ከ8 ዓመታት በላይ ሀገሩን አሜሪካን በብቃትና በታማኝነት ያገለገለው አነፍናፊ ፖሊስ ውሻ ለጡረታ በመድረሱ የክብር አሸኛኘት ተደርጎለታል።
አፓቼ የተባለው አነፍናፊ ፖሊስ ውሻ በኢንዲያና ግዛት ፖሊስ የተሰጠውን ግዳጅ በብቃትና በታማኝነት እየተወጣ ከ8 ዓመታት በላይ አገልግሎ ለጡረታ በመብቃቱ ነው የክብር አሸኛኘት የተደረገለት።
አፓቼ በኢንዲያና ግዛት እ.ኤ.አ ከሴፕቴምበር 2016 ጀምሮ ከስራ አጋሩ ትሩፐር ዋልተር በት ጋር በውሻ ፖሊስ ቡድን በመደራጀት የተሰጠውን ግዳጅ በብቃትና በታማኝነት ሲወጣ ቆይቶ የጡረታ ጊዜው በመድረሱ በትናንትናው ዕለት ደማቅ የሽኝት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶለታል።
“በመርሐ ግብሩ ላይ አፓቼ የሚወዳቸውን ሁሉ ነገሮች ከሚወደው ህዝብ ተቀብሏል፤ የሚፈልገውን ክብርም አግኝቷል” ብሏል የግዛቲቱ ፖሊስ በመግለጫው።
“ከሚወዳቸው ሰዎች ጋር በተዘጋጀለት አዝናኝ የሽኝት መርሐ ግብር አፓቼ ከግዳጅ ተሰናብቷል፤ ቀሪ ጊዜውን በበት ቤተሰብ ውስጥ ከሕይወት ዘመን አጋሩ ትሩፐር ዋልተር በት ጋር በደስታ ያሳልፋል” ብሏል።
የኢንዲያና ግዛት ፖሊስ መግለጫ አፓቼ ከ8 ዓመታት በላይ በግዳጅ ላይ በቆየበት ወቅት የሰራውን ጀብዱ እና ገድል ያትታል።
እ.ኤ.አ በ2017 ለአለቃው አንገት ታልማ የተተኮሰችን ጥይት መሀል ገብቶ በማስቀረት አለቃውን ከሞት ታድጓል።
ይህን ተከትሎም ጥቃት አድራሹ እጅ ከፍንጅ የተያዘ ሲሆን፤ አፓቼም በ3 ሳምንታት ውስጥ ከደረሰበት ጉዳት አገግሞ ወደ ግዳጅ ተመልሷል ብሏል ኤቢሲ ኒውስ በዘገባው።
አፓቼ በኢንዲያና ግዛት ፖሊስ የስራ ቆይታው 954.28 ፓውንድ የሚመዝን አደንዛዥ እጽ (ናርኮቲክስ)፣ 167 ሕገወጥ ጠብመንጃዎች እና ከአደንዛዥ እጽ ሽያጭ የተገኘ 1.6 ሚሊዮን ዶላር እንዲያዝ አስችሏል።
በተጨማሪም ከፖሊሶች ጋር በመሆን 77 ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፤ 7 ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን በጥርሶቹ ነክሶ በመያዝ አስረክቧል።
ከአፓቼ ጀብዱ እና ገድል እዚህ የጠቀስነው ከብዙው በጥቂቱ ሲሆን፤ በዚህም “ለሰጠኸን አገልግሎት እናመሰግንሃለን፣ አፓቼ!” ተብሎ በኢንዲያና ግዛት ፖሊስ ተመስግኗል።
በመሐመድ ፊጣሞ ETV

