መስከረም 25/2017 ዓ.ም በፀደይ እና በአቢሲኒያ ባንክ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅርንጫፎች ዝርፊያ መፈፀሙን የባንኮቹ ሥራ አሥኪያጆች ገልጸዋል።
የአቢሲኒያ ባንክ የግሸን ደብረ ከርቤ ቅርንጫፍ ኦፕሬሽን ሥራ አሥኪያጅ ዘውዱ ቀና እንደገለጹት ከቀኑ 11:30 ሰዓት አካባቢ ታጣቂ ኀይሎች ገብተው እገታ እንደፈፀሙባቸው ተናግረዋል።
በወቅቱ ባንኩ ለበዓሉ የመጡ በርካታ ተገልጋዮችን ሲያስተናግድ መቆየቱን ጠቅሰው ታጣቂዎቹ ደብድበው እና አስፈራርተው ካዝናውን ካስከፈቱ በኋላ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ የሚኾን ገንዘብ ዘርፈው መሄዳቸውን ገልጸዋል።
የፀደይ ባንክ የግሸን ደብረ ከርቤ ሥራ አሥኪያጅ አማረ ማሞ ከለሊቱ 5:30 ሰዓት ላይ በታጣቂዎች ከቤታቸው ታግተው መወሰዳቸውን እና ባንኩ ሲደርሱም ዘበኞቹ ታግተው እንደጠበቋቸው ገልጸዋል።
ከ25 እስከ 30 የሚደርሱ ታጣቂዎች በቦታው እንደነበሩ የሚገልጹት ሥራ አሥኪያጁ ካዝናውን አስፈራርተው እና ደብድበው ካስከፈቱ በኋላ ከ 4 ሚሊዮን 813 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በማዳበሪያ ይዘው መሄዳቸውን ገልጸዋል።
ሲሄዱም መረጃ ቢያወጡ በገዛ ሕይዎታቸው እና በቤተሰባቸው እንደፈረዱ በማስጠንቀቅ መኾኑንም ሥራ አሥኪያጆቹ ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ሥራ አሥኪያጅ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፍራው ቤተክርስቲያኗ በተፈፀመው የዝርፊያ ድርጊት ማዘኗን ገልጸዋል።
በተለይ አቢሲኒያ ባንክ ወደ ቦታው የሚሄደውን አማኝ እንዲያገለግል በሚል ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ እንዲሄድ የጋበዘችው ቤተክርስቲያኗ መኾኗንም አንስተዋል።
አትስረቅ የሚለው ቃል የቤተክርስቲያኗ ዋናው መመሪያ መኾኑን ጠቅሰው በባንኮቹ የተፈፀመው ዝርፊያ የተወገዘ መኾኑን ተናግረዋል።
ዘገባው፦ የአሚኮ ነው ።


