ከአፍሪቃ ቀዳሚው፣ ከዓለም ስመ ጥር አየር መንገዶች ተርታ ስሙ የሚነሳው የኢትዮጵያ አየርመንገድ ከአዲስ አበባ ከተማ በ 45 ኪሎሜትር ርቀት ቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ የሚያስገነባው ግዙፍ ዘመናዊ አየር ማረፊያ በአራት ዓመት የሚጠናቀቅ ነው። ይህንኑ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና ከአፍሪካ የልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ዶክተር አኪንዉሚ አዴሲና ጋር ውል እንደሚፈጽሙ ተገለጸ።
በመጪው ሰኞ ነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአፍሪካ የልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዴሲና ጋር የሚፈራረሙት ለኢትዮጵያ አየርመንገድ አዲስ የአውሮፕላን ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት የሚውል $7.8 ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ ለማፈላለግ ነው።
አየር መነገዱ ቢሾፍቱ አቡሴራ አካባቢ ለሚያስገነባው በአፍሪካ ወደር የለሽ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ $10 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልገው ሲሆን ከዚህ ውስጥ $7.8 ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ የማፈላለግ ሃላፊነቱን የአፍሪካ ልማት ባንክ ወስዷል። ቀሪውን 20% የግንባታ ወጪው በኢትዮጵያ አየርመንገድ በኩል የሚሸፈን ይሆናል።

በቢሾፍቱ አቅራብያ ይገነባል የተባለው ግዙፍ አውሮፕላን ማረፍያ የሚያርፈው በ3,500 ሔክታር መሬት ላይ ነው። ይህ ግዙፍ የአየር ማረፊያ በዓመት 110 መንገዶችን የሚያስተናገድ ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያው እንደሆነ ተነግሮለታል።
ለግንባታው ሲባል ከቀያቸው 2,500 አባወራዎች በቂ ካሳና መኖሪያ ተሰርቶላቸው ይነሳሉ። ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው እነዚሁ ወገኖች አስፈላጊው ሁሉ ተሟልቶላቸው በሕዳር ወር ወደ አዲሱ መኖርያቸው እንደሚዘዋወሩ አስታውቀው ነበር። የሚዛወሩበት መኖሪያ ደረጃውን የጠበቀ፣ በቂ ካሳ የሚከናወንበት እንደሆነ መጠቆሙ በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርበው ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
እንግዲህ በመጪው ሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የአፍሪካ የልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዴሲና የፊርማ ስነ ስርዓት የሚያደርጉት ይህንኑ ግዙፍ አየር ማረፊያ ለማስገንባት ነው።
የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ግንባታ በመጪው ህዳር ወር ገደማ የሚጀመር ሲሆን ግንባታው በአራት ዓመት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ግንባታው ሲጠናቀቅ በዓመት በትንሹ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማጓጓዝ አቅም ይኖረዋል። አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ከነባሩ ቦሌ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ጋር በፍጥነት መንገድ እና በፈጣን የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር የሚተሳሰር ይሆናል።
በአፍሪካ ግዙፉን የሃይድሮኤሌክትሪክ ግንባታ በመጪው አዲስ ዓመት ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ያላችው ኢትዮጵያ፣ ከምረቃው ጎን ለጎን በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ግንባታ ይፋ ታደርጋለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያስገነባው አየር ማረፊያ ግንባታ ከአራት ዓመታት በኋላ የሚጠናቀቅ መሆኑን እና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደሚሆን ተገልጿል።
ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባው ይህ አዲሱ አየር መንገድ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን እደሚያስተናግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ግንባታው በሁለት ምዕራፍ የሚከናወን ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊዮን ተጓዦችን ማስተናገድ የሚችለው የአየር ማረፊያው ፕሮጀት ይገነባል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 50 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግደው ሁለተኛው ምዕራፍ ይገነባል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ እአአ በ2029 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ መስፍን ለቢቢሲ ከገለጹት ለመረዳት ተችሏል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለርዝም ዓመታት ማስፋፊያና እድሳት እየተደረገለት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
የአየር መንገዱ ዕድገት በጨመረ ቁጥር ለአውሮፕላን ማረፊያው የተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎች ሲከናወኑ ቢቆይም፣ በዓመት 25 ሚሊዮን ተጓዦችን ማስተናገድ በሚችልበት የመጨረሻ አቅሙ ላይ መድረሱን አቶ መስፍን አስታውቀዋል።
ይህ ግዙፍ የአየር መንገድ 1.1 ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ የመንገደኞች ተርሚናል እንዲሁም 126,190 ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ ለአየር መንገዱ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት፣100,000 ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ የጭነት አገልግሎት መስጫ እንደሚይዝ ተገልጿል።
አዲሱ በቢሾፍቱ አቅራቢያ የሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረርያ ጋር በፈጣን መንገድ እንዲሁም በፈጣን ባቡር እንደሚገናኝ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ለአዲሱ አየር መንገድ ግንባታ የሚውል የ7.8 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት አድርጓል። ከግንባታው አጠቃላይ ወጪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 20 በመቶውን ይሸፍናል።

