በቱሪዝም ሴክተር የጀመርነውን እንቅስቃሴ አጠናክረን በመቀጠል የኢትዮጵያን ልክ ለዓለም እንገልጣለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ቤኑና መንደር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ሀገርን በትጋት ለመለወጥ ቤኑና መንደር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ሀገርን በትጋት ለመለወጥ ትምህርት የሚወሰድበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በበሰቃ ሀይቅ ላይ የተገነባውን ቤኑና መንደርን መርቀው ከፍተዋል።
ቤኑና መንደር በበሰቃ ሃይቅ ዳርቻ እጅግ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎች፣ አዳራሽ፣ ሲኒማ ቤት የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ስፓ፣ እንዲሁም የፍራፍሬ ልማት እና የሌማት ትሩፋትን አካቶ የያዘ ነው።
የመንደሩ ግንባታም ባህላዊ የኪነ-ህንጻ ጥበብን ከዘመናዊ ግንባታ ጋር አቀናጅቶ የያዘ ሲሆን፣ ለአካባቢው ተጨማሪ የቱሪዝም አቅም የፈጠረ ወብ መዳረሻ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መንደሩን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቤኑና መንደር ይቻላልን በአይናችን ያየንበት ነው ብለዋል።
አካባቢው በጣም አስቸጋሪ የአየር ጠባይና መልክዓ ምድር እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህን በመቋቋም ውብ ገጽታ ያለውን መንደር እውን ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
ይህም ፈተና ኢትዮጵያን ከመቀየር እንደማያቆመን ዳግም ያረጋገጥንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
መንደሩ ከመዝናኛ ስፍራዎች በተጨማሪ የፍራፍሬ ልማትና የሌማት ትሩፋትን ማካተቱ ደግሞ ግብርናን ከቱሪዝም መዳረሻ ጋር ለማስተሳሰር ትምህርት የሚወሰድበት ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በመንደሩ የብርቱካን፣ የሎሚ፣ የፓፓዬና የማንጎ ልማት እንዲሁም ዶሮ፣ ግመል፣ ከብትና ፍየል የማርባት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የቤኑና መንደር ግንባታም በኢትዮጵያ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት ትብብር የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የስካይ ላይት ሆቴል መንደሩን ተረክቦ የማስተዳደር ስራ እንደሚያከናውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው አስታውቀዋል።
ህልማችን ልዕልና መር ነው – አቶ አደም ፋራህ
ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿን ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሻገር ዓላማ አድርጎ የተነሳው የለውጥ ጉዟችን 6 አመታትን ተሻግሮ፣ ብልፅግና ፓርቲም ከተመሰረተ 5 አመታትን አስቆጥሮ በታላላቅ ስኬቶች እና ድሎች ታጅበን ዛሬ ላይ ደርሰናል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገልጸዋል።
ፈተናዎችን ተሻግረን፣ጋሬጣዎችን ገፈን፣ ሰንኮፎችን ነቃቅለን ሊሳኩ የማይችል የሚመስሉ ድሎችን ማሳካት የቻልነው፣ ከባድ የሚመስሉ ወቅቶችን ለመሻገር አቅም ያገኘነው ህልማችን ልዕልና መር ስለሆነ ነው ሲሉም አቶ አደም ተናግረዋል።
አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በልዕልና መር ህልም እውን ማድረጊያ ጉዞ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ድሎችን አሳክተን ህዳሴ ግድብ ላይ ነፍስ ዘርተን፣ የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን ከማሟላት አልፈን ኤክስፖርት አድርገን፣ በአጠቃላይ በፈተናዎች ያልተረታ ዘርፈ ብዙ አማራጮች ያሉበት ኢኮኖሚ ገንብተን ኢትዮጵያን በማሻገር ካይ እንገኛለን ብለዋል።
የተወረወሩብንን ቀስቶች አምክነን፣ ለውድቀታችን የተመከሩ ዶሴዎችን በብልሀት ቀደን፣ የተሰነዘሩብንን ጥቃቶች ቀልብሰን በአይደፈሬ ኢትዮጵያዊ ማንነት ህልውናዋ የተጠናከረ ሀምራዊት ኢትዮጵያን በብልፅግናዊ ብሩሻችን እየሳልናት እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል።
ኮይሻን ገንብተን፣ ጎርጎራን አስውበን፣ ጨበራ ጩርጩራን መስርተን፣ የወንጪን ውበት ገልጠን፣ አዲስ አበባን እንደ ስሟ በአበባነት ተምሳሌት ቀርፀን ያልተቋረጠው የልዕልና መር የህልም ጉዞ ዛሬም የበሰቃ ሀይቅን ውበት ሊያጎላ ብቅ ብሏል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የ “ቤኑና መንደር” ግንባታ እነሆ ሌላኛው የልዕልና መር ጉዟችን ተጨማሪ ምስክርነት ሆኖ ዛሬ ለፍፃሜ መብቃቱ የተበሰረው በታላቅ ኩራት ነው ብለዋል።
ለእዚህም እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ደስ ያለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ENA

