ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት የተካሄደው ሰባተኛው ታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ሥነሥርዓት ላይ “እናንተን ለማገልገል ስልጣን ይዘው፤ ከእናንተ ገንዘብ የሚቀበሉ ባለስልጣናትን የምታስተናግዱ እንዳትሆኑ” አሉ። በኢትዮጵያ ብልጽግና የሚያምኑ እንዲከተሏቸው ጥሪ አቀረቡ። “እኔ አምናለሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማፋጠን፤ ከሚገጥሙን ፈተና እና ተግዳሮቶች ዕድሎችን ፈልቅቀን እያወጣን መስራት እንጂ መቆም የለብንም ብለዋል።
ኢትዮጵያን በትብብር፣ በሕብረት እና በመተጋገዝ ካለችበት ደረጃ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል። አክለውም “የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማየት ሁላችንንም ያብቃን፤ እኔ እንደማይ አምናለሁ ያመነ ከእኔ ጋር ይጓዝ” ሲሉ ተደምጠዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የውጭ ኩባንያዎች እና የውጭ ዜጎች ይበልጥ ትርፋማ እንዲሆኑ እና ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር እንዲዋሀዱ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በኢንቨስትመንት ቦርድ በኩል ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።
ሰባተኛው ታማኝ ግብር ከፋዮች የዕውቅና ሥነሥርዓት ተካሂዷል። በ2010 ዓመተ ምህረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው ይኽ ሥነሥርዓት የዜግነት የግብር ግዴታቸውን በወቅቱ እና በታማኝነት የሚፈፅሙ ዜጎችን ለማበረታታት ታቅዶ የሚተገበር ነው። በዘንድሮው መርሃ ግብር 700 ታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጥቷቸዋል። በ2017 ዓመተ ምህረት እንደነበራቸው አስተዋጽኦ መጠን 105 የፕላቲኒየም ደረጃ፣ 245 የወርቅ ደረጃ፣ 350 ደግሞ የብር ደረጃ ተሸላሚ ሆነዋል። የጋራ አስተዋጽኦዋቸው በሥራ ዘመኑ 900.22 ቢሊዮን ብር በግብር እንዲሰበሰብ አስችሏል።
በተጨማሪም የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን በግብር እና ቀረጥ አሰባሰብን ብቁ እና ግልፅ የሚያደርጉ የዲጂታል ሥርዓቶችን አስጀምረዋል። ከነዚህም ውስጥ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት፣ ኤሌክትሮኒክ የጉምሩክ አስተዳደር ሥርዓት እና ኤሌክትሮኒክ የጭነት መከታተያ ሥርዓት ይገኙበታል።
በ7ኛው የታማኝ ግብር ከፋይ ዕውቅና እና ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፡-
- ላለፉት አራት ዓመታት በታማኝነት ፕላቲኒየም ሽልማት ያገኙ 30 ልዩ ተሸላሚዎች፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ከሆኑ ባለቤቶች ወይም ሥራ አስፈጻሚዎች ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ይሰጣቸዋል።
ይህ የሚሆንበት ዋና ምክንያት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ ለሥራ ሲንቀሳቀሱ ቪዛን ጨምሮ ላለው ማንኛውም ነገር መስተጓጎል እንዳይገጥማቸው ነው።
በዚህም መሠረት ልዩ የፕላቲኒየም ተሸላሚዎች እንደ ኩባንያው ምርጫ ለባለቤት ወይም ሥራ አስፈጻሚ ዲፕሎቲክ ፓስፖርት ሰጥተን እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ዲፕሎማት የሚወሰዱ ይሆናል።
- ከ30ዎቹ የፕላቲኒየም ልዩ ተሸላሚዎች መካከል የኢትዮጵያ ኩባንያ ለሆኑት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከኢትዮጵያ ውጭ በተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት ኢንቨስት እንድታደርጉ መንግሥት የኢንቨስትመንት ዓርማ አድርጎ ከእናንት ጋር ይሠራል።
ኢትዮጵያ ማንሠራራት የጀመረችበት ዘመን ስለሆነ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ኢንቨስት ማድረግ ለእኛ በቂ ስላልሆነ በተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት ለልዩ ተሸላሚዎች በሚያቀርቡት ፕሮፖዛል መሠረት መንግሥት ልዩ ድጋፍ ያደርጋል። በምትሄዱበት ሀገርም ኤምባሲዎቻችን እናንተን ያገለግላሉ።
- ሀገራችን ትሠራለች፤ ለልጆቻችን የበለጸገች ሀገር እናስረክባለን።
- የገባነውን ቃል እንፈጽማለን።
- ብዙ ሕዝብ፤ ብዙ የሚችሉ ዜጎች ያሏት ሀገር ስለሆነች መንግሥት በዕውቀት የግሉን ሴክተር እየደገፈ፤ ከሀገር ውጭ እያመረታችሁ የሀገራችሁን ስም የምታስጠሩ ተጨማሪ ሀብት የምታመጡ እንድትሆኑ አበክረን እንሠራለን።
- በእኛ በኩል ከሞላ ጎደል ሲስተም በማዘመን ሌብነትን ለመቀነስ ጥረት ያደረግን ቢሆንም፤ አሁንም ሌብነት እንዲጠፋ የግሉ ሴክተር ተባባሪ እንዲሆን እናንተን ለማገልገል ሥልጣን ይዘው ከእናንተ ገንዘብ የሚቀበሉ ባለሥልጣናትን እንዳታስተናግዱ አደራ እላለሁ።
- የማይተጋ ሀገር፣ ያለችውን ውስን አንጡራ ሀብት የሚያሸሽ ሀገር አይበለጽግም። እኛ መበልጸግ ስለምንፈልግ ሌብነትን የምንጸየፍ፣ ሀብት ማሸሽን የምንጸየፍ፣ ስንፍናን የምንጸየፍ እና ተግተን የምንሠራ በመሆን ለልጆቻችን የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ በጋራ እንድንቆም አደራ እላልሁ።
- ኢትዮጵያ ለመበልጸግ በምታደርገው ጥረት የሚገጥማት ማንኛውም ፈተና ካለ፤ ከእያንዳንዱ ፈተና እና ተግዳሮት መልካም ዕድሎችን ፈልቅቀን እያወጣን የኢትዮጵያን ብልጽግና የምናፋጥን እንጂ በሚገጥሙን ፈተናዎች የምንቆም መሆን የለብንም።
በትብብር፣ በኅብረት፣ በመተጋገዝ ሀገራችንን ካለችበት ደረጃ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት እንድንሠራ አደራ እላለሁ።
- የውጭ ኩባንያዎች፣ የውጭ ዜጎች ሀገራችንን አምናችሁ በኢትዮጵያ ኢንቨስት የምታደርጉ በይበልጥ ትርፋማ እንድትሆኑ ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር እንድትዋሃዱ ልዩ በሆነ መንገድ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በኢንቨስትመንት ቦርድ በኩል ድጋፍ ያደርግላችኋል።
ለታማኝ ግብር ከፋዮች የተሰጠው ልዩ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትላንት በተካሄደው የታማኝ ግብር ከፋዮች የዕውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር፤ ባለፉት ዓመታት በታማኝነታቸው ለዘለቁ ግብር ከፋዮች ልዩ ዕውቅና ሰጥተዋል።
የወርቅ እና ከዚያ በላይ ተሸላሚ የሆኑ ታማኝ ግብር ከፋዮች ምርጥ ዜጎች ስለሆኑ፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲጓጓዙ በ”ቪአይፒ” እንዲስተናገዱ እና እንግልት እንዲቀርላቸው እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት በታማኝነት ግብራቸውን ሲከፍሉ የነበሩ 30 የፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ድርጅቶች ባለቤቶች ወይም ሥራ አስፈጻሚዎች ደግሞ፤ ኢትዮጵያውያን ከሆኑ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንደሚሰጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት ልዩ የፕላቲንየም ተሸላሚ ሆነው የቀጠሉ ታማኝ ግብር ከፋዮች፤ የኢትዮጵያ ልዩ ኩባንያ ሆነው በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ዕድገት እያስመዘገበች ስለሆነ ዕድገቷ በሀገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ መቅረት የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥ እነዚህ ኩባንያዎች በተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት ብቻቸውን ወይንም ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ሆነው ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ በየሀገራቱ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ልዩ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል ብለዋል።

