በሀገራችን የሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
ፕሮፌሰር በየነ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
“…..እየጨፈርን ያፈረስነውን ቤት እያለቀስን አንሠራውም!” ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ።
“ለሁላችንም ዘር አለን። ዘሩ ግን እኛ አይደለንም፤ እኛ ሰዎች ነን። ሰውነት ከመፈጠር እንጂ ከመወለድ አይጀምርምና ፈጣሪ ዘራችንን ኢትዮጵያ በምትባል ምድር ላይ ዘራው። ሲዘራው ኢትዮጵያ ማለት ሰዎች መሆኗን አወቅን። መነጣጠል እስከማንችል ተዋሃደናል። የሰው ዲስኩር አንዳችንን ካንዳችን ለማለያየት ስያሜ አበጀልን። ፈጣሪን ለማረም ይመስል እኛም ሆ… ብለን ተከተልን።
በሕንድ 2032 ብሔረሰብ በሠላም እየኖረ፤ በቻይና 499 ብሔረሰብ በሠላም እየኖረ፤ እኛ 80 ብሔር መሸከም አቃተን። ተራ በተራ መገዛታችንን ለበላይነት ተጠቀምንበት። ማንም ከማንም ጋር የዕውቀት እንጂ የሰውነት ጥል ሊኖረው አይችልም።
ገና ስንወለድ ዘር እና ቋንቋ ምን ይሁን የምናውቀው ነገር የለም። የዕውቀት ጥል በጠረጴዛ ዙሪያ እንጂ በጦር ሜዳ አይፈታም። ይቅርታ እንጂ በቀል ታሪክን አያርምም። በመቻቻል ሳይሆን በፍቅር እንኑር። መቻቻል አንድ ቀን ያሰለቸናል። ታገስኩህ ቻልኩህን ያመጣል። ፍቅር ግን እስከ ኦሜጋ ይሸከማል።
ከሰውነት በላይ ምንም ማንነት የለም፤ የሁሉም መገኛ የሁላችን አባት አዳም ነውና። የማይሻሩ እውነታዎችን ሽረን፤ የማይድን እያከምን የማይሞትን ገድለናል። ሁልጊዜ ጥፋት ካደረስን በኋላ እንዳጠፋን የሚንረዳ ከሆነ እየጨፈርን ያፈረስነውን ቤት እያለቀስን አንሠራውም። አትዮጵያዊነት ከዘር፣ ከቋንቋ በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለሁላችንም በቂ ናት! እንዋደድ በፍቅር እንኑር።

