በሰሜን ወሎ ዞን ዝናብ ባለመዝነቡ የሰባት ቀን ጸሎተ ምኅላ መታወጁ ተገለጸ። ምህላ መታወጁን ያስታወቁት የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ናቸው። በዝናብ ችግር አርሶ አደሩ ዘር አለመዝራቱም ታውቋል።
ብፁዕነታቸው “ዝናብን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው ወደሱ ፊትን አዙሮ በጸሎትና በምልጃ መለመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ” ሲሉ በሰሜን ወሎ ዞን ለሚገኙ ምዕምናን የሰባት ቀን ፀለተ ምኅላ እንዲይዙ መታዘዙን አመልክተዋ።
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ለቲክቫህ እንደተናገሩት በዞኑ በተለይ ቆላማ በሆኑ ሁሉም በሚባሉ ወረዳዎች የዝናብ እጥረት በመከሰቱ ሰብል እንዳልተዘራና አርሶ አደሩም አዝኖ እንደተቀመጠ ገልፀዋል።
” ለወትሮው ከሚያዚያ ጀምሮ የሚዘሩ አዝርዕቶች ዘንድሮ በዝናብ እጥረት አዝርዕት አልተዘሩም ይባስ ብሎ በዚህ ክረምት የሚዘሩ እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ አተርና ጤፍ የመሳሰሉት ተዘርተው በቅለው የሚታዩበት ጊዜ ነበር።
አሁን የሚታዩ ምንም አይነት ቡቃያ የለም። በተለይ በጉባላፍቶ፣ ሀብሩ፣ በራያ እና አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ መጋቢት አካባቢ ያለን ነው የሚመስለው ምንም አይነት ቅጠል የለም መሬቱ ደርቆ ነው ያለው።
ዝናብን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው ወደሱ ፊትን አዙሮ በጸሎትና በምልጃ መለመን አማራጭ የሌለው መፍትሄ በመሆኑ ከሀምሌ 21/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ገዳማት፣ አድባራትና አጥቢያ አብያተክርስቲያን በመገኘት ምዕምናን ለሰባት ቀናት የሚቆይ ምኅላ ፀሎት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈናል መተላለፉን ተናግረዋል።
የመቄት ወረዳ አደጋ መካላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ የሆኑትን አቶ አታለል አለሙ፣ በወረዳው ባሉ 34 ቀበሌዎች ውስጥ በ19ኙ ቆላማ ቀበሌዎች ከፍተኛ ዝናብ እጥረት መከሰቱን ተናግረዋል። ይህም በግብርና ስራው ላይ ጥላ ማጥላቱን አመልክተዋል።
በ15 ደጋማ ቀበሌዎችም አጥጋቢ ዝናብ እየዘነበ አይደለም እንዲህ አይነት ችግር ደግሞ ሰብሉ ቢበቅል እንኳን ተባይና የሰብል በሽታ እንዲከሰት ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ትልቅ ስጋት ፈጥሯል ” ሲሉ አቶ አታለል ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በ11ዱ ወረዳዎች ከፍተኛ የዝናብ እጥረት መከሰቱን መረጃ እንዳላቸው የገለፁት አቶ አታለል ወትሮም ቢሆን አካባቢው የአፈር ለምነቱን ያጣ የምግብ ዋስትናውን ያላረጋገጠ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዘወትር ጦርነት ስፖንሰር በማድረግ የሚታወቁት የዲያስፖራ ፖለቲከኞች ድርቅ ያንዣበበትን ሕዝብ መርዳት እንኳን ባይችሉ አካባቢው ከጦርነት ስጋት ነጻ እንዲሆንና ልማት እንዲስፋፋ ተባባሪ እንዲሆኑ ከዚህ ቀደም መጠየቁ አይዘነጋም።
በኢትዮጵያ ራሳቸውን የሕዝብ መብት ተቆርቋሪና ተሟጋች አድርገው የሚያቀርቡ ግለሰቦች በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች አንድ እንኳን የውሃ ጉድጓድ አስቆፍረው እንደምያውቁ በመጥቀስ ትችት ሲሰነዘር መስማትም የተለመደ ነው።

