በቅርቡ የወጣው የIMF አመታዊ ሪፖርት ለመቃወም ሲባል ብቻ ጥርሳቸውን እንደሚፍቁበት የዘወትር ሙሾ አውራጆች እይታ ሳይሆን በበጎና በስጋት የሚነሱ ጉዳዮችን ያካተተ ነው። በስኬት ደረጃ የተቀመጡ ጉዳዮች እንዳሉ ሁሉ በስጋት ደረጃ የተዘረዘሩትም ተመልክተዋል።
ማንም ህሊና ያለው እንደሚመሰክረው ሪፖርቱ በደፈናው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የከሸፈ እንደሆነ አንድም ቦታ አልጠቀሰም። እንደውም በበጎ ጎኑ ወይም በስኬት ደረጃ ካነሳቸው ነጥቦች ውስጥ ተግባር ላይ ከዋለው ሪፎርም ማግስት የወጪ ንግድ ቀደም ሲል ይሸፍን ከነበረው ዘጠኝ መቶኛ የ GDP ወደ 12% ማሳደጉን አመልክቷል።
የዓለም የገንዘብ ድርጅት IMF ባወጣውን መግለጫ “የውጭ እርዳታ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ 12% ወደ 4% አሽቆልቁሏል” ማለቱን የኢትዮጵያ መንግስት ችግር አድርጎ በመውሰድ ወቀሳ፣ ትችትና ስላቅ የቀናቸው ኃይሎች፣ በቅርቡ የኃይማኖት አባቶች ወደ ትግራይ መሄዳቸውንና፣ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸውን የረገሙ አካላት መሆናቸው ዓላማቸው ምን እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
የተቋሙን ሪፖርት ጠቅሶ በቅድሚያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ላይ የተለመደውን የስድብ ጅራፉን ያነሳው ጃዋር መሐመድ፣ አፍታም ሳይቆይ የእምነት አባቶች ወደ መቀለ የሄዱት “ክረምቱ እስኪያልፍ ጊዜ መግዛ ነው” በማለት በሰላም መልዕከተኞች ጉዞ ያደረበትን ቁጣ አሳይቷል።
በኦእሮሚያ የሽብር ኃይል አደረጅቶ ንጹሃንን ያስበላ፣ ያሳረደና “ተከበብኩ” በማለት በርካታ ሰዎችን ያስፈጀው ጃዋር ዛሬም ጦርነት ይቀሰቀስ ዘንዳ ተግቶ እየሰራ ባለበት ወቅት የወጣውን የሪፖርቱን ስጋቶች ለቅሞ ለሚፈልገው ሁከትና ዕልቂት ግብአት ለማድረግ እየዳዳው ነው። አንዳንዶችም ይህንኑ በሚዘራበት የማህበራዊ አውዱ ስር በአግባቡ ምላሽ እየሰጡት ነው። ጃዋር ብቻ ሳይሆን በዚያው ሰፈር ያሉ የትርምስ ቡድኖች በገፊና ጎታች መርሃቸው አማካይነት ሪፖርቱን የብሶት ማጣደፊያ ሲያደርጉት ተስተውሏል።
- ኢትዮጵያን እያመሳት ያለው የገፊና ጎታች ሴራ ተጨማሪ ያንብቡ
ኢትዮጵያን እረፍት መንሳት፣ ማተራመስ፣ በታጠቁ ኃይሎች በታትኖ እጎበዝ አለቆች ላይ መጣል የኢሳያስና የጌቶቻቸው ዋንኛ ዕቅድ እንደሆነ ለሚረዱ፣ ይህንኑ የዘመናት የኢትዮጵያ ጠላቶች ህልም ለማሳካት የተሸጡ በገፊና ጎታች ስልታቸው እየተቀባበሉ ሽብር በማሰራጨት፣ የሃሰት ትርክት በመፍጠር፣ ሲፈልጉ እየተጣሉ፣ ሲያሻቸው እየተቃቀፉ ያለ አንዳች ሃፍረት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዲንኮታኮት ሌት ከቀን ይሰራሉ። መልሰው ሆን ብለው በሚሰሩት ደባ የሚታየውን ውጤት ለሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው ሰበር ዜና ያደርጋሉ።
ያም ሆኖ ሪፖርቱ በዋናነት በስጋት ያነሳቸው ጉዳዮች እየቀጠለ ያለው ግጭት ለኢኮኖሚው አደጋ መሆኑ፣ የውጭ እርዳታ ከአስራ ሁለት ወደ አራት በመቶ መቀነሱ፣ የትይዩ የውጭ ምንዛሬ (ጥቁር ገበያ) እያንሰራራ መምጣቱም ለኢኮኖሚ ማሻሻያው እንቅፋት መሆኑን ጠቅሶ ያቀረበው ማስጠንቀቂያዎች ናቸው።
አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም እንቅፋት ሊያጋጥመው ይችላል ሲል ትላንት ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ያስጠነቀቅውም ከላይ በተጠቀሱት ስጋቶቹ መነሻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን የሪፖርቱ የትኛውም ክፍል ላይ በገደምዳሜም ይሁን በቀጥታ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከሽፏል አይልም። እንዲያውም ከሪፎርሙ በኃላ የወጪ ንግድ የ GDP 12% መሸፈን መቻሉን፣ ቀደም ሲል አሃዙ 9% እንደነበር ጠቅሶ በስኬት አስቀምጦታል።
አይኤም ኤፍ በሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንዲሳካ ለማድረገ የሄደበትን ርቀት አድንቋል። አክሎም የድጎማ ቅነሳን ማካሄዱ፣ የታክስ ማዋቅሩ ማሻሻያ፣ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ የመሳሰሉትን እርምጃዎች አወድሷል።
የጸጥታ ችግር፣ ወደ ግል ይዞታነት መዞር የሚገባቸው ተቋማት የፕራይቬታይዜሽን ሂደታቸው መዘግየት፣ በረብሻ ምክንያት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳከም እና የወጪ ንግዱ ዘርፍ ዝቅተኛ አፈጻጸም ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግዳሮት መሆኑ አመልክቷል። በኤክስፖርት እድገት መታየቱን፣ በወርቅና ቡና የታየው ዕድገት በአገሪቱ ታሪክ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ እንደሆነ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካትም ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴርና የየተቋሙ መሪዎች ከበጀት ዓመቱ መጠናቀቅ ጋር አያይዘው ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ሲያስታውቁ መሰነበታቸው ይታወሳል።
ሊስት ፍረድሪክ በዋናነት የተጠቀሱትን ስጋቶች አስመልክቶ በማህበራዊ ገጹ ያሰፈረውን መረጃ ያንብቡ። ማን ነው የሚያተራምሰው? መልሶ አልቅሶ የሚያስለቅሰው? ይህስ ለሕዝብ ማሰብ ነው?
በብዙዎች IMF ሲወቀስ እያየን ነው። ከማውገዝ ውጪ ተቋሙ ስለ ኢትዮጵያ ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰናክሎች የሰጠውን አሰተያየት በቅጡ የተገነዘብነው አልመስለኝም። እስኪ እንመልከታቸው።
፩. የተራዘመ ግጭት
ሃገርህ በሽምቅ ተዋጊ እየታመሰ፣ በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ዜጎች እየታገቱና ተገደው ገንዘብ እየከፈሉ ባሉበት ሁኔታ መንግስት ምንም ዓይነት አጓጊ እና የጠራ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ቢያደርግ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አያመጣም። እንደውም የገቡት በስጋት መስራት ስለማይችሉ ይወጣሉ። ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት በኢንሹራንስ (political risk insurance) ሸፍነውና ታግሰው መስራት አይፈልጉም በተለይ ትክክለኛ የእድገት ምንጭ መሳሪያ ባለቤቶቹ። ኢኮኖሚና ፀጥታ መሳ ለመሳ የሚሄዱ ናቸው።
ታሪክን የኋሊት ከተመለከትን በስድሳዎቹም ተመሳሳይ ፈተና ገጥሞናል።
ለዚህም ነው፣ አስር ጊዜ ግጭት አያዋጣም በአንድ ሃገር ልጅነት ተባበሩ፣ ተወያዩ፣ ልዩነትን አጥብባችሁ ሃገራችሁን ከዚህ ክፉ ጊዜ ጠብቃችሁ አሻግሩ የምንለው።
፪. ጥቁር ገበያ
የውጭ ምንዛሬ በገበያው ተወስኖ እና የዶላር
እጥረት በሌለበት የጥቁር ገበያ ዋጋ የሚንር ከሆነ Financial Subversion እየተፈፀመ እንደሆነ መረዳት አይከብድም። በጥላትነት የፈረጅከውን አንድ ሃገር ኢኮኖሚውን የምታሽመደምድበት እና በተቋማቱ ላይ የህዝብ እምነት እንዲሸረሸር የምታደርግበት መንገድ አንዱ የወጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያውን በማናር ህጋዊውን ግብይት አደጋ ላይ መጣል ነው። የጥቁር ገበያ ተዋናዮችን በገንዘብ ይደጉማሉ፣ እንዲሁም እጅግ ለእውነት የቀረቡ ሃሰተኛ የብር ወረቀቶችን ያመርታሉ፣ ይበትናሉ። ለውጭ ምንዛሬ ገበያ ላይ ይውላል። እንዲሁም ለሽምቅ ታጣቂዎች ይሰጣሉ።
ለዚህም ከወትሮው የተለየ ጥብቅ የደህንነት ክትትል ሊደረግ ይገባል።
፫-የውጭ እርዳታ መቀነስ
ዘመኑ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የዓለም ፓለቲካና ኢኮኖሚ የደፈረሰበት ነው። ጦርነትና የንግድ መስተጓጎል፣ ባለ ብዙ ወገን የኢኮኖሚ ተቋማት ችግር ውስጥ የገቡበት ነው። ሁሉም ሃገር ከጋራ ጥቅም ይልቅ ብሄርተኛ Protectionist ሆኖ የራሱን ጥቅም የሚያሳድበት ሆኑዋል። ጦርነት ወጪ አለው፣ ከዜጎችህ ጉርሻ ላይ ቀንሰህ ለወታደራዊ ጉዳይ ታውላለህ።
ብዙ እርዳታ ሲለግስ የነበረው አውሮፓ በትራምፕ ተገዶ ከአመታዊ ምርቱ ላይ ወታደራዊ በጀቱ አምስት ከመቶ እንዲሆን ወስኗል። ይህ ለሌሎች ሃገራት የሚሰጠውን የልማት፣ የኢኮኖሚና የሰብአዊ እርዳታውን እንዲቀንስ ወይም እንዲያቆም ያደርገዋል።
አሜሪካ ከመቼው ጊዜ የባሰ የመንግስት ወጪ ቆጣቢ ፕሬዝዳንት መርጣለች። USAID ከተዘጋበት ምክንያት ከፓለቲካው ባለፈ ወጪ ቁጠባ ነው።
ራሽያም በጦርነት ተጠፍንጋልች እንኳን እርዳታ ልትሰጥ ቀርቶ። ቻይናም የቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሸቲቭ በሃገር ውስጥ የብድር ጫና ምክንያት ተዳክሟል። ስለዚህ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ የውጭ ሃገር የገንዘብ ድጋፍ የምናገኝበትን መንገድ በብልሃት ካልፈለግን እንዲሁ በብላኔ አይገኝም። በተለይ የውጭ ጉዳይ ፓሊሲያችንን በአግባባ ካልያዝነው ችግር ውስጥ የምንገባ ይመስለኛል። ለዚህም የሃገር ውስጥ ሰላም ወሳኝ ነው።
በአጠቃላይ IMF ለኢትዮጵያ ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሸያ መጓተት እንደምክንያት ያነሳቸው ጉዳዮች ትክክል ናቸው። እነዚህን በተለይ የእርስ በርስ ግጭትና ጥቁር ገበያን ለመፍታት መጣር አለብን። ከተቋሙ አቅም ውጪ ናቸው። የራሳችንን የቤት ስራ ሳንሰራ ተቋሙን ማማት አይነፋም።

