ከሃምሳ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አሁን አሜሪካ ናቸው። የሚመሩት ፓርቲ ኦፌኮን የውጭ ደጋፊዎችንና ተከታዮች ለማግኘት ረዘም ያለ ዕቅድ ይዘው ከባልደራባቸው ጋር ባሉበት ኢትዮሪቪው ከቀናት በፊት እንግዳ አድርጓቸዋል። ፕሮፌሰር መረራ የሰጡትን ማብራሪያ ለአንባቢ እንዲመች በማድረግ አቅርበናል፡
ፕሮፌሰር መረራ ከስር በተቀመጡት ቀናት የህዝብ መድረክ አላቸው። በተጠቀሰው ቀናትና ሰዓት ፈቃደና የሆናችሁ ተከታይና ደጋፊዎች እንድትገኙ ጋብዘዋል። መልካም ንባብ።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
ኢትዮ ሪቬው – ፈሪ ነዎት?
መረራ – እፈርላሁ ማለት ይቻላል። አልፈራም ማለትም እችላለሁ። ይህ ነው ብዬ ለይቼ መግለጽ ይቸግረኛል። ሌሎችን ብትጠይቅ አይሻልም?
ኢትዮ ሪቬው – ቂመኛ ነዎት
መረራ – ቂመኛ እንኳን አይደለሁም።
ኢትዮ ሪቬው – አኩራፊ ነዎት?
መረራ – እንደሁኔታው ላኮርፍ የምገደድባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ግን ራሴን በአኩራፊነት አልመደብም።
ኢትዮ ሪቬው – ከሚቆጭዎት ነገሮች ዋናው ምን ይሆን?
መረራ – በእድሜዬ ሁለት ትውልድ በመከፋፈል ፖለቲካ ሲበላ ከማየት በላይ የሚቆጭ ነገር የለም። እልፍ እንዳንል ያደረገን መከፋፈል ነው። የመከፋፈል አደጋ ያደረሰብንን እልቂትና መከራ እያየን አሁንም እዛው ችግር ውስጥ መሆናችን እጅግ ይቆጨኛል። የመከፋፈል ፖለቲካ አጀንዳው አለመዘጋቱ እኔን ብቻ ሳይሆን …
ኢትዮ ሪቬው – ሃዘን ይሰማዎታል፣ ሃዘን ውስጥ ነዎት ማለት ነው?
መረራ – ቁጭት ሃዘን ነው። ከፍተኛ ሃዘን የሚፈጥረው ስሜት ቁጭት ነው። ቁጭት የሃዘን ውጤት ይመስለኛል። ካላዘንኩ ልቆጭ አልችልም። ይህ በሽታ ነው። መድሃኒት ያለው በሽታ መሆኑን ለሚያስቡ ሁሉ በመጠፋፋት ፖለቲካ 50 ዓመት መዝለቅ ወይም ከዚያ በላይ እረፍት የሚነሳ ታላቅ ሃዘን ነው።

ኢትዮ ሪቬው – የሚድን በሽታ ሲሉ?
ግልጽ እኮ ነው። የአገሪቱ ልሂቃን መስማማት አልቻልንም። ልሂቃን ናቸው ታግለው የሚታግሉት። ህዝብን የሚመሩ። ይህን ማድረግ አልቻልንም። ተግባብቶና በልዩነት ውስጥ ተከባብሮ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማምራት ከመስማማት ይልቅ በረባውና ባልረባው ልዩነት እየተፈጠረ መባላት ተመረጠ። እርስ በእርስ በመባላት የደረሰውን ጥፋት አስቦ አንዱ ከሌላው መማር አልቻለም። መድሃኒቱ መባላትን ለማቆምና የኢትዮጵያ ህዝብ እከሌ ከከሌ ሳይባል በእኩልነት ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማምራት መስራት ነው። ቀላልና አመቺውም መንገድ ይህ ነው።
ኢትዮ ሪቬው – ምን ያስደስትዎታል?
መረራ – የተሻለች፣ ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን ብንፈጥር ወይም የምትፈጠርበትን መንገድ ዛሬ ላይ አደላድለን ብናልፍ ምኞቴ ነው። የእስካሁኑ ጉዞ የእድሜ ልክ ቁጭቴ ነው።
ኢትዮ ሪቬው – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን አኩርፈዋቸዋል ይባላል፤
መረራ – ማኩረፍ ሳይሆን ጮሌዎች ለውጡ ከተጀመረበት አግባብ ውጭ ይዘዋቸው ወጡና የለውጡ መስመር ሳተ።
ኢትዮ ሪቬው – ጮሌዎቹ እነማን ናቸው?
መረራ – ከለውጡ ማግስት የወሰዷቸው።
ኢትዮ ሪቬው – ካላብራሩት እንደው በደፈናው እርስዎ ከሚታይዎት ከዚያ መንገድ የሚመለሱ ይመስልዎታል?
መረራ – ከውጭም ከውስጥ የከበቡዋቸውን ማራገፍ የሚችሉ አይመስለኝም። ስልጣን በያዙ በሁለትና ሶስት ወር ሚኒሊክ ቤተመንግስት የገባ ኦሮሞ ራሱንም ኦሮሞንም ይዞ ይጠፋል። ይህን ነገሩልኝ ብዬያለሁ።
ኢትዮ ሪቬው አቶ ጃዋር ኦፌኮ ውስጥ አሁንም አሉበት
መረራ – አዎ። የተለወጠ ነገር የለም።
ኢትዮ ሪቬው – ለቅቄያለሁ ማለታቸውን የዘገቡ ነበሩ
መረራ – አልሰማሁም። ጃዋር በራሱ ችግር የተነሳ የሚኖረው ኬንያ ነው። እንገናኛለን። የማውቀው ይህን ነው።
ኢትዮ ሪቬው – ስራ አስፈጻሚ እንደመሆኑ ለአሰራር አያስቸግርም?
መረራ – ምን ጥያቄ አለው? አብረን አንድ ላይ ብንሰራ ይመረጣል። የሚሻለውም እሱ ነው። ምንም እንኳን አስቸጋሪ ቢሆንም፣ እሱም መልቀቂያ አልጠየቀም። እኛም አላሰብነውም። እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የቅርብ ደጋፊዎቻችን የግድ ቅርብ ሆነው ይታሰሩ ይሙቱ አንልም። ባሉበት ሆነው የሚቻላቸውን ያበረክታሉ።
ኢትዮ ሪቬው – እና ጃዋር አሁንም ስራ አስፈጻሚ ነው? ይወስናል?
መረራ – አዎ ከቀድሞው የተቀየረ ነገር የለም።
ኢትዮ ሪቬው – አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን አግኝተዋቸዋል የሚሉ መረጃዎች አሉ።
መረራ – በፍጹም ፣ በፍጹም አልገኘሁዋቸውም። ለምን ነበር አገኛቸው የተባለው?
ኢትዮ ሪቬው – አብሮ ቅንጅት የመፍጠር ዕቅድ አላችሁ ነው የተባለው፤
መረራ – ለመሆኑ ድርጅት አለው እንዴ?
ኢትዮ ሪቬው – እሳቸው በይፋ “የዚህኛው ነኝ” ባይሉም ከፋኖ አደራጀቶች መካከል በአንዱ አሉ ይባላል። ጽሁፍም ጽፈዋል
መረራ – እሱን አላውቅም። ግን ፋኖ እኮ ያለው በአማራ ጫካ ውስጥ ነው። ወደ ሁዋላ የሚያዩት ነገር ጥርጥር ውስጥ ያስገባል። በዚያ መልኩ ከፋኖ ጋር መነጋገር ያስቸግራል። እሳቸውን ግን አላገኘሁዋቸውም።
ኢትዮ ሪቬው – ከፋኖ ጋር ጭራሽ አብረን አንሰራም እያሉ ነው? ቀደም ሲል የመከፋፈል አጀንዳ ጉዳቱ ቁጭት ውስጥ እንደከተተዎ ነገረውኝ ነበር እኮ፤
መረራ – ቁጭቱ የኔ ብቻ ሳይሆን በርካታ እኔን መሰሎችም የሚጋሩት ነው። በተለይ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ስሜት አለው። ከፋኖም ሆነ ከማንም ጋር አብሮ መስራት አግባብ ነው። እኛ ከህብረትና መድረክ ጋር ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ሰርተናል። አሁንም እየሰራን ነው። ፋኖን አስመልክቶ ወደ ሁዋላ የሚያዩት ነገር ያሳስበናል። አንዳንድ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ለመነጋገር የሚጋብዙ አይደሉም። እኔ በምለው የትግል አግባብ ተደራጁ የሚሉ አካሄዶች አያዋጡም። ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ የማያቀነቅን ፖለቲካ የቀደመውን ችግር ከመድገም የተለየ ውጤት አያመጣም። ሁሉም ለውጦች የጨነገፉት ለዚሁ ነው። አሁን በተያዘው መንገድ ለውጥ ቢመጣም ተመልሶ የሚበላሽ ነው። መታየት ያለበት በዚህ አግባብ ነው። ፋኖ ፊውዳሊስቷን ኢትዮጵያ ለመመለስ የሚታገል ሁሉ ይመስላል።
ኢትዮ ሪቬው – ወለጋ የእኛ ነው የሚለው መፈክር ያበሳጨዎት ይመስላል ፤
መረራ – እንደሱ አይደለም። ብስጭትም አይባልም። ዝም ብሎ አየር ላይ የሚነፍስን ወሬ እያነሳን ጊዜ መፍጀትም አይጠቅምም። የህልም አይነት፣ የቅዠት አይነት ነገር ዋጋ የለውም። ዋናው ጉዳይ መሰረታዊ በሆኑ አግባቦች ላይ በማተኮር ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ መጠላለፍን አስወግዶ መስራት ነው የሚበጀው። እኛ በመከፋፈል አናምንም። አስቀድሜ እንዳልኩት ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ የጠራና መከፋፈል ላይ ያተኮረ ትግል ሁለት ትውልድ በልቷል። ስለዚህ ከስሜት በመውጣት መሬት ላይ ያለውን እውነት በማስላት አብሮ ለጋራ ጥቅም.መታገል አስፈላጊ ነው። ከላፉት ጊዜያት ስህተቶች መማር ግድ ነው። አለበለዚያ ሁሌም ለመገዛት እየተመቸን እንቀጥላለን።
ኢትዮ ሪቬው – እና እርስዎ እንዳሉት አካሄዱ ከተስተካከለ ከፋኖ ጋር አብራችሁ ለመስራት ፍላጎት አላችሁ?
መረራ – እኛ እኮ አብሮ የመስራት ችግር የለብንም። አብሮ የመስራት ችግር እንደሌለብን አብረውን የሰሩና እየሰሩ ያሉ ይመስክራሉ። ግን አብሮ የማያሰሩ መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ በወለጋና አምቦ መስመር ጅባት ተራ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ተፈጽሟል። ማንም …
ኢትዮ ሪቬው – ሰፊ ቁጥር ያላቸው አማራዎችም በኦሮሚያ ተገድለዋል እኮ
መረራ – ማንም ይሁን ማን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸም የለበትም። ይህን በድርጅትም ይሁን በግሌ አጥብቄ እቃውማለሁ። በርካታ ወንጀሎች በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጽመዋል። ይህ በጥልቅ መመርመርና መጣራት ያለበት ጉዳይ ነው። ዝም ብሎ በመቀባባትና ጣት በመቀሰር የሚታለፍ ሊሆን አይገባም። ወንጀሉ ተፈጽሟል። ሰዎች ሞተዋል። ተፈናቅለዋል። ጥፋተኛውን ወገን በትክክል መለየት ግድ ነው። አሁን በያዝነው አግባብ ትክክለኛውን ጥፋተኛ ወገን ለመለየት አያስችልም። ሰላማዊ ዜጎች ላይ ሲፈጸሙ የቆዩና አሁንም የሚፈጸሙ ወንጀሎች ጉዳይ ሰፊ ምርመራና ክትትል የሚሻ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ወደ ጥያቄው ስመጣ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ስጋት አለን። የቴድሮስ ጦር፣ የሚኒሊክ ጦር እየተባለ የቀድሞውን ጉዳይ እንደ አንድ ጥሩ ሞዴል መገልገል ትግሉ ምን ለማግኘት እንደሆነ በጥርጥር እንድናየው ያደርገናል። እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎችም በተመሳሳይ መንገድ ማሰባቸው አይቀሬ ነው። አካሄዱና ሙከራው የቀድሟዋን ፊውዳላዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት ከሆነ መግባባት አይቻልም። ከእኛ ጋር ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ የሚሸጥ ዓላማም አይመስለኝም። ይህን አካሄድ ሰከን ብሎ በማየት በኢትዮጵያ የቀደሙ ችግሮችን ዘግቶ ወደ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋግረውን አግባብ ካልሞከርን ግንኙነት ቢጀመረም ዋጋ አያስገኝም። እንደውም ለመገዛት መመቸት ይሆናል።
ኢትዮ ሪቬው – ለመገዛት መመቸት” ደጋግገሙ፤
መረራ – ልዩነትና የእርስ በእርስ መከፋፈል ለመገዛት መመቸትን ያመጣል። በማትስማማበት ሁኔታ ህብረት ጀምረህ መልሰህ ስትበታተን ገዢዎች እንዲረግጡህ ትመቻለህ። በኢትዮጵያ ታሪክ በተደጋጋሚ የታየው ይህ ነው። የተቃዋሚው ጎራ አጀንዳ እየፈጠረ እርስ በእርሱ ሲበላላ ገዢዎች ተመችቷቸዋል። በተለይ የትግሬ፣ የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን መግባባት አለመቻላቸው ለመንግስት ድል ነው። መንግስት አሞሌና ዱላ አለው። በዚህ ላይ እኛ ስንከፋፈልለት ለመግዛት ያመቸዋል። ይህ በተግባር የታየ እውነት ነው።
ኢትዮ ሪቬው – ሁሌ “አሞሌና ዱላ ይላሉ” የማን ጥፋት ነው የገዢው ወይስ ራሱን የሚሸጠው?

መረራ – ዱላው የመንግስት ጉልበቱ ነው። ያስራል ይገላል። አሞሌው ሃብቱ ነው። ፖለቲከኞችን ይገዛል። ድርጅቶችን ይገዛል። ከሞራል አንጻር አንድ መንግስት በዚህ ዓይነት ተግባር ውስጥ መሳተፍን ቀዳሚ ተግባሩ ማደረጉ ነውር ነው። ይህ ቀድሞ ነበር አሁንም ቀጥሏል። ከምንም በላይ ግን እንደ በግ ራሳቸውን ለገበያ የሚያቀርቡት “ሰዎች” ያሳፍራሉ። ዞሮ ዞሮ ሰለባዎቹ ለውጥና እድገት የሚፈልጉ ዜጎች ናቸው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት አንድ መንግስት ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ፣ ትርጉም ያለው ልማትና ብልጽግና ካላመጣ የትም ስለማይደርስ ከዚህ ተግባር በመውጣት አገሪቱን ወደ ተሻለ አግባብ መምራት ይገባዋል። ይህን ካደረጉ በስተመጨረሻም የመልካም ታሪክ ባለቤት ይሆናሉ።የሰለጠነው አካሄድም ይህ ነው። ሰዎችን በመግዛት፣ በማፈንና በመጨፍለቅ አካሄድ ያለፉ እንዴት እንደወደቁ የታየ በመሆኑ ከዚህ የተለየ ውጤት አይጠበቅም። በድሮው መንገድ ከቀጠሉ የሚሆነው ያው የቀድሞውን አወዳደቅ መድገም ብቻ ነው። እንደ ቀደሙት ዓይነት …
ኢትዮ ሪቬው – ከኦነግ ጋር ፍቅር ናችሁ?
መረራ – አብረን እየሰራን ነው።
ኢትዮ ሪቬው – ማለቴ እንደው ግንኙነታችሁ ከልብ ነው?
መረራ – ድሮ እነሱ ሙሉ በሙሉ በትጥቅ ትግል ያምኑ ነበር። እኛ ደግሞ ሰላማዊ ትግል እንጂ የትጥቅ ትግል እንደማይሰራ አበክረን እንገልጽ ነበር።፡አሁን እነሱ ወደ ህጋዊው መስመር መጥተዋል። ስለዚህ በመሰረታዊ ልዩነታችን ዙሪያ የነበረው አጅንዳ አሁን የለም። እናም …
ኢትዮ ሪቬው – ላቋርጥዎ ነው
መረራ – ይቻላል
ኢትዮ ሪቬው – ኦነግ እኮ አሁንም እየተዋጋ ነው። የኦነግ ሰራዊትና እነሱ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል። ይስማማሉ?
መረራ – እኔ እስከማውቀው ድረስ አዲስ አበባ ያሉት የኦነግ አመራሮች ከኦሮሞ ነጻነት ጦር OLA ጋር ግንኙነት የላቸውም። እንዳውም ይጣላሉ።
ኢትዮ ሪቬው – እርስዎ ይህን ቢሉም ጨዋታው ሁለት ቦታ እንደሆነ የሚናገሩ ብዙ ናቸው፤
መረራ – በግል እስከማውቀው ግንኙነት ያላቸው አይመስለኝም። እንደዚያ አይነት ግንኙነት እንዳላቸው አይሸተኝም። መረጃዬ የሚነገረኝ ይህንን ነው።
ኢትዮ ሪቬው – የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሚያሸንፍ ይመስልዎታል?
መረራ – እሱ የሚወሰነው በመንግስት አቋም ነው።
ኢትዮ ሪቬው – ቢያብራሩት
መረራ – በኢትዮጵያ ፖለቲካ ልምድና እውነታ የመንግስታቱ ጨዋታ ነው የታቃውሞ ሃይሎች እንዲያሸንፉና እንዲሸነፉ የሚያደርገው። በተሸነፉት መንገድ ከቀጠሉ ሌሎቹ የደረሳቸው እድል ሊገጥማቸው የማይችልበት አግባብ የለም። የሚበጀው ሁሉንም አሳትፎ ዴሞክራሶያዊ መንግስት መመስረት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው አግባብ ውጤቱ እርስ በእርስ መጠፋፋት ነው። የሚያሳዝነኝም ይኸው ማቆሚያ የሌለው መተፋፋት ነው። መጫረስ!
ኢትዮ ሪቬው – እና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ጦር አይጠፋም እያሉ ነው?
መረራ – እኛ እነሱ በጠመንጃ ሃይል ይጥፉ የሚል አቋም የለንም። እነሱም ሌላውን የማጥፋት አቋም ሊኖራቸው አይገባም። የሚበጀው በውይይት፣ በውይይት ስል በትክክለኛ የውይይት አግባብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገነባበትን የመጫወቻ ግብዓቶች ሁሉ አሟልቶ ህዝብ የሚወስነበት መድረክ ማመቻቸት ነው። ይህ ሲሆን ጠፊም አጥፊም አይኖርም።
ኢትዮ ሪቬው – የኦሮሞ ነጻ አውጪ ጦር የእናንተን አባላት ወይም አመራሮች ይተናኮሳሉ?
መረራ – እስካሁን ባለኝ መረጃ አይነኩንም።
ኢትዮ ሪቬው – እድሜዎ እየሄደ ነው። ስለ ፖለቲካ ጡረታ አያስቡም? “በቃዎት” የሚሉም አሉ፤
መረራ – ሃምሳ ዓመት በኢትዮጵያ ፖለቲካ አሳልፌያለሁ። ይህ ቀላል ጊዜ አይደለም። የሁለት ትውልድ ዘመን ነው። ወያኔ ከእስር ሲለቀኝ “በቃኝ” ለማለት ውስኜ ነበር። እኔን ለመቀበል የወጣው ህዝብና በሄድኩበት ሁሉ ያየሁት አቀባበል ከህዝቡ ብዛት ጋር ተዳምሮ “ይህን ህዝብ ትቼ ወዴት ነው የምሄደው?” በሚል ራሴን እንድጠይቅ አስገደደኝ። ለግል ምቾት ብዬ በአግባቡ ተተኪ ሳይኖር ጥሎ መሄድ ክህደት ሆኖ ተሰማኝ…
ኢትዮ ሪቬው – ስለ ተተኪ ከተነሳ የማን ጥፋት ነው ተረካቢ ወይም ምትክ አመራር ያለማዘጋጀቱ ጉዳይ
መረራ – ተተኪ የለም ማለት አይቻልም። የወጣቶች ሊግ አመራር ራሱን ችሎ የቆመ ነው። ማንም እንደሚያውቀው ጥሩ ፓለቲከኞች ብቅ ሲሉ ይቀጫሉ። ተስፋ የሚጣልባቸው ጀግኖች ሲነሱ ይታሰራሉ። ስደትን እንዲመርጡ ይደረጋል። ፈተናው ብዙ ነው። ይህ ሁሉ ጥያቄ መልስ የሚያገኘው አገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲኖራት ብቻ ነው። ስንት ፖለቲከኞች እንደተገደሉና እንደተሰደዱ፣ እንደታሰሩ ህዝብ ያውቃል። አሁን ድረስ የት እንደገቡ የማይታወቁ ደብዛቸው የጠፋ አሉ። ያም ሆኖ ለጊዜው ሊቀመንበር ባይሆኑም ተተኪዎች አሉን።
ኢትዮ ሪቬው – ቄሮ የት ደረሰ?
መረራ – ቄሮ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለው አዲስ የህብረተሰብ ክፍል ነው። ከለውጡ በሁዋላ አንዱ ወገን በመንግስት ተገዛ። አንደኛው ወገን ጫካ ገባ። አንዱ ወገን ተሰደደ። ለውጥ ለማምጣት የታገሉ እንዳልኩት በየፊናቸው ሄዱ። ዳግም ለትግል ጫካ የገቡ እንዳሉ ሁሉ፣ መንግስትን ለማገልገል ወስነው ከመንግስት ጋር የቀጠሉ ኦሉ። ይህ ጥቅል እየታዬ ነው።
ኢትዮ ሪቬው – አሁን አሜሪካና ካናዳ ሆነው በተለያዩ መድረኮች ላይ እየታዩ ነው። ዓላማው ምንድን ነው? ውጤቱስ?
መረራ – ውጭ ያለው ዲያስፖራ የትግሉ አካል ነው። አቅም ይጨምርልናል። የውጩን ዲፕሎማሲም ለማጠናከር ይረዳል። በዚህ አግባብ በውጭ ካሉ ደጋፊዎቻችን፣ ህብረተሰባችን ጋር መመካከር አስፈላጊ በመሆኑ ይህንኑ ስራ እየሰራን ነው። ስለውጤቱ ከጉዟችን መጠናቀቅ በሁዋላ የምንገመግመው ይሆናል። በስፖርቱ ውድድርና በተለያዩ ስቴቶች በምናደርገው ውይይት ሰፊ ስራ እንደምንሰራ ግን ጥርጥር የለውም።
ኢትዮ ሪቬው – በሜኖሶታ ኮንግረስ አባል ኢልሃን ዑመር ጋር አንድ መድረክ ላይ መታየትዎን በርካቶች እየተቹ ነው?
መረራ – ትችቱ ብዙም ባይገባኝም የተገናኘነው የኦሮሞ ጥናት ማዕከል ባዘጋጀው መድረክ ላይ እሷም እንደ እኔው ተናጋሪ ሆና ተጋብዛ ነው። እንደሚታውቀው በሜኖሶታ ሰፊ ቁጥር ያላቸው የሶማሌ ዜጎች ናቸው። ቀጥሎ ደግሞ ኦሮሞዎች ናቸው። የሁለቱን ህዝብ ግንኙነት ማጠናከር አግባብ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ ምርጫም አለባት። ድምጽ ትፈልጋለች። በነገራችን ላይ አማኒ ባሾ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነች የምርጫ ተወዳዳሪ አለች። በመድረኩ ላይ እሷም በተሰጣት ርዕስ ተናግራለች። እኔም ተናግሪያለሁ። ይህ ከምንም ጉዳይ ጋር አይገናኝም።
ኢትዮ ሪቬው – በጋራ ለመስራት አስባችሁ ከሆነ?
መረራ – እሷ እኮ አሜሪካዊ ናት። እንዴትና ምንድን ነው በጋራ የምንሰራው?
ኢትዮ ሪቬው – እሷ ኃላፊነቷን ተጠቅማ የምታመቻቸው ጉዳይ ካለ?
መረራ – አስቀድሜ እንዳልኩት ሰፊ ቁጥር ያላቸው የሶማሌና ኦሮሞ ተወላጆች በሚኖሶታ ይኖራሉ። ቁጥራቸው ትልቅ ነው። ይህ ህዝብ ግንኙነቱን ቢያጠናክር ሰፊ ስራ መስራት ይችላል። ግኝኙነታቸው ቢሰፋ ሃይል ይሆናቸዋል። ሃይል ካላቸው ይደጋገፋሉ። ግልጽ አመክንዮ መስለኝ።
ኢትዮ ሪቬው – የአሜሪካና የካናዳ ጉዞ ከፖለቲካ ነጋዴዎች አካሄድ የተለየ ሰመሆኑ ምን ይላሉ?
መረራ – ግልጽ አይደለም፤
ኢትዮ ሪቬው – ማለቴ እዛም እዚህም ብር ለቀማ በርክቷል። ህዝብ እያጫረሱ ገንዘብ የሚሰበስቡ መበራከታቸው ገሃድ ነው። ኦፌኮ ስሙ በዚህ ጉዳይ ባይነሳም የብሄር ዋሻ ውስጥ ሆነው የግል ኪሳቸውን የሚጠቀጥቁ …

መረራ – ነጋዴዎች አሉ። እጅግ በሚገርም ሁኔታ ፖለቲካውን ንግድ ያደረጉ በርክተዋል። አንዱ የመከፋፈሉ ወቃታዊ በሽታ ይህ የንግድ እሳቤና ፖለቲካውን ለከርስ የማዋል አካሄድ ነው። ትግሉን እየበላ በአጭር የሚያስቀረው ይህ በሽታ ነው። እዚህ ላይ ህዝብ ሊጠነቀቅ ይገባል። በተለይ ዲያስፖራው የአቅም ምንጭ እንደመሆኑ ነጋዴውን ክፍል ትክክለኛ የፖለቲካ ስራ ከሚሰሩት ለይቶ ማየት አለበት። መመርመርና መመዘን አስፈላጊ ነው።፡ይህ ካልሆነ ነጋዴዎችን መቀለብ ይሆናል። ይህ ደግሞ ለውጥን ከመመኘት በዘለለ ሌላ ውጤት አያመጣም። እውነት ለመናገር አሁን ላይ በኢትዮጵያ ፖለቲክ ውስጥ በአሞሌ መሸጥና ራስን የህዝብ ተቆርቋሪ በማስመሰል መነገድ የተለመደ ሆኗል። ወደ እኛ ስንመጣ ይህን አጥርተን ለማሳየት በየመድረኩ እንናገራለን። ቢወደድም ባይወደድም ህዝብ ማንን መርዳት እንዳለበት በይፋ እንናገራለን። ለእኛ ብቻ ሳይሆን በትክክል ለህዝብ ለሚሰሩ ወገኖች በአግባቡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ እናስተምራለን።
ኢትዮ ሪቬውን አዲስ ቴሌግራም ገጽ ይከተሉ https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk
READ ALSO THIS


