ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተመሰረተ የምግብ ጥገኝነትን በማስቀረት ራስን ለመቻል ሀገራት ለአየር ንብረት ተስማሚ የምግብ ፖሊሲ ሊተገብሩና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ሊያሳድጉ እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገለጹ፡፡
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ የመክፈቻ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንዲሁም የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ፣ የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ፣ የተመድ ምክትል ዋና ጸሀፊ አሚና መሀመድ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀመድ ዩሱፍ እና የሌሎች ሀገራት የሥራ ኃላፊዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ለጉባኤው ታዳሚዎች በበይነመረብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ከተመድ ጋር በመተባበር 2ኛውን የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በጋራ በማዘጋጀታቸው አመስግነዋል፡፡
ከመጀመሪያው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ወዲህ በርካታ ሀገራት በምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ዙሪያ ዕቅዶችን አዘጋጅተው መተግበራቸውን ተናግረዋል። ከ100 በላይ የሚሆኑ ሀገራትም የምግብ ሥርዓትን ከአየር ንብረትና ብዝሃ ሕይወት ጋር በማቀናጀት መተገብር መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚታየው አለመረጋጋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቁመው ይህም የሰዎችን ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ የመግዛት አቅማቸውን እየተፈታተነው እንደሚገኝ አንስተዋል። በምግብ ሥርዓት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት 17ቱን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል፡፡
ከአየር ንብረት ጋር የተጣጣመ የምግብ ሥርዓት ፖሊሲን ለማስፋፋት እየተወሰዱ የሚገኙ እርምጃዎች የማምረት አቅምን በማሳደግ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተመሰረተ ጥገኝነትን ያስቀራሉ ብለዋል። በምግብ ሥርዓት ላይ እየተተገበሩ የሚገኙ ኢኒሼቲቮች የስራ ዕድልን እየፈጠሩ እንደሚገኙም ዋና ጸሀፊው አስረድተዋል፡፡
ይህን ይበልጥ ለማሳደግም ከመንግስት በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን እና የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግ ብክነትን መቀነስ እና የእሴት ሰንሰለትን ማሳለጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል። ለታዳጊ ሀገራት የእዳ እፎይታ፣ አስፈላጊ የሆኑ የፋይናንስ አቅርቦትና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል። የምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማሳካት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ዕድገትን ለማፋጠን ሁሉም በጋራ መሥራት እንደሚገባውም ነው ያስገነዘቡት።

