠበቅ ታሪካዊ ሀላፊነት አለባት።
ስለዚህ የባሕር በር ጥያቄያችን ለንግድ ሸቀጥ ማስተላለፊያ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የኢኮኖሚና የደህንነት ሚዛን ጠብቃ እንድትዘልቅ የሚያስችላት ወሳኝ የስትራቴጂ አቅም ነው።
አሁን እየተሄደበት ያለው የዲፕሎማሲ መንገድም የጥንቶቹ ወራሪዎች የጉልበት መንገድ ሳይሆን የዘመናዊው ዓለም የሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫና ቀጣናዊ ትስስርን መሠረት ያደረገ በጋራ የማደግ ራዕይ ነው።
ይህን ፍትሐዊ ጥያቄ ማስመለስ ማለት ለቀጣዩ ትውልድ በራሷ የምትተማመን፣ የኢኮኖሚ ዋስትናዋ የተረጋገጠ እና የተከበረች ሀገር ማውረስ ማለት ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ታሪክ ያለ ጠረፎቿና የንግድ መስመሮቿ ሊነገር ፈጽሞ እንደማይችል ሁሉ፣ የሀገራችን የነገ ብሩህ ተስፋና የተሟላ ሉዓላዊነትም ከተፈጥሯዊ የባሕር በሯ ውጭ ሙሉ ሊሆን አይችልም።
በመሆኑም ዛሬ የምንጠይቀው የባሕር በር አባቶቻችን በደምና በአጥንት ተከላክለው ያቆዩንን ታሪካዊ አደራ ለማደስ፣ የተቆረጠውን የታሪክ እምብርት ለመጠገን እና እንደ ሀገር በጽናት የመቀጠል የሕልውና መሠረታችንን ለማረጋገጥ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

