ይህ የአሜሪካ እና የቻይና ድብቅና ግልጽ ፉክክር ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ እምብርት በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንጸባረቀ ይገኛል። ቻይና በታላላቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ዲጅታል መሰረተ ልማት፣ በብድርና በኢንዱስትሪ ፓርኮች በኩል የኢኮኖሚ የበላይነቱን ስትይዝ፤ አሜሪካ በበኩሏ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት (IMF እና የዓለም ባንክ)፣ በፀጥታ አቅርቦት፣ ከእርዳታ ይልቅ በልማት ትብብርና በዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች አማካኝነት የበላይነት ለማስከበር ትጥራለች። ትራምፕ ወደ ቻይና ከማቅናቱ በፊት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ወደ አሜሪካ አቅንቶ ከአቻው ከማርኮሮብዮ ጋር እንዲገናኝ የተደረገው ለምን ይመስላችኋል? ይህ ፍልሚያ ለአገራችን ብሔራዊ ጥቅም (ደህንነት፣ ብልጽግና እና ነፃነት) አደጋዎችንና ዕድሎችን በአንድነት ይዞ የመጣ በመሆኑ፣ ጉዳዩን በጥልቀት መረዳት የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የቤት ሥራ ነው።
በList Fredrick ተጻፈ
ባለፈው ሳምንት ትራምፕና ፑቲን ወደ ቤጂንግ አቅንተው ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት አልተከታተልኩም ነበር። ትላንትና ዛሬ መረጃዎችን ቃርሜ የጉብኝቱን አንድምታ ለመረዳት ጥረት አድርጌያለሁ። እጅግ የገረመኝ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የጥንታዊ ግሪክ የታሪክ ጸሐፊ የሆነውን የቱሲዲደስን የታሪክ ዘገባዎች ደጋግመው ማንሳታቸው ነው።
ዢ ዓለም በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ሕግጋት እየፈረሱ ወደሚሄዱበት “የሕገ አራዊት ሥርዓት” ( Law Of the Jungle) እያመራች እንደሆነና ዋሽንግተንና ቤጂንግ የ“ቱሲዲደስ ወጥመድ” (Thucydides Trap) ሰለባ እንዳይሆኑ አስጠንቅቀዋል። ይህ ወጥመድ ቱሲድደስ እያደገች የነበረችው አቴንስና እና የራሷን ስርዓት ዘርግታ የበላይ የነበረችው ስፓርታ መካከል የተከሰተውን ጦርት መነሻ በማድረግ ወደ ልዕለ ሃያልነት እያደገ ያለ ሃገር እና የነባሩ ስርዓት ባለቤት ሃገር (Established Hegemony) መካከል ባለው ግንኙነት የኋለኛው በፊተኛው እድገት ስጋትና ፍራቻ ውስጥ ስለሚወድቅ ግዴታ ወደ ጦርነት ያመራሉ የሚል ነው።
ምንም እንኳን የጂኦፖለቲካ ተንታኞች ቻይና እና አሜሪካ ቱሲድድስ ወጥመድ ውስጥ ገብተው የግድ ወደ ቀጥተኛ ወታደራዊ ጦርነት ያመራል በሚለው ላይ ሙሉ ስምምነት ባይኖራቸውም፣ ዓለም አዲስና ውስብስብ ወደሆነ የኃይል ሚዛን መሸጋገሯን ግን አይክዱም። በአሁኑ ወቅት ውድድሩ ከመደበኛ ጦርነት በታች ባሉ አውድማዎች (Below the threshold of conventional war) ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ፍልሚያ በሳይበር መረጃ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን (እንደ 5G)፣ በሴሚኮንዳክተር ቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ ማዕቀቦች፣ በንግድ ታሪፍ፣ በዲፕሎማሲ፣ በህቡዕ ግዳጆች( Covert Ops) በውክልና ጦርነት እና የባህር የንግድ መስመሮችን በመቆጣጠር የበላይነት ዙሪያ የሚሽከረከር ሲሆን፣ አንዱ የሌላውን ተጽዕኖ ለመቀነስ አገራትን በውዴታም ሆነ በግዴታ (Accommodation and Coercion) ወደ ራሱ ጎራ ለመሳብ የሚደረግ ስልትን ያጠቃልላል። ሁለተም ሃገራት በእጃቸው ያለውን ብሄራዊ የተፅዕኖ መሳሪያዎች ተጠቅመው ጥቅማቸውን ለማስከበር ከመቸውም ጊዜ የበለጠ ብርቱ ጥረት የሚያደርጉበት ነው። አንዳንዶች ይህን ዘመን The weaponisation of Everything ብለው ይጠሩታል።
ኢትዮጵያ እንደ ፍልሚያ አውድማ…
ይህ የአሜሪካ እና የቻይና ድብቅና ግልጽ ፉክክር ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ እምብርት በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንጸባረቀ ይገኛል። ቻይና በታላላቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ዲጅታል መሰረተ ልማት፣ በብድርና በኢንዱስትሪ ፓርኮች በኩል የኢኮኖሚ የበላይነቱን ስትይዝ፤ አሜሪካ በበኩሏ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት (IMF እና የዓለም ባንክ)፣ በፀጥታ አቅርቦት፣ ከእርዳታ ይልቅ በልማት ትብብርና በዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች አማካኝነት የበላይነት ለማስከበር ትጥራለች። ትራምፕ ወደ ቻይና ከማቅናቱ በፊት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ወደ አሜሪካ አቅንቶ ከአቻው ከማርኮሮብዮ ጋር እንዲገናኝ የተደረገው ለምን ይመስላችኋል? ይህ ፍልሚያ ለአገራችን ብሔራዊ ጥቅም (ደህንነት፣ ብልጽግና እና ነፃነት) አደጋዎችንና ዕድሎችን በአንድነት ይዞ የመጣ በመሆኑ፣ ጉዳዩን በጥልቀት መረዳት የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የቤት ሥራ ነው።
ይህንን አዲስ ፉክክር በአግባቡ ለመወጣት፣
የመንግስት ሚና..
በመጀመሪያው ቀዝቃዛ ጦርነት ወቅት (በአሜሪካ እና በሶቭየት ኅብረት መካከል በነበረው ፍልሚያ) የደረሰብንን ጠባሳና ያገኘነውን ትምህርት ማስታወስ ይገባል። በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት (ደርግ) ከአሜሪካ አጋርነት ወጥቶ ሙሉ በሙሉ ወደ ሶቭየት ኅብረት በማዞሩ፣ አገሪቱ የሁለቱ ኃያላን የውክልና ጦርነት (Proxy War) መፋለሚያ አውድማ ሆና ነበር። በወቅቱ ከሶቭየት ኅብረት የተገኘው ዘመናዊ መሣሪያ የሶማሊያን ወረራ ለመቀልበስ ቢረዳም፣ በረጅም ጊዜው ግን አገሪቱን ለከፋ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ለኢኮኖሚ ውድቀት እና ለሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለም ግትርነት አጋልጦ በመጨረሻም ለሥርዓቱ መፈራረስና ለአገር መዳከም ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። ጦሱ እስካሁን እለቀቀንም።
ከዚህ መራራ የታሪክ እውነት የምንማረው፣ በአዲሱ የኃይል ሚዛን ውስጥ የአንዱ ወገን ፍጹም ጥገኛ መሆን አውዳሚ መሆኑን ነው። ስለዚህ፣ የመጀመሪያውና ዋነኛው ኃላፊነት የሚወድቀው በገዥው ፓርቲና በመንግሥት አካላት ላይ ነው። መንግሥት የአገሪቱን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የ“ነፃና ሚዛናዊ” ገቢርነበብ ዲፕሎማሲ (Pragmatic Non-Alignment) መከተል አለበት። ከአንዱ ጋር የስትራቴጂክ መሠረተ ልማት አጋርነት ሲፈጥር፣ ከሌላኛው ጋር ደግሞ የፀጥታ፣ የንግድና የፋይናንስ ትብብሩን ሳያቋርጥ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም ማዕከል ያደረገ ስልጡን የዲፕሎማሲ ጨዋታ መጫወትና በአገር ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን በአንድ ሃገር ልጅነት በትብብርና በውይይት በመፍታት አንድነትን ማጠንከር ይጠበቅበታል።
የአሰላሳዬች ሚና…
በሌላ በኩል፣ የአገሪቱ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና የምርምር ተቋማት የልዕለ ኃያላኑን እንቅስቃሴ በንቃት በመከታተል ለመንግሥትና ለሕዝብ ስትራቴጂካዊ አማራጮችን ማመንጨት ይኖርባቸዋል። እነዚህ ተቋማት ቻይና እና አሜሪካ የሚያወጧቸውን የፖሊሲ አቅጣጫዎች አስቀድመው በመተንተን፣ ኢትዮጵያ እንዴት በሁለቱ መካከለኛ መስመር ላይ ተጉዛ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር እንደምትችል የምክር አገልግሎት የመስጠትና የማንቃት ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው። ጉዳዩን እንደ ተራ የውጭ ዜና ከመመልከት ወጥተው፣ የአገር ደህንነት ስጋትነቱንና ዕድሉን በጥናት ሊያሳዩ ይገባል።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች…
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸውም ቢሆኑ፣ የዚህ ፉክክር ዋነኛ ኢላማዎች መሆናቸውን ከአሁኑ ቀድመው ማወቅና ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው። በብሔራዊ ጥቅም፣ በድንበር ሉዓላዊነትና በውጭ ተጽዕኖ ጉዳዮች ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን አቁመው የጋራ አቋም መያዝ መቻል አለባቸው። የውጭ ኃይሎች የአገር ውስጥ የፖለቲካ ክፍተቶችን ተጠቅመው አገሪቱን የሁከት ቀጠና እንዳያደርጓት፣ ተቃዋሚዎች የበሰለና ለአገር ቅድሚያ የሚሰጥ የፖለቲካ ባህል ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ…
የንግዱ ማኅበረሰቡና ነጋዴዎች ደግሞ የዚህ ፉክክር ቀጥተኛ ተዋናዮችና ተጽዕኖ አራጋቢዎች ናቸው። የቻይናን የኢንዱስትሪና የአቅርቦት ሰንሰለት (Supply Chain) ዕድሎች በሚገባ እየተጠቀሙ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙትን የነፃ ገበያ እድሎችን (እንደ AGOA ይሉትን) እና የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን ለመጠቀም መሥራት ይኖርባቸዋል። እንዲሁም የንግዱን የአቅርቦት ሰንሰለት በአንድ ወገን ብቻ ከማንጠልጠልና ለጥቃት ተጋላጭ ከመሆን ወጥተው፣ ዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለታቸውን ማስፋት ወይም ማብዛት (Diversification of supply chain) ይግባል። ከቻይና የምናስገባውን ምርት ከህንድ፣ ከቬትናም፣ እና ከሌሎች የኤዥያ አገሮች ለማስገበት ጥረት ማድርግ፣ አማራጮችን መፈለግ ለነገ የማይተው ጉዳይ ነው።
እንዲሁም ገቢ እቃዎችን ወይም ምርተችን በውስጥ አምራችነት አቅምን በማሳደግ (Import substitution) የውጭ የኢኮኖሚ ጫናዎችን መቋቋም የሚችሉበትን አቅም መገንባት አለባቸው። መንግስትም በድጎማ ማበረታታት ይገባዋል። በአጠቃላይ ዘመኑ የንግድ ግንኙነትና ጥገኝነትን ወደ ጦር መሳሪያነት የሚቀየርበት መሆኑን ተረድቶ ስጋት ለመለየትና ጉዳትን ለመቀነስ ነቅቶ የሚጠበቅበት መሆኑን መረዳት ይገባል- ሳያንቀላፉ ንቅተው መተኛት ይገባል።
መገናኛ ብዙሃን…
ሲቪል ማኅበራትና የመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያዎች) በአዲሱ የኃይል ሚዛን ውስጥ የሕዝብን ግንዛቤ የማሳደግና አገር በቀል አጀንዳዎችን የመቅረጽ ሚና አላቸው። ሚዲያዎች የልዕለ ኃያላኑን የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ሳያስተጋቡ፣ የራሳችንን አገራዊ የወል ትርክት (National Narrative) መገንባትና ማኅበረሰቡ የውጭ ጫናዎችን የሚመክትበትን ንቃት መፍጠር አለባቸው። ሲቪል ማኅበራትም ቢሆኑ ከውጭ ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ፍላጎት ተነስተው የሌሎች አገራትን አጀንዳ አስፈጻሚ ከመሆን ተቆጥበው፣ ለአገር በቀል ሰላምና ልማት መቆም ይኖርባቸዋል።
እንደ ማመውጫ..
የቻይናው መሪ ያሰሙት ማስጠንቀቂያና የ“ቱሲዲደስ ወጥመድ” ስጋት ለኢትዮጵያ ትልቅ የማንቂያ ደወል ነው። ኃያላኑ አዲስ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያደርጉት ፍልሚያ ውስጥ ተጎጂ ላለመሆን፣ እንደ ዜጋም ሆነ እንደ ተቋም ፍጹም ንቃትና ዝግጅት ያስፈልጋል። ከታሪክ በመማር የውክልና ጦርነት ከመሆን ወጥተን፣ የታሪክ ተጠቃሚ ለመሆን የውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር፣ ገቢር ነበብ ዲፕሎማሲ መከተል እና ብሔራዊ ጥቅማችንን በማንኛውም ዋጋ ማስከበር የሁላችንም የወቅቱ ታላቅ ኃላፊነት ነው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር



