ቪኦኢ ዜና – ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የመጪው ዘመን የአፍሪካ ኃያል ሀገር ወደመሆን እየተሸጋገረች መሆኗን ታዋቂው የህንድ ሚዲያ ፈርስት ፖስት ዘገበ።
ሚዲያው ባወጣው ወደ ዘጠኝ ደቂቃ በሚጠጋ የቪዲዮ ትንታኔው፤ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ መንግስታት ምድር እና የታሪካዊ መሰረት ባለቤት መሆኗን በማስታወስ፣ በአሁኑ ወቅት ከቀድሞ ገናና ታሪኳ ጋር የሚመጣጠን አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለመገንባት በከፍተኛ ትጋት ላይ እንደምትገኝ ገልጿል።
ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገሪቱ በጦርነት፣ በድርቅ እና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ትታወቅ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ ያንን የተዛባ ትርክት በኢነርጂ፣ በአቪየሽን፣ በማዕድን እና በዲጂታል ኢኮኖሚ እያስመዘገበች ባለው አስደማሚ ለውጥ እየቀየረችው እንደሚገኝ ዘገባው አመልክቷል።
በዘገባው መሰረት ለዚህ አህጉራዊ ሽግግር በዋና ምክንያትነት ከተጠቀሱት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል፡፤
ከ5 ሺህ ሜጋዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው ይህ ፕሮጀክት የመንግስትና የሕዝብ ቁርጠኝነት ማሳያ ከመሆኑም በላይ፤ ሀገሪቱ ለኬንያ፣ ጂቡቲ እና ሱዳን ታዳሽ ኃይል በመሸጥ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል።
በ12.5 ቢሊዮን ዶላር ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን ተጓዦችንና 4 ሚሊዮን ቶን ዕቃ በማስተናገድ አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲና ንግድ ዋና መተላለፊያ ያደርጋታል።
የወርቅ ምርትን በማስፋፋት የውጭ ምንዛሬ አማራጮችን ማሳደግ መቻሉና በሶማሌ ክልል የሚገነባው በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የሚያመርተው ፋብሪካ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥነዋል።
የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ፣ የ4ጂ እና 5ጂ አውታሮች መስፋፋት እንዲሁም እንደ ቴሌኮም እና ባንክ ያሉ ዘርፎች ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት መሆናቸው ለግል ዘርፉ ማደግ መንገድ ከፍቷል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗን የጠቀሰው ፈርስት ፖስት፤ ሀገሪቱ ጎራ ሳትለይ ከቻይና፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከምዕራባውያንና ከአፍሪካ አጋሮቿ ጋር የምታደርገውን የኢንቨስትመንት ትብብር አጠናክራ በመቀጠል የቀጣናውንና የአህጉሪቱን አጠቃላይ ገጽታ በአዲስ መልኩ እየቀረፀች ትገኛለች ሲል አብራርቷል።

