ደቡብ ሱዳን የናይል ስምምነት ማዕቀፍን በፓርላማ በማጽደቅ ስድስተኛ ሀገር ሆናለች፡፡ ከ11 የናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ስድስት ሀገራት በፓርላማ ካጸደቁ ቋሚ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መግባት ይችላል፡፡
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነቢል ማህዲ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የናይል ስምምነት ማዕቀፍን በአባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ከተፈረመ ቆይቷል፡፡ አምስት ሀገራት በፓርላማቸው አጽድቀው ነበር፡፡
የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን ለመመስረት የሚጠበቀው ስድስተኛ ሀገር በፓርላማ እስኪያጸድቅ ድረስ ነበር፤ ደቡብ ሱዳን አጸድቃለች ብለዋል፡፡
ስድስት ሀገራት የናይል ስምምነት ማዕቀፍን ማጽደቃቸው ፋይዳው ከፍተኛ ነው ያሉት አምባሳደሩ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በሙሉ በሰነዱ ይገዛሉ፡፡ በሐምሌ አንድ ቀን 2016 ዓ.ም የደቡብ ሱዳን በፓርላማ የናይል ስምምነት ማዕቀፍን በማጽደቅ ስድስተኛ ሀገር ሆናለች፡፡
የናይል ስምምነት ማዕቀፍን ለማጸደቅ ሂደቱ በጣም ከባድ ነበር ያሉት አምባሳደር ነቢል፤ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለፉት ሶስት አመታት ብዙ ትግል አድርጓል፡፡ የደቡብ ሱዳን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከአምስት አመት በፊት ያጸደቀው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን ገልጸዋል፡፡
በፓርላማ ውስጥ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የተገኘ ውጤት ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት በመሆኑ የሰላም ስምምነቱን የፈረሙ ፓርቲዎችን በሙሉ በማነጋገር የመጣ ነው ብለዋል፡፡ መፈረማቸው ለደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር ሆና የናይል ስምምነት ማዕቀፍን አጽድቃለች ያሉት አምባሰደሩ፤ በቅርቡ የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ይፈርማሉ፡፡ በመቀጠልም ሰነዱን ለአፍሪካ ህብረት በመላክ ሕጋዊ ሰነድነቱ ይረጋገጣል፡፡
ከደቡብ ሱዳን በፊት የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ፈርመዋል፤ይሁንና ወሳኙ ስድስተኛ ሀገር መፈረም በመሆኑ ደቡብ ሱዳን መፈረሟ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ጉዳዩን የኢትዮጵያ መንግስት የቅርብ ክትትል ያደረገበት በመሆኑ የተሳካ መሆን ችሏል፡፡
ደቡብ ሱዳን የናይል ስምምነት ማዕቀፍን መፈረሟ ለኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ነጻነት ከፍተኛ መስዋትነት ከፍላለች፡፡ ደቡብ ሱዳንም አጠቃላይ ለተፋሰሱ ሀገር በተለይ ለላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ያላትን አጋርነት ያረጋገጠችበት ነበር ብለዋል፡፡
ማእቀፉን ያጸደቁ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋዳንዳ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን ናቸው፡፡
የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እአአ 2006 የተዘጋጀ ሲሆን የናይል ተፋሰስ አገራት የውሃ ሀብቶችን በትብብር ማልማትና ማስተዳደር የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ያስቀመጠ ነው፡፡ የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ (NBI) የሽግግር ማእቀፍ ሆኖ በዘጠኝ መስራች አባል ሀገራት የጋራ ራእይ የተመሰረተና ቋሚ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን እስከሚመሰረት የሽሽግር ማእቀፍ ሆኖ እንዲያገልገል ታስቦ መቋቋሙ ይታወቃል።
በሞገስ ጸጋዬ ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓም (ኢ ፕ ድ)


