በአዲስ አበባ ዘላቂ ማረፊያ የሆኑ የቀብር ስፍራዎች የሚያምር ገፅታ ኖሯቸው መናፈሻ እንዲሆኑ እየተሰራ ቢሆንም ‘’ሙታንን የሚያውኩ ነገሮች’’ በህግ ያስቀጣሉ ተብሏል፡፡
ቀብር የሚፈፀምባቸው ስፍራዎች በአብዛኛው ሰወር ያሉ፣ በደንና ቁጥቋጦዎች የተሞሉ እንደመሆናቸው እነዚህን ስፍራዎች ከነበራቸው አስፈሪ ገፅታ ወደ መናፈሻነት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን በአዲስ አበባ ካሉ የቀብር ስፍራዎች መካከል አንዱ የሆነው የቀጨኔ ዘላቂ ማረፊያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ድሪባ ገመቹ ነግረውኛል ሲል ሸገር ዘግቧል፡፡
‘’እውነት ነው የቀብር ስፍራዎቹ ለወንጀል ድርጊት የተመቹ ነበሩ፤ አሁን ግን ቦታውን ወደ መናፈሻነት ቀይረነዋል፣ ባሉን 17 የሚደርሱ የጥበቃ ባለሙያዎች ጥብቅ ቁጥጥር እያደረግን ነው’’ ብለዋል፡፡
አቶ ድሪባ ‘’ምንም አይነት ሙታንን የሚረብሹ ተግባራት’’ በህግ የሚያስጠይቁ መሆኑን በቅርቡ በመቃብር ስፍራው ሲጨፍሩ በመቅረፅ በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ ሰዎችን ጉዳይ በማንሳት አስረድተዋል፡፡
በቅርቡ አንዳንድ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ መቃብር ስፍራ ላይ በመሄድ ጭፈራ ሲያደርጉበት ነበር የተባለዉ የቀጨኔን መቃብር ስፍራን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ስር የሚተዳደሩ 15 ያህል ዘላቂ ማረፊያዎች አሉ፡፡
በዘላቂ ማረፊያዎቹ መደበኛ የቀብር አገልግሎት፣ የባይተዋር (ቀባሪ የሌላቸው በህመምም ሆነ በድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸው ያልተገኙ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቀብር ማስፈፀም፣ የግብዓተ መሬት ማስረጃ መስጠት፣ የሙታን መረጃ መስጠት፣ 7 ዓመት ሞልቷቸው የሚነሱ አፅሞችን ወደ ዴፖ የማዛወር ስራን በዋነኛነት የሚሰራ ነው ተብሏል፡፡
ዘላቂ ማረፊያዎቹንም በዘመናዊ መልክ በመስራት ቀብር ለመፈፀም ለሚመጡ ሰዎች ማረፊያ የሚሆኑ ቦታዎችን በማዘጋጀት በአጠቃላይ ደረጃቸውን የጠበቁ የዘላቂ ማረፊያ ስፍራዎችን አስገንብቶ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማድረጉን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
Via ሸገር ራዲዮ

